2021.02.18 Gesù nel deserto - albanese

ክርስቲያኖች ተጋድሎ ማድረግ ይኖርባቸዋል!

ስለ ተጋድሎ በቀድሞ ባሕታውያን ገድል የሚከተለው ምሳሌ ተጽፎ ይገኛል፣ በአንድ በረሃ አንድ ባሕታዊ ነበር፣ ጎጆው ከወንዙ በጣም ሩቅ ስለነበር ውኃ ለመቅዳት ቁልቁል ሲወርድና ዳገት ሲወጣ ብርቱ ድካም ይሰማው ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ውኃ ተሸክሞ ሲመለስ ድካም ስልተሰማው «ከእግዲህ ወዲህ በወንዙ አጠገብ ሄጄ እቀመጣለሁ ብሎ አሰበ። በእንደዚህ ያለ ሐሳብ ተውጦ የውሃ መቅጃውን ተሸክሞ ሲሄድ ሳለ በጀርባው አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት! የሚል ድምጽ ሰማ። በበረሃ እንዲያውም በዚያን ጊዜ የሰው ድምጽ በመስማቱ ተገረመና ወደ ኋላ ዞር አለ፣ ነገር ግን አንድ ሰው እንኳ አላየም። ግራ ቀኝ ተመለከተና መንገዱን ቀጠለ። በድጋሚ ያ ድምጽ እንደገና ተሰማ እርሱም እንደ በፊቱ ዞር ብሎ ቢያይ አሁንም ምንም የለም። አንድም ሰው እንደሌለ አረጋገጠ መንገዱን ቀጠለ። በሦስተኛውና በመጨረሻው ጊዜ «አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት! የሚል ድምጽ ሰምቶ ወደ ኋላ ተመልሶ ቢመለከት አንድ የማያንጸባርቅ ጐረምሳ አየ። እርሱም «አይዞህ! እኔ የአንተ ጠባቂ መልአክ ነኝ እርምጃህን እቆጥራለሁ ይህ ሁሉ ድካምህ እንኳ ያለደመወዝ ወይም ያለዋጋ እንዳይቀይር ብዬ ነው የምቆጥረው በማለት ተናገረ።

ያ ባሕታዊ በዚህ ተደስቶ «እኔ እብድ አይደለሁም ይህንን ሽልማት የማጣው በማለት በተጋድሎ ብዙ ሽልማት ለማግኘት ብሎ ተመልሶ ከወንዝ ሩቅ ወደ ነበረችው ጎጆው ሄደ። እንግዲህ ተጋድሎ ማድረግ ሲታክተን ይህንን አብነት እናስታውስ።

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት ጠለቅ ብለን ብንመረምር ሕይወቱ በሙሉ ተጋድሎ ነበር። በተጋድሎ ውስጥ ተወለደ፣ በተጋድሎ መካከል ኖረ፣ በብርቱ ተጋድሎ ሞተ። ኢየሱስን ተመልክተን ተጋድሎ ለማድረግ እንበርታ፣ በሕይወታችን ተጋድሎ ማድረግ ያስፈልገናል። መላአኩ ሩፋኤል ለጦቢት «ጸሎት ከጾም ጋር መልካም ነው” (ጦቢ.12፣8) እያለ መከረው። ተጋድሎ ከሰማይ ምሕረትና ጸጋ ያወርድልናል። የመንፈስ ቅዝቃዜንና ቸልተኛነት፣ መጥፎ ዝንባሌን አስወግዶ ብርታትንና ትጋትን ይሰጠናል፣ መንፈሳዊያን ያደርገናል፣ ቅዱሳን እንድንሆን ይረዳናል። ቅዱሳን በሙሉ በተጋድሎ ሕይወታቸውን አሳልፈዋል። የተጋድሎ መንፈስ ካለን አእምሮአችን፣ ፈቃዳችንን፣ ሕዋሳቶቻችንን በጥንቃቄ ሰብስበን ለመያዝ እንችላለን፣ ፈተናዎችንም እናሸንፋለን።                  

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገዛ ራሱ ለደቀ መዛሙርቱ «የዚህ ዓይነት ጋኔን ግን ካለ ጸሎትና ካለጾም በስተቀር አይወጣም አላቸው” (ማቴ 17፣21)፣ በታጋድሎ ለሥጋችን መንፈሳዊ መወዳደሪያ እናበጅለታለን፣ ለማሸነፍም እንችላለን። ነፍሳችን እንዳትጐዳ፣ ሥጋችንም ከእርስዋ ሥር እንዲሆንና፣ ከእርስዋ ጋር ተባብሮ ስለ መንግሥተ ሰማያት እንዲሠራ እናደርጋለን። ሥጋችን ወደሚፈልገው እንዳይሄድና ፍላጐቴ ብቻ እንዳይፈጽም መግታት እንችላለን። መልካም ሥራ ካልሆነ እንዳይሠራ እንከለክለዋለን።ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ስለተጋድሎ ሥጋችንን መቆጣጠር እንደሚያስፈልግ ሲያስተምር «ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ እኔ ራሴ ውድቅ ሆኜ እንዳልቀር፣ ሰውነቴን እየጐሰምሁ እንዲገዛልኝ አደርገዋለሁ” (1ኛ ቆሮ. 9፣27) ይላል። ያለ ተጋድሎ ደህንነት የለም ተጋድሎ ሳናደርግ መንግስተ ሰማያትን ለመውረስ አንችልም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ንጹህ ሳለ የተጋድሎ ግዴታም ሳይኖረው በተጋድሎ ካለፈ እኛ የኃጢአት ዕዳ ያለብን እንዴት ብለን ከተጋድሎ ግዴታ ማምለጥ እንፈልጋለን? የማይቻል ሞኝነት ነው። በዚህ ዓለም ተጋድሎ ከጠላን በሚመጣው ዓለም የባሰ መከራና ስቃይ ይጠብቀናል። ስለዚህ የእኔ ነው ይጠቅመኛል ብለን እንያዘው አንጥላው፣ በዛብን፣ በረታብን ብለን አናጉረምርም፣ በሚመጣው ዓለም እንዳናዝንና እንዳንጸጸት እንጠንቀቅ።

አንድ መነኩሴ ተጋድሎን ይወድ ነበር፣ ባልንጀሮቹ ግን «በዛ፣ ቀንሰው እያሉ ቢናገሩት «ወንድሞቼ! በሰማይ ቅዱሳን ሊያዝኑ የሚችሉበት ነገር ቢገኝ በምድር ሳሉ በይበልጥ ተጋድሎ ማድረግ ስላልወደዱ ብቻ ሊሆን እንደሚችል እወቁ፣ ምክንያቱም ተጋድሎ በምድር በተደረገ መጠን በዚያ ልክ በሰማይ ክብር ነውና እያለ ይመልስላቸው ነበር። በዚህ የሚያጽናና መንፈሳዊ አብነት ተንቀሳቅሰን ተጋድሎን ለመውደድና ለማዘውተር ጥረት እናድርግ።

               

11 March 2024, 13:19