የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት  (AFP or licensors)

ጋዛ ውስጥ የሚሞቱ ሕጻናትን ከማየት መራቅ የማይቻል መሆኑ ተገለጸ

የቅድስት አገር መጋቢ አባ ኢብራሂም ፋልታስ “SIR” ከተሰኘ የቤተ ክርስቲያን የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ በጋዛ የሕጻናትን እና የእናቶችን ሕይወት ለማዳን አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በረሃብ እና በፍርሃት ውስጥ የሚገኙ የጋዛ ሕጻናትን ከመመልከት ዓይንን እና ልብን መዝጋት ፍጹም እንደማይችሉ የገለጹት አባ ፋልታስ፥ በጋዛ ውስጥ 60,000 ነፍሰ ጡር እናቶች በረሃብ እና በተመጣጠነ ምግብ እጦት ሲሰቃዩ እያየን ቸላ ልንላቸው አንችልም ብለዋል።

አባ ኢብራሂም ፋልታስ ይህን አዲስ ተማጽኖ ያቀረቡት፥ ቅዳሜ የካቲት 30/2016 ዓ. ም. ከጣሊያን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያ የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደሆነ ታውቋል።


ግብጻዊው ፍራንችስካዊ ካኅን አባ ኢብራሂም ፋልታስ በቅርቡ ከጣሊያን ባለስልጣናት ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት ሕጻናትን ከጋዛ ሰርጥ ሮም ውስጥ ወደሚገኝ “ባምቢኖ ጄሱ” የህፃናት ሆስፒታል በማምጣት ጣሊያን ውስጥ እንደሚገኙ ሲታወቅ፥ የመጀመሪያው ቡድን ጥር 20/2016 ዓ. ም. ወደ ሮም መድረሱ ይታወሳል።

አባ ኢብራሂም ፋልታስ በቃለ ምልልሳቸው፥ እንደማንኛውም ጦርነት በእስራኤል እና በሃማስ መካከል በቀጠለው የትጥቅ ግጭት የመጀመሪያ ሰለባ የሆኑት ንጹሃን ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውን አስታውሰዋል።

ወላጅ አልባ የሆኑ ልጆች እና ልጆቻቸውን እያጡ እናቶች

በሐማስ ታጣቂዎች እና በእስራኤል ጦር ሠራዊት መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ከመስከረም 26/2016 ዓ. ም. ጀምሮ ከ9,000 በላይ የፍልስጤም ሴቶች እንደተገደሉ፥ ብዙ ህጻናት ወላጅ አልባ እንደሆኑ እና በርካታ እናቶችም ልጆቻቸውን እንዳጡ የገለጹት አባ ኢብራሂም፥ጋዛ ውስጥ ምግብ የሌላቸው ህጻናት በረሃብ ሊሞቱ እንደሚችሉ እና ሴቶች በዕለቱ በሚወድቁ ቦምቦች ሕይወታቸው አደጋ ውስጥ እንደሚገኝ ገልጸው፥ "የሰው ልጅ ቀዳሚ ፍላጎቶች ካልተሟሉለት ገደል ውስጥ ይወድቃል" ሲሉ አስረድተዋል።

ልጆች በረሃብ ሊሞቱ ይችላሉ

እነዚህን ልጆች ከሞት ለማትርፍ ፈጣን ምላሽ ሊስጣቸው እንደሚያስፈልግ አባ ኢብራሂም ተናግረው፥ ሕጻናቱ የዓለም ኃያላን የምግብ ዕርዳታን እስኪልኩ ድረስ ረሃብን ታገሱ ማለት አንችልም ብለዋል።

“ከፍርስራሽ ስር ሆኖ ከጎኑ የሞቱ ቤተሰቦችን የሚመለከት ሰው ጉዳት ከአእምሮው መሰረዝ አንችልም” ያሉት አባ ኢብራሂም፥ ልጇን በሞት ያጣችውን እናት ለማጽናናት የሚሞክር የጥቂት ዓመት ሕጻንን እንዴት ማጽናናት እንችላለን?” ሲሉ ጠይቀዋል።

አባ ኢብራሂም ፋልታስ በቃለ ምልልሳቸው ማጠቃለያ፥ “ግብዝነትን የሚያሸንፍ የእውነት ብርሃን የሰዎችን ሕሊና እንዲነካ እንጸልያለን፤ በጦርነት የሚሰቃዩትን ለመከላከል፣ እውነትን፣ ፍትህን እና ሰላምን ለመጠየቅ ድምጽ ለሌላቸው ሰዎች ድምጽ ለመሆን እንሞክራለን” ብለዋል።

 

11 March 2024, 16:14