የሜክሲኮ የምርጫ ውድድር የሜክሲኮ የምርጫ ውድድር   (AFP or licensors)

የሜክሲኮ ጳጳሳት በአገሪቱ በሚካሄደው ምርጫ ወንጀለኞች ጣልቃ እንዳይገቡ አስጠነቀቁ

በሜክሲኮ ግንቦት 25/2016 ዓ. ም. ሊካሄድ የታቀደው ብሔራዊ ምርጫ ሰላማዊ እንዲሆን የተመኘው የሜክሲኮ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ባስተላለፈው መልዕክት፥ 99 ሚሊዮን ሜክሲካውያን 20,000 ተወካዮችን ለመምረጥ ድምጽ በሚሰጡበት ምርጫ ላይ ወንጀል ያለበት ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር አስጠንቅቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እሑድ ግንቦት 25/2016 ዓ. ም. በላቲን አሜሪካ ሜክሲኮ የሚካሄደው ፌደራላዊ ምርጫ በመራጮች ተሳትፎ እና በተመራጮች ብዛት ታሪካዊ ሊሆን ይችላል ተብሏል።

ሜክሲካውያን አዲስ ፕሬዝዳንት እና 628 አባላት የሚገኙበት የሁለቱም የኮንግረስ ምክር ቤቶች አባላትን እንዲሁም 9ኙን ከ32 የክልል መሪዎች እና ሌሎች የአካባቢ ባለስልጣናት፣ በድምሩ 20,000 ተወካዮችን ይመርጣሉ። ስድስት ዓመታት የሥልጣን ጊዜያቸውን የፈጸሙትን የወቅቱን ፕሬዚደንት አንድሬስ ማኑዌል ሎፔዝ ኦብራዶርን ለመተካት ሁለት ሴቶች ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚወዳደሩ ታውቋል።

የሜክሲኮ ሲቲ ተሰናባች ከንቲባ ክላውዲያ ሺንባም የወቅቱ የግራ ክንፍ ፕሬዝደንት ምትክ እና በምርጫው ወቅት ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያገኙት የቀኝ ክንፍ ሴናተር ጋልቬዝ በሀገሪቱ ታይቶ በማይታወቅ ሁከት እና ብጥብጥ መካከል እንደሚጋጠሙ ታውቋል። ከምርጫ ዘመቻው አስቀድሞ ዓርብ መጋቢት 22/2016 ዓ. ም. በአገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል በወታደራዊ ጥበቃ ላይ በደረሰ የቦምብ ጥቃት አራት ወታደሮች መሞታቸው ታውቋል።

120 ጳጳሳት የሚገኙበት የሜክሲኮ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሁከት በምርጫው ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር አስጠንቅቋል። ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ከተደራጁ ወንጀሎች ጋር የተደባለቀ ከሆነ ፍጹም ተቀባይነት የሌለውም ሲልም ገልጾ፥ ጉባኤው በማከልም “ይህ ክስተት በማንኛውም አቅም መወገድ ያለበት እጅግ አሳዛኝ የሙስና ምልክት ነው” በማለት አስረድቷል።

ከተደራጁ ወንጀለኞች ጋር መስማማት አይገባም

የሜክሲኮ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ እሑድ የካቲት 24/2016 ዓ. ም. ለመላው የሜክሲኮ ሕዝብ ባስተላለፈው መልዕክቱ፥ “የተደራጁ ወንጀለኞች እና የወንጀል ቡድኖች ሰላማዊ ምርጫዎችን እንደሚካሂዱ ለማስመሰል በመካከላቸው ባደረጉት የሐሰት ስምምነት ማዘኑን ገልጿል።

በሜክሲኮ በዓመት ከ 30,000 ግድያዎች በላይ የሚመዘገብ ሲሆን አብዛኞቹ ከአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ጋር የተቆራኙ እንደሆነ ተነግሯል። 120 ጳጳሳት የሚገኙበት የሜክሲኮ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሰላማዊ የምርጫ ቅስቀሳዎች እንዲካሄዱ በማሳሰብ፥ ዜጎች ግዴለሽነትን፣ ችላ ማለትን እና ድምጽ አለመስጠትን እንዲያስወግዱ ጠይቋል።

"አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ጥሩ አይደለም” ያለው የጳጳሳቱ ጉባኤ፥ በግልጽ እንደሚታየው ከተወሰነ ጊዜ ጀምሮ በፀጥታው፣ በማኅበራዊ እኩልነት፣ በኢኮኖሚ ዕድገት፣ መደበኛ የሥራ ዕድል ማመቻቸትን ጨምሮ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ገልጾ፥ የትምህርት እና የጤና ጥራት፣ ስደት፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮችን ጠቅሷል። ጳጳሳቱ በመልዕክታቸው፥ “ይህን ጠቃሚ የፖለቲካ ሂደት በሰላም ማካሄድ እንዲቻል በእውነት እና በፍትህ ተደግፎ ተገቢውን ምህዳር በጋራ ለመገንባት እንፈልጋለን” ሲሉ ተናግረዋል።

ከሜክሲኮ ዲሞክራሲ ጋር የሚስማማ የጨዋነት ምሳሌ

በዚህ የምርጫ ሂደት የሜክሲኮ ታላቅነት በጓዳሉፔ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንዲባረክ፣ ዘንድሮ እሑድ ግንቦት 25/2016 ዓ. ም. ሊካሄድ በታቀደው ብሔራዊ የምርጫ ሂደት የበኩላችንን አስተዋጽዖ እናበርክት ሲሉ ጳጳሳቱ አሳስበዋል። በወንጀለኞች ጥቃት ዲሞክራሲያዊ መረጋጋት አደጋ ውስጥ እንደሚወድቅ እንዲሁም የዜጎችን ነፃነት የሚነኩ አንዳንድ አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ብጹዓን ጳጳሳቱ አምነዋል።

የካቲት 6/2016 ዓ. ም. የደቡብ ምዕራብ ሜክሲኮ ግዛት በሆነች ጌሬሮ ውስጥ አራት ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ከወንጀል ቡድኖች መሪዎች ጋር የሰላም ስምምነት ለመደራደር ተገናኝተው እንደነበር ታውቋል። የሽምግልና ሃሳብ የአገሪቱ ፕሬዝደንት በሆኑት በአቶ አንድሬስ ማኑዌል ሎፔዝ ኦብራዶር የተደገፈ ቢሆንም በወንጀል ድርጅቶች ውድቅ ተደርጓል።

የሜክሲኮ ካቶሊክ ጳጳሳት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ 2024 የምርጫ ሂደት፥ "ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ የሜክሲኮ ሕዝብ ከገነባው እና ካጠናቀቀው የዴሞክራሲ ባህል ጋር የሚጣጣም የሥልጣኔ ምሳሌ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

የምርጫ ተቋማት ኃላፊዎች፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የፌዴሬሽኑ የፍትሐ-ብሔር፣ የምርጫ ልዩ ዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች፥ ምርጫው በህጋዊ መንገድ እንዲካሄድ እና ሊከሰቱ የሚችሉ ጉድለቶች በጊዜ እንዲታረሙ፥ ከስሥ-ምግባር እና ሙያዊ ብቃት ጋር ገለልተኛ እና ፍትሃዊ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ጳጳሳቱ ገልጸዋል።

በምርጫ ወቅት የሚነሳ ብጥብጥ ጨምሯል

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ከምርጫው ጋር በተያያዘ በእጩዎች፣ በፖለቲከኞች እና ዘመዶቻቸው፣ በጋዜጠኞች እና ሌሎች ዜጎች ላይ እየጨመረ የመጣው ጥቃት እና ግድያ እንዲወገድ በማለት ጳጳሳቱ አሳስበዋል።

አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ተቋም ከምርጫ ሂደት አጥኚ ድርጅት ያገኘውን ዘገባ ጠቅሶ እንደዘገበው፥ ከግንቦት 27/2015 እስከ ጥር 29/2016 ዓ. ም. ባሉት ጊዜያት መካከል 16 አዲስ እጩዎችን ጨምሮ 33 የክልል የፖለቲካ መሪዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

የሜክሲኮ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በመልዕክታቸው ማጠቃለያ ላይ፥ የምርጫ ቅስቀሳዎች ነፃ፣ በመረጃ የተደገፉ እና የድምጽ ማጭበርበር የሌሉበት፣ ከመንግሥት ባለስልጣናት ሆነ ከማንኛውም ሕገወጥ ድርጊት እና ጣልቃ ገብነት የጸዳ እንዲሆን አሳስበዋል።

 

 

06 March 2024, 15:32