የኖርዌይ ብጹዓን ጳጳሳት በውርጃ ሕግ ላይ መንግሥት ያቀረበውን የማሻሻያ ሃሳብ ውድቅ አደረጉ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ሕግ ከተቀየረ ለበጎ መሆን አለበት" ያሉት በኖርዌይ የትሮንዳሂም ጳጳስ አቡነ ኤሪክ ቫርደን፥ የኦስሎው ከተማ ጳጳስ ከሆኑት ከአቡነ በርንት ኤድቪግ ጋር በመሆን፥ የኖርዌይ መንግሥት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1975 ጀምሮ በሀገሪቱ ውስጥ ሲተገበር የነበረውን የውርጃን ሕግ ለመቀየር ያቀረበውን ሃሳብ የሚቃወም ባለ ስምንት ገጽ የምላሽ መልዕክታቸውን ተፈራርመዋል።
በውርጃ ላይ የሚነሱ ጉዳዮችን እንዲያጤን በመንግሥት የተመረጠው ኮሚቴ በኖርዌይ ፅንስ ማስወረድ እንዴት እና ምን ያህል ቀላል እንደሆነ ሃሳቡን በጽሑፍ አቅርቧል።
ብጹዓን ጳጳሳቱ በምላሻቸው፥ የጽሑፉ ይዘት ከሳይንስ፣ ከፖለቲካ እና ከርዕዮተ ዓለም ጋር ወጥነት ካለመኖሩ ጋር ተዳምሮ አንባቢው ረቂቅ ሕጉ ሊጸና የማይችልበትን የአመለካከት ነጥቦች ላይ ትኩረት ለመስጠት እንደሚያስቸግረው አስገንዝበው፥ የኮሚቴው ሐሳብ ዋና ነጥብ ድምጽ መስጫ ጊዜን በስድስት ሳምንታት ማለትም እስከ 18 ሳምንት ድረስ ማራዘም እንደሆነ አስረድተዋል።
ሕይወት የሚጀምረው ከጽንስ ነው
አሁን በሥራ ያለው ሕግ መልካም አለመሆኑን አቡነ ቫርደን ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ተናግረው፥ በካቶሊክ ክርስቲያናዊ የኅብረተሰብ ጥናት አኳያ የሰው ልጅ ህይወት በፅንስ መጀመሩ መርህ እንደሆነ እና ከዕለቱም ጀምሮ ክብር ሊሰጠው እንደሚገባ አስረድተዋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ በምላሻቸው፥ አሁን ያለውን ሕግ ከአዲሱ ረቂቅ ሕግ ጋር በማዛመድ፥ በርካታ የሥነ ምግባር፣ የስነ ሕዝብ እና የፍልስፍና ለውጦችን ሊያስከትል እንደሚችል ገልጸው፥ ውርጃን በማስመልከት አዲስ ሕግ ለማውጣት የቀረበው ሃሳብ ከኖርዌይ ክርስቲያናዊ እና የሰብዓዊነት ቅርስ የራቀ ግልፅ እርምጃ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።
የሕይወት ወይም የሞት ምርጫ
ብጹዓን ጳጳሳቱ በምላሻቸው፥ አዲሱ ረቂቅ ሕግ ስለ ሕጻናት የሚናገር ሳይሆን ነገር ግን በአጭሩ ነፍሰ ጡር ሴቶች ፅንስን ለማስወረድ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ሕክምናን የማግኘት መብት እና ዋስትና የሚሰጣቸው በመሆኑ በአካሎቻቸው ላይ ገለልተኛ ውሳኔዎችን እንዲያደርጉ የሚያደፋፍር መሆኑን አስታውቀዋል።
በማሻሻያ ሃሳቡ ላይ የቃላት ለውጥ መኖሩን ያስተዋሉት ብጹዓን ጳጳሳቱ፥ አሁን ያለው ሕግ ሴት ልጅ በምትወልድበት ጊዜ ኅብረተሰቡ የሚኖረውን ሃላፊነት ከመናገር ይልቅ ጥያቄዎችን፣ የመብት እና የጥራት ዋስትናን የመሳሰሉ የፍጆታ ቃላትን መጠቀሙን ተናግረዋል።
የፆታ ሚና ግጭት አይደለም
የማሻሻያ ረቂቁ ከዚህ በፊት የነበረው ሕግ ጊዜ ያለፈበት እንደሆነ በመፈረጅ በሚያሳስት መልኩ የቀረበ እንደሆነ የገለጹት ብጹዓን ጳጳሳቱ፥ በተፈጥሮ ሴቶችም እንደ ወንዶች በራስ የመመራት እና በገዛ ሰውነታቸው ላይ ቁጥጥር ሊኖራቸው እንደሚገባ ተናግረው፥ “ነገር ግን ፅንስ ማስወረድ እንደ ማሻሻያው ሃሳቡ ሁሉ ከፆታዊ ሚናዎች ጋር መጋጨት የለበትም” ብለዋል።
ገና ያልተወለደ ሕጻን በኖርዌይ ሕገ መንግሥት የተጠበቀ ነው
ገና ያልተወለደ ሕፃን በኖርዌይ ሕገ መንግሥት በሕግ የተጠበቀ መሆኑን ያስታወሱት ብጹዓን ጳጳሳቱ፥ በሀገሪቱ ሕግ መሠረት ገና ያልተወለዱ ሕፃናት ውርስ የማግኘት መብት ካላቸው ሰዎች ጋር የሚመደቡ መሆናቸውን አስታውሰዋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ በማከልም ገና ያልተወለደ ሕጻን መብቶች እና ግዴታዎች በእናቶች መብት እና ግዴታ ሊዋጥ የማይችል መሆኑን አስታውሰዋል።
የማሻሻያ ሕጉ ገና ያልተወለዱ ሕፃናት ክብር ሊሰጣቸው እንደሚገባ ብያሳስብም ነገር ግን በተመሳሳይም እርግዝና የሴቷ የግል ሕይወት አካል ተደርጎ መወሰድ እንዳለበት፥ በሌላ አገላለጽ አዲሱ የማሻሻያ ሕጉ ለሕጻኑ ዕውቅናን የመስጠት መስፈርቱ በፅንሱ መፈለግ ወይም ያለመፈለግ ላይ የተመካ መሆኑን ያረጋግጣል።
የብጹዓን ጳጳሳቱ ምላሽ የመስጠት ግዴታ
በኖርዌይ የትሮንዳሂም ጳጳስ አቡነ ኤሪክ ቫርደን፥ ስለ እርግዝና ግንዛቤ መኖር ማሻሻያ ሕግን በትክክል ተረድቶ ትክክለኛ ምላሽ ለመስጠት እንደሚጠቅም ገልጸዋል። አክለውም፥ “እንደ ጳጳስ ግዴታችን ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮችን በግልፅ መናገር ነው” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው፥ ሕጉ እንደሚለው ሰዎች ሕይወት ዋጋ ያለው በመሆኑ ሊጠበቅ እንደሚገባ እና ምን ማለት እንደሆነ የመፍረድ መብት እንዳላቸው ይናገራል ብለዋል።