ሶርያውያን ለሌላ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ እንደሚሰጉ እና ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተነገረ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ከአንድ ዓመት በፊት በሬክተር መለኪያ 7.8 የተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ በደቡብ ምሥራቅ ቱርኪ እና ሰሜን ሶርያ በአጠቃላይ ወደ 60,000 ለሚጠጉ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል። ቀድሞውንም ለአሥራ ሦስት ዓመታት ያህል በጦርነት በወደመች ሶርያ አደጋው ከ6,000 እስከ 10,000 የሚደርሱ ሰዎችን ገድሏል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከየካቲት 6/2010 ዓ. ም. ጀምሮ አንድ ዓመት ያስቆጠረው አውዳሚ የመሬት መንቀጥቀጥ በክልሉ ነዋሪዎች ላይ አሁንም አዲስ ስጋት በመፍጠር በጦርነት ሁከት እና ታይቶ በማይታወቅ የኢኮኖሚ ቀውስ ሕዝቡን ለድህነት ዳርጎታል። ወደ 5.6 ሚሊዮን የሚጠጉ ሶርያውያንን ሲመግብ የቆየው የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ፕሮግራም (WFP) በቅርቡ በአካባቢው የሚሰጠውን የምግብ ዕርዳታ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ማቋረጡ ይታወሳል።
የ “ብሉ ማርስት” ማኅበር አባል ወንድም ጆርጅ ሳቤ የሚኖረው በመሬት መንቀጥቀጥ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው የሶርያ ሰሜናዊ ምዕራብ ከተሞች አንዷ በሆነችው አሌፖ ውስጥ ነው። ወንድም ጆርጅ ሳቤ ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስቃይ ውስጥ የሚገኘውን የአካባቢውን ሕዝብ እንዳይተው ተማጽኖ፥ እንዲሁም ማኅበሩ የአሌፖ ከተማ ነዋሪዎች ተስፋ ለመመለስ ዕለት ተዕለት እየሠራ እንደሚገኝ አብራርቷል።
ቁሳዊ ጉዳት እና የሥነ-ልቦና ጉዳት
በከተማዋ ከ500 እስከ 600 የሚደርሱ ቤታቸው የፈረሰባቸው አባወራዎች አሁንም ተፈናቅለው እንደሚገኙ የገለጸው ወንድም ጆርጅ ሳቤ፥ ሌሎች ብዙ ሰዎች የሚሄዱበት ቦታ ስለሌላቸው እና መልሶ ግንባታ ገና እየመጣ በመሆኑ ደህንነታቸው ባልተጠበቀ ቤቶች ውስጥ እንደሚኖሩ አስረድቷል።
ወንድም ጆርጅ ሳቤ ከንብረት መውደሙ በተጨማሪ የሥነ ልቦና ቀውስ መኖሩን ተናግሮ፥ በርካታ ሕፃናት፣ ጎልማሶች፣ ወጣቶች እና አዛውንቶች የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ እንደገና እንዳይከሰት ፈርተው ልብሳቸውን ለብሰው እንደሚተኙ፥ እስከ አሁን ድረስ በምሽትም ሆነ በቀን ከወላጆቻቸው መለየት የማይፈልጉ ብዙ ልጆች እንዳሉ አስረድቷል። የመሬት መንቀጥቀጡ የጦርነት ጉዳትን እንደሚጨምር የገለጸው ወንድም ጆርጅ ሳቤ፥ ዛሬ የሰዎችን የደህንነት ስሜት እንደገና መገንባት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ እንደሆነ ተናግሯል።
በሶርያ ላይ የተጣለው ዓለም አቀፍ ማዕቀብ በሕዝቡ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል
“ጦርነቱ ካስከተላቸው መዘዞች አንዱ በሶርያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ያስከተለው የኢኮኖሚ ቀውስ ነው” ያለው ወንድም ጆርጅ ሳቤ፥ “ምንም እንኳን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ “በሶርያ ሕዝብ ላይ አላነጣጠርኩም” ያለ ቢሆንም ማዕቀቡ ግን በዕለት ተዕለት ኑሮው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳስሯል” ብሏል።
ውስን የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዕርዳታ
ወንድም ጆርጅ ሳቤ መንግሥታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በታየው የሰብዓዊ ዕርዳታ እጥረት የተሰማውን ሐዘን ገልጾ፥ እንደ ጎርጎሮሳያኑ ከጥር 1/2024 ጀምሮ የመንግሥታቱ ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለሶርያ የሚሰጠውን ማንኛውንም ዓይነት ዕርዳታ ማቆሙን በማስታወስ፥ በግሉ በዚህ ነጥብ ላይ “የሚሰቃየውን ሕዝብ የመተው መብት የለንም ብዬ አምናለሁ" ካለ በኋላ፥ “ዛሬ ሕዝቡ በድህነት እና በሰቆቃ ውስጥ መኖሩን በምን መብት ነው የምንቀበለው?” በማለት ጠይቋል።
"ክብራችን ተጠብቆ መኖር አለብን"
ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዕርዳታ እንዲደረግለት ተማጽኖን ያቀረበው ወንድም ጆርጅ ሳቤ፥ “ምንም እንኳን ብዙ ችግር ቢደርስብን እና ዕድለ ቢሶች ብንሆንም ነገር ግን ለማኞች ባለመሆናችን ክብራችን ተጠብቆልን መኖር አለብን፣ የሚደረገልን ዕርዳታ ወደ ቀድሞ ኑሮአችን ለመመለስ የሚረዳን እንጂ ወደ ልመና የሚዳርገን መሆን የለበትም” ብሏል።
አሁንም ተስፋ አለን!
ወንድም ጆርጅ ሳቤ በቃለ ምልልሱ፥ “ምንም እንኳን ይህ መጥፎ ገጽታ ቢኖርም በእምነት ላይ የተመሠረተ ተስፋ አሁንም አለ፤ እግዚአብሔር እንደማይተወን ማመን አለብን፤ በዚህ ተስፋ ላይ በመመስረት ከሌሎች ጋር መገናኘት አለብን፤ እምነታችንም ወደ ፊት እንድንጓዝ ይረዳናል” ብሏል
“ይህ በአሌፖ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የ “ብሉ ማርስት” ማኅበር አገልግሎት ዋና ግብ ነው” ያለው ወንድም ጆርጅ ሳቤ፥ ማኅበሩ በተጨባጭ መንገድ ተስፋ መዝራትን ለመቀጠል እየሠራ እንደሚገኝ፥ ለተራቡት ምግብ በማደል፣ ሥነ-ልቦናዊ ድጋፍ በመስጠት፥ ትምህርትን በማዳረስ፣ ልማትን በማስተዋወቅ እና ችግረኞች የቤት ኪራያቸውን እንዲከፍሉ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጿል።