በሊባኖስ የሚገኝ የማልታ ሉዓላዊ ሠራዊት ማኅበር በሊባኖስ የሚገኝ የማልታ ሉዓላዊ ሠራዊት ማኅበር  

በሲቪሎች እና የዕርዳታ ሠራተኞች ላይ የሚፈጸም ጥቃት በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው ተባለ

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2024 ዓ. ም. በጀርመን ሙኒክ ከተማ በተካሄደ የሙኒክ የጸጥታ ጉባኤ (ኤም.ኤስ.ሲ) ጎን ለጎን፥ የማልታ ሉዓላዊ ሠራዊት ማኅበር በሲቪል ሕዝብ እና ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች በሚገኙ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች መሆናቸውን በድጋሚ ገለጸ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሀገር መሪዎች፣ የመንግሥት ባለ ስልጣናት እና ፖሊሲ አውጭዎች ዓርብ የካቲት 8/2016 ዓ. ም. በጀርመን ሙኒክ ከተማ ባደረጉት 60ኛው የጸጥታ ጉባኤ ላይ አሳሳቢ በሆኑ ወቅታዊ የዓለም የጸጥታ ስጋቶች ላይ ተወያይተዋል። አባላቱ በመካከላቸው ያለውን ትብብርን ለማሳደግ የተስማሙ ሲሆን፥ ከዚህ ጉባኤ ጎን ለጎን የማልታ ሉዓላዊ ሠራዊት ማኅበርም በበኩሉ በአስቸጋሪ ሁኔታ እና ጂኦፖለቲካዊ ግጭቶች ባሉበት በዚህ ወቅት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ እንዲከበር አስቸኳይ ጥሪ አቅርቧል።

በግጭቶች ውስጥ የሚደረግ የዜጎች ጥበቃ አስቸኳይ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል

በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እና በጋዛ ሰርጥ በተከሰተው ጦርነት እንደታየው ለሲቪሎች እና ለሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች ደኅንነት አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል ሲሉ የማልታ ሉዓላዊ ሠራዊት የተባለ ካቶሊካዊ ማኅበር ፕሬዝደንት አቶ ሪካርዶ ፓተርኖ ዲ ሞንቴኩፖ ተናግረዋል።

የማኅበሩ ፕሬዝደንት ይህን የተናገሩት፥ ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች ደኅንነት በማስመልከት በጀርመን-የባቫሪያ ግዛት ዋና ከተማ በሆነች ሙኒክ ዓርብ የካቲት 8/2016 ዓ. ም. በተካሄደው “የሙኒክ የጸጥታ ጉባኤ” ላይ እንደሆነ ታውቋል። "በጤና አጠባበቅ ተቋማት እና በሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች ላይ ሆን ተብሎ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በማንኛውም ረገድ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ናቸው" ሲሉ በድጋሚ ተናግረዋል።

ግጭት ውስጥ የሚገኙ ሲቪሎች ማዕከል በሚባል ተቋም ድጋፍ የማልታ ሉዓላዊ ሠራዊት ማኅበር ያዘጋጀው ጉባኤ ዋና ዓላማ፥ በዓለማችን ውስጥ በየቀኑ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እያፈናቀሉ እና ለሕይወት አስጊ የሆኑ ወቅታዊ አደጋዎችን ለማስቀረት ያለመ እንደሆነ ታውቋል። ግጭቶች እና ጦርነቶች ባሉባቸው አካባቢዎች የሚገኙ በርካታ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች፣ መኖሪያ ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች እና የአምልኮ ቦታዎች ጨምሮ የሲቪል ሕንጻዎች የወታደራዊ ጥቃቶች ኢላማ ሆነዋል። መሠረታዊ የኃይል አቅርቦት መሠረተ ልማቶች ሰላማዊ ዜጎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ማግኘት በማችሉበት ሁኔታ ተበላሽተዋል ወይም ወድመዋል። እንደ ቀደሙት ግጭቶች ሕጻናት፣ ሴቶች፣ አረጋውያን እና ሌሎች ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሆን ተብሎ ለሞት ተዳርገዋል።

በጀርመን ሙኒክ ከተማ ከተካሄደው የጸጥታ ጉባኤ ጎን ለጎን የማልታ ሉዓላዊ ሠራዊት ማኅበር ያዘጋጀው መድረክ ዋና ትኩረት የእምነት ተቋማት እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መርሆች እና ሕጎች እንዲከበሩ በማለት የሚያቀርቡት ጥሪ ውጤታማ በሚሆንበት መንገድ ላይ እንደ ነበር ታውቋል።

ዩክሬን እና ጋዛ ብቸኛው የሰብዓዊ ቀውሶች የሚታዩባቸው ቦታዎች አይደሉም

የማልታ ሉዓላዊ ሠራዊት የተባለ ካቶሊካዊ ማኅበር ፕሬዝደንት አቶ ሪካርዶ ፓተርኖ ዲ ሞንቴኩፖ በመግቢያ ንግግራቸው፥ በዩክሬን እና በጋዛ ሰርጥ በሲቪሎች እና በዕርዳታ ሠራተኞች ዘንድ በግልጽ የሚታዩ ቀውሶች ጥቂቶቹ ብቻ እንደሆኑ ጠቁመው፥ እንደ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶርያ፣ ሄይቲ፣ ምያንማር እና ለሌሎች የመሳሰሉ ክልሎች በግጭት የተሞሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶችን መቀላቀል

የማልታ ሉዓላዊ ሠራዊት ካቶሊካዊ ማኅበር በግጭት ዞኖች የሚገኙ ሰላማዊ ዜጎችን በአካባቢ፣ በጾታ እና በሃይማኖት ሳይለይ ከአደጋ ለመጠበቅ የተጫወተውን ሚና ያስታወሱት የማኅበሩ ፕሬዝደንት አቶ ሪካርዶ ፓተርኖ ዲ ሞንቴኩፖ፥ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች፣ የእምነት ተቋማት ወይም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተሳትፏቸውን በማጠናከር ለዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ መከበር የጋራ ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

“የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች በመሠረታዊ ዓላማ ዙሪያ በመሰባሰብ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግን ለማስክበር በምጣኔ ሃብት ከበለጸጉ እንደ G7 እና G20 ካሉ መንግሥታት እና ዋና ዋና ዓለም አቀፍ መድረኮች ጋር በመቀናጀት የጥብቅና እንቅስቃሴአቸውን ወደ ፊት ማምጣት እንደሚችሉ የማልታ ሉዓላዊ ሠራዊት ካቶሊካዊ ማኅበር ያምናል” ሲሉ አቶ ሪካርዶ ፓተርኖ ዲ ሞንቴኩፖ ተናግረዋል።

በጉባኤው ላይ ንግግር ካደረጉት እንግዶች መካከል የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አቶ ባን ኪሙን፣ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፊሊፖ ግራንዲ፣ የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ኤሚ ፖፕ፣ የዓለም ቀይ መስቀል ኮሚቴ ፕሬዝደንት ወ/ሮ ሚርያና ስፖልያሪክ ኤገር፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ 1997 ዓ. ም. የኖቤል ሽልማት አሸናፊ የነበሩት ጆዲ ዊሊያምስ እና የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ናጂብ ሚካቲ ይገኙበታል።

ለጥቃት የተጋለጡ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች

ባለፉት አምስት ወራት ቢያንስ 167 የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች የሞቱበትን የጋዛ ሰርጥ ጨምሮ በግጭት አካባቢዎች የተገደሉትን የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች አስመልክተው የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አቶ ባን ኪሙን ያቀረቡት አስገራሚ አሃዝ የጉባኤውን ተካፋዮች ትኩረት ስቧል።

የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ኤሚ ፖፕ እና የዓለም ቀይ መስቀል ኮሚቴ ፕሬዝደንት ወ/ሮ ሚርያና ስፖልያሪክ ኤገር፥ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞችን በየዕለቱ የሚያጋጥሙ ስጋቶችን እና ቀጥተኛ የጥላቻ ንግግሮች እየጨመሩ መሄዳቸውን አውግዘዋል። በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፊሊፖ ግራንዲ፥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ስደት የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ ጥሰት ቀጥተኛ ውጤት ነው ብለዋል።

በዓለማችን ቢያንስ 114 ሚሊዮን የተፈናቀሉ ሰዎች አሉ

"ለዓለም አቀፍ ሕግ የሚሰጥ ክብር ሲቀንስ የተፈናቃዮች ቁጥር ይጨምራል" ያሉት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፊሊፖ ግራንዲ፥ በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ላይ ቢያንስ 114 ሚሊዮን ተፈናቃዮች እንዳሉ ጠቁመዋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ 1997 ዓ. ም. የኖቤል ሽልማት አሸናፊ የነበሩት ወ/ሮ ጆዲ ዊሊያምስም በበኩላቸው፥ “የሁሉንም ሰው መሠረታዊ ፍላጎቶች ማሟላት ይገባል” ሲሉ ልባዊ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

 

 

 

 

 

19 February 2024, 16:44