የጋዛ ህፃናት በሁለተኛው ዙር ለህክምና ወደ ጣሊያን መድረሳቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ህፃናቱን የያዘችው መርከብ ባለፈው አርብ ዕለት ከግብፅ አል ሃሪሽ ወደብ የተነሳችው፥ ህፃናቱ የራፋህ ድንበርን አቋርጠው ወደ ግብፅ ከገቡ በኋላ ነው።
ህፃናቱ ጥር 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ሰኞ ዕለት ጣሊያን የደረሱ ሲሆን፥ የኢጣሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ታጃኒ እና በፕሮጀክቱ ላይ ከጅምሩ ጀምሮ ትልቅ ተሳትፎ የነበራቸው እና ከግብፅ፣ ከፍልስጤም እና ከእስራኤል ተቋማት ጋር የተለያዩ የሎጂስቲክስ ችግሮችን ለመፍታት የማስተባበር ሥራውን ሲሰሩ የነበሩት የቅድስት ሀገር ተንከባካቢ ካህን የሆኑት አባ ኢብራሂም ፋልታስ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የጣሊያን 'ምርጥ ገፅታ'
አባ ፋልታስ የተሰማቸውን ደስታ፥ በሌላ ጎኑ ደግሞ ያላቸውን ሀዘን ሲገልፁ፥ “ይህ ኦፕሬሽን በመሳካቱ ታላቅ የደስታ ቀን ነው፥ ነገር ግን እነዚህ ህጻናት የደረሰባቸውን አሳዛኝ ሁኔታ ማየቱ ጥልቅ ሀዘን ውስጥ ይከታል፥ አንዳንዶቹ በከባድ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፥ በተዘጋጁት አምቡላንሶች ወዲያውኑ ለቀዶ ጥገና ወደተመደቡ በአቅራቢያው ወደሚገኙ፣ በፍሎረንስ ከተማ ወደ ሚገኘው ሜየር ሆስፒታል እና ጋስሊኒ ከተማ ወደሚገኘው ጄኖዋ ሆስፒታል አድርሰዋቸዋል” ብለዋል።
ካህኑ በማከል “በድጋሚ ጣሊያን ምርጥ ገፅታዋን እና ለሰብአዊ ዕርዳታ ያላትን ቁርጠኝነት አሳይታለች፥ ለዚህም ይህ ፕሮጄክት እንዲተገበር ከወታደራዊ እና ሲቪል ባለስልጣናት ውስጥ ትልቅ ትብብር ሲያደርጉ የነበሩትን ወክለው እዚህ የተገኙትን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታጃኒን ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ” በማለት ንግግር አድርገዋል።
ከጅምሩ መጠነ ሰፊ ሥራ ሰርተዋል
የቅድስት ሀገር ተንከባካቢ ካህን የሆኑት አባ ፋልታስ በጋዛ ውስጥ አስቸኳይ የህክምና እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ህጻናት ብዛት ግምት ውስጥ በማስገባት ፕሮጄክቱ በቀጣይነት ተስፋፍቶ እንደሚቀጥል ያላቸውን ተስፋ አካፍለዋል።
በሌሎች በርካታ የጣሊያን ሆስፒታሎች የተገለፀውን በፕሮጄክቱ የመሳተፍ ፈቃደኝነትን በደስታ የተቀበሉ ሲሆን፥ እነዚህ በመጀመሪያ ዙር የመጡት ህፃናት ምናልባትም ለትልቁ ሥራ እንደመግቢያ ይቆጠራል ብለዋል። ሆኖም ግን ወደ ራፋህ እየተስፋፋ የመጣው በጋዛ ደቡባዊ ክፍል እየተካሄደ ያለው የቦምብ ድብደባ ሁኔታውን የበለጠ ፈታኝ ያደርገዋል በማለት ያለውን ችግር ገልጸዋል።
አባ ኢብራሂም ፋልታስ የተሰማቸውን ከባድ የሆነ ስሜት ሲገልጹ፥ “ዛሬ ጠዋት ዕድሜያቸው ከ 4 ወር እስከ 18 ወር የሚሆናቸው ህፃናት ወላጆቻቸው በጦርነቱ ምክንያት ስለሞቱባቸው ብቻቸውን ያለ አስታማሚ እዚህ መጥተው ሳያቸው ልቤ ክፉኛ አዝኗል” በማለት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል።
“አብዛኛዎቹ እንደነገሩኝ ከሆነ ከፍርስራሽ ሥር እንደተገኙ ነው” ያሉት አባ ፋልታስ፥ “እንደ አለመታደል ሆኖ ከአስተባባሪዎቹ ውስጥ አንዳቸውም አረብኛ መናገር ስለማይችሉ፥ ህጻናቱ ከእኔ ጋር ጥብቅ ግንኙነት የፈጠሩ ሲሆን፥ ተለይቻቸው እንድሄድም አልፈለጉም ነበር” ብለዋል።
“ከህፃናቱ ውስጥ በጣም ትንሹ 'አባዬ' ብሎ ጠራኝ። ይህ ብዙ ነገር ይነግረናል፥ ይህንን ተግባር በፍጹም መቀጠል አለብን ፤ አሁንም ትኩረት የሚሻ ብዙ መከራ በጋዛ ውስጥ አለ” በማለት ኦፕሬሽኑ እንዲቀጥል ጥሪ አድርገዋል።
ህፃናቱ ቀደም ሲል የተገለጹትን የሜየር እና ጋስሊኒ ሆስፒታሎችን ጨምሮ፥ በቦሎኛ በሚገኘው ሪዞሊ ሆስፒታል እንዲሁም የመለየት እና የመጀመሪያ መስተንግዶን ያስተናገደው ሮም በሚገኘው ባምቢኖ ገሱ ሆስፒታሎች እና ወደ ተለያዩ የህጻናት ህክምና መስጫ ሆስፒታሎች እንደተወሰዱም ተነግሯል።