2023.08.04 Viaggio Apostolico in Portogallo in occasione della XXXVII Giornata Mondiale della Gioventu' - Confessione di alcuni giovani della GMG

ምስጢረ ንሰሐ

ፕሮቴስታንቶች በሙሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን እንደሰጣቸው ይክዳሉ፡፡ ስለ ምሥጢረ ንስሐ ለመወያየት የዮሐንስ ወንጌል 20 19-23 ያለውን ሐሳብ በደንብ ማወቅ አለብህ።ኢየሱስ ይህንን ሥልጣን ለሐዋርያቱ የሰጣቸው በፋሲካ በዓል ዕለት በሰንበት ቀን ነው፡፡

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ይህም በመንፈሳዊ ሕይወት በምሥጢረ ንስሐ ትንሳኤ ከማድረግ ጋር ይተሳሰራል፡፡ ጌታ ሥልጣኑን የሰጣቸው በእነርሱ ላይ በመተንፈስ እንደሆነ አስተውል፡፡ አምላክ ከዚህ ውጪ ‹‹እፍ›› ብሎ በመተንፈስ ሲሠራ ያየነው በኦሪት ዘፍጥረት የመጀመርያውን ሰው አዳምን በፈጠረበት ጊዜ ነው (ዘፍ2፡7)፡፡ ከፕሮቴስታንቶች ጋር ስትወያይ እነዚህን ኃይለኛ ምሳሌዎች ወይም ምልክቶች እንዲያስተውሉ እና ለሐዋርያቱ የተሰጣቸውን ሕይወት ሰጪ ኃይል እንዲገነዘቡ ጠይቃቸው፡፡ ኢየሱስ ለሐዋርያቱ የሰጠው ሥልጣን ኃጢአትን የማሰር እና የመፍታት ሥልጣን መሆኑን ልብ በል፡፡ ይህ ማለት ካህኑ ኃጢአትን ይቅር ለማለት ወይም አስሮ ለማቆየት መጀመሪያ ከኃጢአተኛው አንደበት በደሉን መስማት አለበት፤ ይህ ንስሐ ይባላል፡፡

ፕሮቴስታንቶች ‹‹እኛ ኃጢአታችንን ለእግዚአብሔር ስንናዘዝ ካቶሊካውያን ግን ለካህናት ብቻ ይናዘዛሉ›› ብለው ያስባሉ፤ይህ በጣም የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡ ካቶሊካውያን ዘወትር ኃጢአታችንን ለእግዚአብሔር እንናዘዛለን፡፡ ነገር ግን መፅሐፍ ቅዱስ በግልፅ እንደ ሚያስተምረው ይህንን ተግባር የምንፈጽመው በምድር ላይ የእግዚአብሔር ወኪል ሆኖ ንስሐችንን ለመቀበል በመንበረ ኑዛዜ ውስጥ በሚጠብቀን በካህን በኩል ነው፡፡

ሁለተኛ ቆሮንቶስ 5፡17-20 ያለውን ክፍል አጥና፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ሐዋርያት የዕርቅ አገልግሎት አምባሳደርነት ያብራራል! ይህ ምን ማለት ነው? በእርግጥ ሐዋርያት የማስታረቅን አገልግሎት ከክርስቶስ ተቀብለው በእርሱ ስም ኃጢአትን ይቅር ይላሉ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ያዕቆብ 5፡13-16 ያለውን ሐሳብ አጥና፡፡ ያዕቆብ የህመምተኞች ኃጢአት በምሥጢረ ቀንዲል (በተባረከ ዘይት) እንደሚደመስስ በግልጽ ይናገራል፡፡ በዚህ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች (ካህናት) መገኘት እንዳለባቸው ያብራራል፡፡ እነዚህ ካህናት ከሕዝብ ክርስቲያን የተለየ ለእነርሱ ብቻ የተሰጠ ኃይል አላቸው፤ ይህም ኃጢአትን ይቅር የማለት ኃይል ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ያዕቆብ ይህንን ሥርዐት ለመፈጸም እነርሱን ለይቶ መጥራት ፋይዳው ምንድነው? ካህናቱ ሥልጣን ባይኖራቸው ኖሮ በሌሎች በርካታ አጋጣሚዎች እንደሚገኘው ሁሉ ከሕዝበ ክርስቲያን መካከል ማንኛውም ሰው ይህንን ሥርዐት ለመፈጸም ብቁ ሆኖ በቀረበ ነበር፡፡

በርካታ ፕሮቴስታንቶች ጥምቀት ኃጢአትን እንደሚደመስስ ያምናሉ፡፡ ይህ ማለት እግዚአብሔር የጥምቀትን ሥርዐት በሚፈፅሙት አገልጋዮቹ ተጠቅሞ ኃጢአታቸውን ይቅር ይላቸዋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አገልጋዮች እግዚአብሔር ኃጢአትን ከሰው ልጆች ነፍስ ላይ ለማስወገድ የሚጠቀምባቸው መሣርያዎች ናቸው፡፡ ካቶሊካውያንም በዚሁ መልኩ ካህናት የእግዚአብሔር መሳርያዎች እንደሆኑ እናምናለን፡፡ እግዚአብሔር በሦስቱ መንገዶች ካህናትን በመጠቀም የኃጢአት ሥርየት ይሰጠናል፤ እነዚህም ንሰሐ፤ ቀንዲል እና ጥምቀት ናቸው፡፡ እንግዲህ ፕሮቴስታንቶች እግዚአብሔር የእነርሱን አገልጋዮች ተጠቅሞ የሚፈውስ ከሆነ፣ ዕውራንን የሚያበራ ከሆነ፣ ሽባውን የሚተረትር ከሆነ ታዲያ ከዚህ በላይ ለሆነው መንፈሳዊ ፈውስ እግዚአብሔር የሰው ልጆችን የማይጠቀምበት ምክንያት ምንድነው? አካላዊ ፈውስ ለመስጠት የሚያገለግሉ መሳሪያዎች ሆነው የተመረጡ አገልጋዮች አሉ ካልን መንፈሳዊ ፈውስ ለመስጠት የሚያገለግሉ መሳሪያዎች ሆነው የተመረጡ አገልጋዮች የሉም እንዴት እንላላን?

 በመጨረሻ ወደ ዮሐ 20፡21 ተመለስ “አብ እኔን እንደላከኝ እኔ ደግሞ እናንተን እልካችኋሉሁ” ይላል፡፡ ሐዋርያት የኢየሱስ ተልዕኮ ፈጻሚዎችና አስፈሚዎች ናቸው፡፡ የዚህ ተልዕኮ ማዕከላዊ ነጥብ የኃጢአት ሥርዓት ነው፡፡ ኢየሱስ ሰብዓዊ ማንነታችንን ያውቃል፡፡ ስለዚህ ምሥጢረ ንስሐን የሠራልን በርካታ ሥጦታዎችን ሊሰጠን ፈልጎ ነው፤ እነዚህም፡- ትኅትና፣ ይቅርታን የማግኘት ዋስትና፤ መንፈሳዊ ምክር፣ ራስን ከመውቀስ ነፃ መውጣት እና ኃጢአትን በሚመለከት ቀርጥ ፈቃድ ማድረግ ወ.ዘ.ተ. ናቸው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥም ለሐዋርያቱ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን ሰጥቷቸዋል፡፡ የሰው ልጆች እስከ መጨረሻው በኃጢአት ይወድቃሉና ይህ የሐዋርያት ሥልጣን ለዘለቄታው ለሐዋርያት ተተኪዎችም የተሰጠ ነው፡፡ የጥንት ክርስቲያኖች ይህ የሐዋርያት ሥልጣን ከእነርሱ በኋላ ለተተኩት አገልጋዮችም የተሰጠ እንደሆነ ምሥክሮች ሆነው ይህንኑ ትምህርት ለእኛም ደግሞ አስተላልፈውልናል።

 

15 February 2024, 14:58