በዲሞክራሳዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኮልዌዚ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው በሻባራ የባህላዊ ማዕድን ማውጫ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች አጠቃላይ እይታ በዲሞክራሳዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኮልዌዚ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው በሻባራ የባህላዊ ማዕድን ማውጫ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች አጠቃላይ እይታ  (AFP or licensors)

የአፍሪካ ብጹአን ጳጳሳት ‘በአፍሪካ የማዕድንና የተፈጥሮ ሀብት ዘረፋ ይቁም’ አሉ

የአፍሪካ እና ማዳጋስካር ጳጳሳት ጉባኤ ሲምፖዚየም (SECAM) ከቫቲካን የተቀናጀ የሰው ልጅ ልማት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ትምህርታዊ ጉባኤ የውጭ ማዕድንና የተፈጥሮ ሀብት ብዝበዛ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ በሚነሱ ግጭቶች ጋር ያለውን ግንኙነት አጉልቶ አሳይቷል።

  አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በየአፍሪካ እና ማዳጋስካር ጳጳሳት ጉባኤ ሲምፖዚየም (ሴካም) በተጠራው ትምህርታዊ ጉባኤ ላይ የተሳተፉት ተናጋሪዎች በአፍሪካ በሚካሄደው የተፈጥሮ ሃብት ብዝበዛ እና በአህጉሯ በሚነሱ ግጭቶች መካከል ያለውን ጥብቅ ግንኙነት በማሳየት፥ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በአፍሪካ የሚካሄደውን የማዕድን እና የተፈጥሮ ሃብት ዘረፋ እንዲያስቆም አሳስበዋል።

በጋና ዋና ከተማ አክራ የተካሄደው ትምህርታዊ ጉባኤ

በጋና ዋና ከተማ አክራ ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በተካሄደው ስብሰባ “በአፍሪካ ውስጥ ያሉ ግጭቶች በተፈጥሮ እና ማዕድን ሃብቶች ብዝበዛ አንፃር ሲታዩ” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዓለም አቀፍ የንግድ ተቋማት እና የውጭ ሃይሎች እየደረሰ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት ዘረፋ እንዲቆም ጠይቀዋል።

በትምህርታዊ ጉባኤው ላይ የተሳተፉት ጉባኤተኞች እንደተናገሩት የሀብት ብዝበዛው በአፍሪካውያን ላይ ግጭቶችን እና መፈናቀሎችን ጨምሮ ከፍተኛ ስቃይ እያስከተለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ጉባኤው የተዘጋጀው የቫቲካን የተቀናጀ የሰው ልጅ ልማት ጽ/ቤት ከአሜሪካ ካቶሊካዊ የእርዳታ አገልግሎት እና መቀመጫውን በጀርመን ያደረገው 'ሚሴሬኦር ፋውንዴሽን' ጨምሮ ከበርካታ የካቶሊክ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ነው።

ከአፍሪካ ላይ እጃችሁን አንሱ!

ተሳታፊዎቹ ከተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት የመጡ ብጹአን ጳጳሳት፣ ካህናት እና የካቶሊክ ምእመናንን እንዲሁም በስብሰባ ላይ እንዲሳተፉ የተጋበዙ ሰዎችን ያካተተ ሲሆን፥ በውይይቱም በርካታ ጠቃሚ ርዕሰ ጉዳዮችን ተዳሰዋል። ከእነዚህም መካከል ለአብነት በአፍሪካ የማዕድን እና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች ብዝበዛ፣ ሥነ-መለኮታዊ ነጸብራቆች፣ የሕግ ማዕቀፎች እና ደንቦች፣ በጉዳዩ ላይ ቤተክርስቲያኗ ስላላት ቁርጠኝነት፣ የተሟጋችነት ተነሳሽነቶች፣ እንዲሁም ከእነዚህ ሁኔታዎች ጋር ተያይዘው የሚመጡ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ያለመ የወደፊት ጥረቶች እና ስትራቴጂዎች፣ በተለይም ግጭቶች እና ከተፈጥሮ ሃብቶች ብዝበዛ የመነጩ ጉዳቶቻቸው ላይ ተወያይተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በ2015 ዓ.ም. ወደ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉዟቸው ወቅት በኪንሻሳ ለኮንጐ ባለስልጣናት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ላይ የተናገሩትን ትንቢታዊ ቃል የጉባኤው ተናጋሪዎች በአንድ ድምፅ አስተጋብተዋል።

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በወቅቱ ባሰሙት በስሜት በተሞላ ተማጽኖአቸው፣ “ከአፍሪካ እጃችሁን አውጡ! አፍሪካን መበዝበዝ አቁሙ፤ የምትገፈፍ ወይም የምትዘረፍ የማዕድን ስፍራ አይደለችም፥ አፍሪካ የራሷ እጣ ፈንታ ዋና ተዋናይ ትሁን!” ሲሉ ተማጽነዋል።

የኪንሻሳው የሴካም ፕሬዝዳንት ብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ባደረጉት ወሳኝ የሆነ ንግግር የአፍሪካ ሀብት ለልማቷ የበኩሉን አስተዋፅዖ እንደሚያበርክት፣ አብዛኛው ህዝቦቿን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ፣ ድህነትን ማቃለል እንደሚችል እና ሰላም እንደሚያሰፍን ማረጋገጥ አለብን በማለት ደጋግመው አሳስበዋል።

በነዳጅ፣ በጋዝ፣ በማዕድን እና በተፈጥሮ ሃብት በሚደረጉ ከፍተኛ የውጭ ኢንቨስትመንቶች የአካባቢውን ህዝብ በበቂ ሁኔታ ተጠቃሚ ማድረግ ያልተቻለበትን አወዛጋቢ ጉዳይንም አንስተዋል።

ለአፍሪካ ህዝብ የተዋሃደ ስነ-ምህዳርን ማሳደግ እና መደገፍ

ኮንጎዋዊው ብጹእ ካርዲናል በማከልም በቅርቡ ለሩዋንዳ ወዳጅ በመሆን በምስራቅ ዲሞክራሳዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚገኘውን የማዕድን ሃብቶች በአውሮፓ ህብረት ተባባሪነት “ያለ ይሉኝታ የተደረገውን ዝርፊያ” አውግዘዋል።

ብፁዕ ካርዲናል አምቦንጎ በካቶሊክ ማሕበራዊ አስተምህሮ ውስጥ የተጠቀሱትን በተለይም ከማዕድን አውጪ ኢንዱስትሪዎች ጋር በተገናኘ በአፍሪካ ውስጥ ያለች ቤተክርስቲያን የሃዋሪያዊ አቀራረብን ወደ ተሳለጠ ሥነ-ምህዳር እና ሥነ-ምህዳራዊ አጠቃቀም ማምጣት አስፈላጊ መሆኑን አበክረው አሳስበዋል።

ከማእድንና ተፈጥሮ ሀብት ብዝበዛ ጋር የተያያዙ ቁልፍ ተግዳሮቶችን እና የቤተክርስቲያኗን ወቅታዊ ምላሾች በመለየት ተሳታፊዎቹ ለአፍሪካ ህዝቦች የተሻለ መፃኢ ዕድል ለመፍጠር ያተኮሩ ተግባራዊ ሀሳቦችን አቅርበዋል።

ከእነዚህም መካከል በእያንዳንዱ አገራት ውስጥ ያሉ የተለዩ ጉዳዮችን ለማጉላት እና የተገለሉ ወገኖችን ድምጽ ለማሰማት በአፍሪካ አህጉራዊ የጸሎት እና የአብሮነት ቀን እንዲመሰረት መሟገት የሚሉት ይገኙበታል።

በአፍሪካ የግጭት መንስኤዎችን መፍታት

በተጨማሪም ትምህርታዊ ጉባኤው የተጠናከረ የስነ-ምህዳር ትምህርት እንዲሁም የህግ እና የሚዲያ ባለሙያዎች የተፈጥሮ ሃብት ብዝበዛን እና የጥብቅና ጥረቶችን በመከታተል ላይ እንዲሳተፉ አሳስቧል።

የትምህርታዊ ጉባኤው ቁልፍ አጋር እና ተሳታፊ የሆነው የቅድስት መንበር የተቀናጀ የሰው ልጅ ልማት ጽ/ቤት በበኩሉ በአፍሪካ የምትገኘ ቤተክርስትያን ከፍተኛ ስቃይ የሚያስከትሉ እንደ ግጭቶች እና የህዝብ መፈናቀል ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ያላትን ቁርጠኝነት እንድታጠናክር አሳስቧል።
 

14 March 2024, 14:56