ሄይቲ በአመፁ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃለች ሄይቲ በአመፁ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃለች 

የሄይቲ ፍትህ እና ሰላም ዳይሬክተር በሃገሪቷ ውስጥ የወሮበሎች ጥቃት መባባሱን ገለጹ

የሄይቲ ጳጳሳት የፍትህ እና የሰላም ኮሚሽን ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ጆሴሊን ኮላስ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ወደ 4,000 የሚጠጉ እስረኞች በጅምላ ከእስር ቤት ያመለጡበትን ሁኔታ ተከትሎ በሄይቲ ስላለው አሳሳቢ የጸጥታ ሁኔታ ተናግረዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የብሔራዊ ፍትህና ሰላም ኮሚሽን ዳይሬክተር የሆንት ወ/ሮ ጆሴሊን እንደተናገሩት በሄይቲ የታጣቂ ወሮበሎች ጥቃት አዲስ እንዳልሆነ፥ ነገር ግን ዛሬ ላይ የመንግስት እና የቤተክርስቲያን ተቋማት እንኳን ሳይቀሩ ማንንም በማይምር መልኩ የማይታለፍ ደረጃ ላይ ደርሷል በማለት የጉዳዩን አሳሳቢነት ገልጸዋል።

ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ የታጠቁ ወሮበሎች በሄይቲ ዋና ከተማ ፖርት ኦው ፕሪንስ፣ ክሮክስ ዴስ ቡኬትስ መንደር አቅራቢያ የሚገኙ ሁለት ዋና ዋና እስር ቤቶችን ወረው 12 ሰዎች ከገደሉ እና 4,000 የሚሆኑ እስረኞችን ካስመለጡ በኋላ፥ ለ72 ሰዓታት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአገሪቱ ታውጇል።

ይሄንንም ተከትሎ ዳይሬክተሩ ከቫቲካን ዜና ባልደረባ ዣን ቤኖይት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት ከታጣቂ ወሮበሎቹ ጋር የተያያዘ ጥቃት ከዚህ ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ መጨመሩን በመግለጽ፥ የፀጥታው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል በማለት አረጋግጠዋል።

የተባበሩት መንግስታት እ.አ.አ. በ2023 በሄይቲ 5,000 የሚጠጉ ሰዎች በወሮበሎች ጥቃት ተገድለዋል ማለቱ
እ.አ.አ. በ2023 ከታጣቂ ወሮበሎቹ ጋር በተፈጠረው ግጭት ወደ 5,000 የሚጠጉ ሰዎች እንደሞቱ እና 300,000 የሚሆኑት ደግሞ ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግምቱን አስቀምጧል።

በዚህ ዓመት በጥር ወር ብቻ ከ100 በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፥ የካቲት ወር ላይ ቁጥሩ ከፍ በማለት በአብዛኛው በጥይት የተመቱ 176 ሰዎች መሞታቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።

“አገሪቱ ለዓመታት በብጥብጥ ውስጥ ነበረች፥ አሁን ግን የታጠቁ ቡድኖች ተቋማትን ጭምር እያጠቁ ነው፥ አሁን በጣም በዝቷል፥ በቃ ሊባሉ ይገባል” ብለዋል ወይዘሮ ጆሴሊን።

ቤተክርስቲያን የወረበሎቹ ኢላማ ሆናለች

በመሆኑም የተለየዩ አቢያተ ክርስቲያናት በታጣቂ ቡድኖቹ በብዛት እየተጠቁ እንደሆነ እና የአጥቢያ ቤተክርስቲያናትን በማጥቃት ካህናትን እና ገዳማዊያትን በማገት ላይ እንደሆኑም ተጠቅሷል።

የፍትህ እና የሰላም ዳይሬክተሯ ይሄንን በማስመልከት እንደተናገሩት የካቲት 15 በፖርት ኦ-ፕሪንስ ታግተው የተወሰዱ ስድስቱ የቅዱስ ልብ ወንድሞች ሁኔታ እስካሁን ምንም አዲስ ዜና የለም ካሉ በኋላ በዕለቱ አብረዋቸው ታፍነው የተወሰዱት ካህን ግን እንደተለቀቁ ተናግረዋል።

“ታጣቂ ወረበሎቹ ሁሉንም ሰው ያጠቃሉ። ሁሉንም ተቋማት ማለት ይቻላል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያጠቃሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ቤተክርስቲያን ኢላማ ሆናለች”

የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች በግጭቱ ምክንያት ተዘግተዋል

ተጠናክሮ እየቀጠለ ያለው የጸጥታ ችግር የፍትህ እና የሰላም ኮሚሽን መስሪያ ቤትን ጨምሮ የቤተክርስቲያኒቱ ተቋማት አሰራራቸውን እንዲቀይሩ አስገድዷቸዋል። ዳይሬክተሯ ይሄንን በማስመልከት ለጋዜጠኛው እንደተናገሩት “መታገትን በመፍራት በጣም አልፎ አልፎ ወደ ቢሮአችን ከምንሄደው በስተቀር ቤት ውስጥ ሆነን ለመስራት ተገደናል፥ የእኛ ቢሮ ብቻ ሳይሆን ብዙ የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ለመዘጋት ተገድደዋል” በማለት አስረድተዋል።

የሄይቲ ፍትህ እና ሰላም ዳይሬክተር በቃለ ምልልሱ ላይ ቀውሱን ለመቅረፍ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ቤተክርስቲያን ለባለስልጣናቱ ተደጋጋሚ ጥሪ ብታቀርብም ምንም እርምጃ ባለመወሰዱ ማዘናቸውን ገልጸዋል።

በሄይቲ የሚገኙ የፖለቲካ መሪዎች በስልጣን ላይ ለመቆየት ሲሉ የወረበሎቹን እንቅስቃሴ እየተጠቀሙ እንደሆነ በመጠቆም፥ “ምንም ነገር አያደርጉም፤ ስለዚህ ብጥብጡ እንዲቀጥል ፈቅደዋል” ብለዋል።

በማከልም "የሄይቲ ቀውስ ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው፥ እናም በስልጣን ላይ ያሉ ባለስልጣናት በወንበራቸው ላይ ለመቆየት የታጠቁ ቡድኖችን እየተጠቀሙ ነው የሚል ግምት አለን” ብለዋል።

ጥር 19 ቀን 2016 ዓ.ም. በደረሰው የቦንብ ፍንዳታ የቆሰሉትን የሄይቲ ጳጳሳት ጉባኤ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑትን ብጹእ አቡነ ፒየር አንድሬ ዱማስ በማስታወስ፥ ቤተክርስቲያን የወሮበሎች ቀጥተኛ ኢላማ ሆናለች በማለት አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ጊዜ በፍሎሪዳ ግዛት ስር በምትገኘው ማያሚ ከተማ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ በማገገም ላይ የሚገኙት ብጹእ አቡነ ዱማስ የሄይቲ ባለስልጣናት ለችግሩ መፍትሄ ባለማግኘታቸው ከፍተኛ ትችት ሲያቀርቡ እንደነበር ይታወሳል።

በፖርት ኦ-ፕሪንስ የሚገኘው የካቶሊክ ሆስፒታል ጥቃት ተሰነዘረበት

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሁለቱ ማረሚያ ቤቶች ላይ ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ ወደ 4,000 የሚጠጉ እስረኞች በማምለጣቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና ለ72 ሰአታት የሚቆይ የሰዓት እላፊ አዋጅ ቢታወጅም ሁከቱ በሀገሪቱ ተቀጣጥሎ ቀጥሏል።

ታጣቂ ወረበሎቹ አሁን ላይ ሆስፒታሎችን ጨምሮ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን፣ በርካታ የህዝብ ሕንፃዎችን እያጠቁ እንደሆነ ተነግሯል። ከነዚህም መካከል በፖርት ኦ-ፕሪንስ የሚገኘው “ቅዱስ ፍራንቺስኮ ደ ሳሌስ” የሚባለው የካቶሊክ ሆስፒታል እንደሆነ የአካባቢው የቤተ ክርስቲያን ምንጭ ሁኔታውን “እጅግ አስፈሪ” በማለት ‘ፊደስ ኤጀንሲ’ ለተባለ የዜና ማሰራጫ ዘግቧል።

የሄይቲ ጳጳሳት በሃገሪቷ እየታየ ያለው የጸጥታ ሁኔታ እንዲሻሻል ደጋግመው የተማጸኑ ሲሆን፥ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ የሄይቲ ነዋሪዎች ለአመፅ እጅ እንዳይሰጡ እና ለሃገሪቷ ሰላም ሲሉ ከጠቅላይ ሚኒስትር አሪኤል ሄንሪ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

እ.አ.አ. በ2021 ከፕሬዚዳንት ጆቨኔል ሞይስ ግድያ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ሄንሪ፥ በዚህ ዓመት፣ ባለፉት ሳምንታት ውስጥ መካሄድ የነበረበትን ምርጫ ለሌላ ጊዜ በማስተላለፋቸው ከፍተኛ ትችት ሲሰነዘርባቸው ቆይቷል።

በሄይቲ የመጨረሻው ምርጫ የተካሄደው እ.አ.አ በ2016 ሲሆን፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የካቲት ወር መጀመሪያ ላይ እንደገለጹት ምርጫው አሁን ያለው ሁኔታ ከተረጋጋ በኋላ በሚቀጥለው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ እንደሚያካሂድ አስታውቀዋል።
 

06 March 2024, 13:54