ብጹእ አቡነ ሼቭቹክ በዩክሬን የሚፈጸሙ የጦር ወንጀሎች መወገዝ አለባቸው አሉ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የካቲት 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ሩሲያ ጎረቤቷ በሆነችው ዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ የፈጸመችበት ቀን ሲሆን፥ ከሳምንት በኋላ ሁለተኛ ዓመቱ ታስቦ ይውላል ተብሏል። ሩሲያ ከአስር ዓመታት በፊት ክሬሚያን ለመቀላቀል ካካሄደችው ጦርነት የበለጠ የሟቾች ቁጥር እየጨመረ ነው ተብሏል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለተጎጂው ሕዝብ ያቀረቡት የሰላም ጥሪ ለመቁጠር እጅግ ቢያዳግትም፥ አሁንም በተጨማሪ ረቡዕ ዕለት በተደረገው አጠቃላይ የታዳሚዎች ጸሎት ስቃዩ እንዲያበቃ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ወቅታዊውን ሁኔታ በማስመልከት ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን በሆነው እገዛ ለምትሻ ቤተ ክርስቲያን እርዳታ የሚያደርገው ተቋም ባዘጋጀው ኮንፍረንስ ላይ የዩክሬን የግሪክ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ስቪያቶስላቭ ሼቭቹክ በሕዝቡና በአገራቸው ላይ እየደረሰ ስላለው አደጋ በቁጭት ገልጸዋል።
ኮንፈረንሱ የተካሄደው የሩሲያ ጦር የካቲት 13 ቀን 2006 ዓ.ም. በክሬሚያ እና አንዳንድ የምስራቅ ዩክሬን አከባቢዎች ወረራ የጀመረበትን 10ኛ ዓመት ለማስታወስ፥ እንዲሆም በተጨማሪ በ 2014 ዓ.ም. በዩክሬን ላይ የተደረገው ሙሉ ወረራ ለማስታወስ እንደሆነ ተነግሯል።
የዘንድሮውን የዐብይ ጾም ዘመቻውን ለዩክሬን ለማድረግ የወሰነው ፋውንዴሽኑ፥ በሀገሪቱ ያሉ ክርስቲያኖች ስላጋጠሟቸው ሁኔታዎች የበለጠ ለማወቅ ዝግጅቱን እንዳዘጋጀም ተገልጿል ።
ስቃይ እና ሞት ቀጥሏል
ሩስያ ሙሉ ወረራውን ከጀመረች ጀምሮ በነበሩ ሁለት ዓመታት ውስጥ የወታደራዊ ሰለባዎች ቁጥር ወደ ግማሽ ሚሊዮን ጨምሯል ሲል ራሱን ይፋ ያላደረገ ኤጀንሲ ግምቱን አሳይቷል።
ወደ 22,000 የሚጠጉ ሲቪሎች በጦርነት እና በአየር ድብደባ የተጎዱ ሲሆን፥ ወደ 17.6 ሚሊዮን የሚጠጉ ዩክሬናውያን ሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጿል።
በየቀኑ 6.2 ሚሊዮን ሰዎች ከዩክሬን ለቀው የሚሰደዱ ሲሆን፥ ከ5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ደግሞ በአገር ውስጥ ተፈናቅለው ይገኛሉ።
የጦር ወንጀሎች ውግዘት
በጉባዔው ወቅት ብፁዕነታቸው እንደተናገሩት “የጦር ወንጀሎችን ማውገዝ በጣም አስፈላጊ ነው” ሲሉ በቡቻ የተፈፀመውን እልቂት በማስታወስ፥ እነዚህ ወንጀሎች በፅኑ ካልተወገዙ የጦር ወንጀሎች በዓለም ላይ እንደሚስፋፉ አስጠንቅቀዋል።
ሊቀ ጳጳሱ አጥብቀው እንደገለጹት፥ ይህ ውግዘት ማለት ጦርነትን መቃወም እንደ ማለት ነው ብለዋል። የዩክሬን የግሪክ-ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ኃላፊ በመቀጠል “በዩክሬን ያሉ ሰዎች እየተገደሉ ያሉት ዩክሬናውያን በመሆናቸው ነው” ካሉ በኋላ
በተለይ ሕጻናት እና ቤተሰቦቻቸው እየሞቱ መሆኑን ገልጸው፥ ከ500 በላይ ሕጻናት ሕይወታቸውን እንዳጡ እና ከ1,200 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከጦርነቱ መጀመር በኋላ መቁሰላቸውን አስታውሰዋል።
ብፁዕ ብጹእ አቡነ ሼቭቹክ በተጨማሪም በርካታ የዩክሬን ልጆች ወደ ሩሲያ መባረራቸውን እና በርካታ ቤተሰቦች በዚሁ ጦርነት ምክንያት መለያየታቸውን አውግዘዋል።
በምስራቅ ዩክሬን ካህናት እንደሌሉ እና እዛ ያሉ ምዕመናን በሮቻቸው ወደ ታሸጉ አብያተ ክርስቲያናት ሊገቡ እንደማይችሉ በመግለጽ፥ በሀገሪቱ እጅግ ውድመት በደረሰባቸው አካባቢዎች የቤተክርስቲያን መገኘት እንዴት እንደሚከለከልም አብራርተዋል።
ከፍተኛ ስቃይ ቢደርስበትም እንደ ቤተ ክርስቲያን ‘ለሕዝባችን ተስፋ እየሰጠን ነው’ በማለት ምስጋናቸውን ገልጸው፥ በዓለም አቀፍ ትብብር “በዩክሬን ውስጥ በሰብዓዊ ጉዳዮች ማለትም በረሃብ ወይም ጥማት የሞተ አንድም ሰው የለም” በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
'ለመናገር በጣም ይከብዳል'
በተጨማሪም በዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የዩክሬን ሐዋርያዊ ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ቪስቫልዳስ ኩልቦካስ ዩክሬንን የሚጎበኙ ሰዎች ወደ አገራቸው ሲመለሱ ‘መናገር ያዳግታቸዋል’፥ ምክንያቱም ‘ባዩት ነገር በጣም ስለሚነኩ’ ነው ብለዋል።
ሊቀ ጳጳስ ኩልቦካስ አክልውም በፊት በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት አሁን ደግሞ በጦርነቱ ምክንያት “በአሁኑ ጊዜ ምንም ዓይነት ትምህርት ቤት አገልግሎት እየሰጠ አይደለም” በማለት በሀገሪቱ ስላለው የትምህርት ቀውስ አስጠንቅቀዋል።
በተጨማሪም የሰብዓዊ ድርጅቶችን በተለይም ‘ኤ ሲ ኤን’ የሚባለውን ዕርዳታ የሚፈልጉ ቤተክርስቲያናትን የሚረዳው ተቋምን ታላቅ ሥራ አጉልተው ገልጸዋል፥ ነገር ግን ትናንሽ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ብዙ ጊዜ ገንዘባቸው ስለሚያልቅ እና ድንበር የማቋረጥ ወይም አቅርቦትን የማቅረብ ችግር ስለሚያጋጥማቸው ‘ተስፋ ይቆርጣሉ’ ሲሉ በቁጭት ተናግረዋል።
በልጆች እና ቤተሰቦች ላይ የሚደረጉ ጥቃቶች
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሀዛዊ መረጃ እንደሚያሳየው በጥር ወር በሲቪል ዜጎች ላይ የደረሰው ጉዳት ከባለፈው ዓመት የህዳር ወር በ37 በመቶ ከፍ ያለ ሲሆን፥ ይህም በዋነኝነት በመላ ሀገሪቱ የሩሲያ ታጣቂ ሃይሎች በሚሳኤል እና በጦር መሳሪያ በታገዙ ጥቃቶች ምክንያት ነው ተብሏል።
እነዚህ ጥቃቶች ከግንባር መስመር ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች ላይ ጉዳት በማድረስ የተገደሉ እና የቆሰሉ ህጻናት ቁጥር ጨምሯል።
የተባበሩት መንግስታት ተልዕኮ መሰረት በጥር ወር 40 ህጻናት መገደላቸውን ወይም መቁሰላቸውን አረጋግጧል፥ ይህም በህዳር ወር ከነበረው ቁጥር በ18 መጨመሩን ያሳያል።
እርዳታ የሚፈልጉ ቤተክርስቲያናትን የሚረዳው ተቋም ለዩክሬን ያደረገው ድጋፍ
ይህ ኤሲኤን የተባለው የእርዳታ ተቋም 117 ሙሉ ክፍያ ፕሮጄክቶችን ጨምሮ 630 ፕሮጀክቶችን አጽድቋል፥ ይህም ከ16.5 ሚሊዮን ዩሮ በላይ የሚሆነውን የሁለቱም የዩክሬን የአምልኮ ሥርዓቶችን የሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለመደገፍ ነው ተብሏል።
በ 2014 ዓ.ም. እና በ2015 ዓ.ም. ለኤሲኤን በጎ አድራጊዎች ልግስና፣ ፀሎት እና መስዋዕትነት ምስጋና ይግባውና ዩክሬን በዓለም አቀፍ ደረጃ በተቋሙ የምትደገፍ ሀገር ሆናለች።
ከ2,200 የሚበልጡ ተፈናቃዮች በኤሲኤን በጎ አድራጊዎች በቀጥታ የሰብአዊ እርዳታ ተጠቃሚ ሆነዋል።