ክርስቲያኖች በፓኪስታን የሚካሄደውን ጭካኔያዊ  ድርጊት ተቃውመዋል ክርስቲያኖች በፓኪስታን የሚካሄደውን ጭካኔያዊ ድርጊት ተቃውመዋል  (ANSA)

የፓኪስታን ክርስቲያኖች ከ2015ቱ የፑንጃብ ጥቃት በኋላ አሁንም ድረስ 'በፍርሃት እንደሚኖሩ’ ተገለጸ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ አብያተ ክርስቲያናት በዚህ ባለንበት በመጋቢት ወር ለክርስቲያን ሰማዕታት እንዲጸልዩ በጋበዙበት ወቅት፥ የፑንጃብ ሃገረስብከት ካህን የሆኑት አባ ዛፋር ኢቅባል ፓኪስታን ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖችን የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በማንሳት በተለይም በፑንጃብ ግዛት አንዳንድ አከባቢዎች ባለፈው ዓመት ነሐሴ 2015 ዓ.ም ሙስሊሞች ቤተክርስቲያናትን እና መኖሪያ ቤቶችን ካጠቁ በኋላ በስጋት እንደሚኖሩ አስገንዝበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የፓኪስታን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነሐሴ 2015 ዓ.ም. በክርስቲያን ማህበረሰብ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት ተጨማሪ ምርመራ ይደረግበታል ብሎ በቅርቡ ካስተላለፈው ውሳኔ በኋላ፥ በፑንጃብ ግዛት ውስጥ ባለችው ጃራንዋላ ከተማ የሚኖሩ ክርስቲያኖች መሃል የተስፋ ጭላንጭልን ፈጥሯል።

ፍርድ ቤቱ የፑንጃብ ግዛት ባለስልጣናት ያቀረቡት የመጀመሪያ የምርመራ ዘገባ በቂ አለመሆኑን በማረጋገጡ በአካባቢው ያሉት የምርመራ ባለስልጣናት ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ ቁርጠኝነት የሌላቸው መሆኑን በመግለጽ ስለ ጅምላ ጥቃቱ ተጨማሪ መረጃ እንዲቀርብ ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱ የበርካታ ክርስቲያኖች መኖሪያ ከሆነችው ፑንጃብ አዲስ የምርመራ ውጤት እንዲቀርብለት የጠየቀው ከተፈጸሙት ጥቃቶች የተወሰኑት ብቻ ተመዝግበው ለፍርድ ቤቱ በሰነድ የቀረቡ በመሆኑ ምክንያት እንደሆነም ተገልጿል።

የፓኪስታን የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ሊቀ መንበር እና የሀይድራባድ ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ሳምሶን ሹካርዲን የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመደገፍ፥ ይህ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን በቁም ነገር እየተመለከተው እንደሆነ ያሳያል ብለዋል።

ጳጳሱ ‘ኤይድ ቱ ዘ ቸርች ኢን ኒድ’ ለተባለ በችግር ውስጥ ያሉትን ቤተክርስቲያናት ለሚረዳው ተቋም እንደተናገሩት፥ ዜናው “ለኛ ለክርስቲያኖች በጣም አወንታዊ” ነው ብለዋል።

የክርስቲያን መኖሪያ ቤቶች እና አብያተ ክርስቲያናት ወድመዋል

ነሃሴ 10 ቀን 2015 ዓ.ም. በፑንጃብ ግዛት የተቀሰቀሰውን ሁከት በተመለከተ የሃገረስብከቱ ካህን የሆኑት አባ ዛፋር ኢቅባል ቀኑ ለአካባቢው ክርስቲያኖች “ጥቁር ቀን” ነበር ብለዋል።

ሙስሊሞች የፑንጃብ ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ጃራንዋላ በክርስቲያን ማህበረሰቦች ላይ የጥቃት ድርጊቶችን የፈጸሙት ‘ሁለት ክርስቲያኖች በእምነታችን ላይ የስም ማጉደፍ ተግባር ፈጽመዋል’ ብለው ክስ ካቀረቡ በኋላ መሆኑ ተነግሯል።

ይሄንንም በማስመልከት አባ ኢቅባል እንደገለጹት “እነዚህ ሰዎች በጣም በመናደዳቸው ከ200 የሚበልጡ የክርስቲያን መኖሪያ ቤቶችን፣ 26 አብያተ ክርስቲያናትን፣ ትምህርት ቤትን፣ የመቃብር ሥፍራዎችን እና በርካታ መስቀሎችን፣ እንዲሁም መፅሃፍ ቅዱሳችንን ጭምር አቃጥለዋል” በማለት ለቫቲካን ዜና ተናግረዋል።

በወቅቱ ለሥልጠና ሮም የነበሩት ካህኑ በማከልም፥ “በእውነቱ በጣም መጥፎ ሁኔታ ነበር” ካሉ በኋላ ሆኖም ግን በጥቃቱ የተገደለ ክርስቲያን እንደሌለ ገልጸዋል።

"በፍርሃት ጥላ ስር መኖር"

ምንም እንኳን አሁን ሁኔታው በቁጥጥር ሥር የዋለ ቢመስልም ክርስቲያኖች አሁንም ድረስ ፍርሃቱ እንዳልለቀቃቸው የተነገረ ሲሆን፥ አባ ኢቅባል ይሄን አስመልክተው “ክርስቲያኖች አሁንም ድረስ በፍርሀት ጥላ ስር እየኖሩ ነው፥ በነጻነት መንቀሳቀስ፣ በነጻነት መናገር እና በነጻነት መስራት አይችሉም። በአሁኑ ጊዜ በአካላቸው ላይ ጉዳት ላይደርስባቸው ይችላል፥ ነገር ግን ፍርሃት በልባችን እና በአዕምሮአችን ላይ ነግሷል” ሲሉ ገልጸዋል።

በፑንጃብ የሚኖሩ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ድሆች እና በሙስሊም አሠሪዎች ላይ ጥገኛ እንደሆኑ ተነግሯል። "በእኛ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ ሴቶች የሚሰሩት በሙስሊም ቤተሰቦች ውስጥ ነው፣ ወንዶች ደግሞ በሙስሊም የመሬት ባለቤቶች ጋር የእርሻ ሥራ ይሰራሉ፥ በመሆኑም እነዚህ ክርስቲያኖች አሁን ውጥረቱ በስራቸው ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል መማለት ስጋት ላይ ናቸው” ብለዋል ካህኑ።

ከጥቃት በኋላ ፍትህን መፈለግ

ከነሃሴው ጥቃት በኋላ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው የነበረ ቢሆንም፥ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ተጠርጣሪዎች መለቀቃቸውን አባ ኢቅባል አስታውቀዋል።

በፓኪስታን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ችሎት 304 ሰዎች በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ 22 ጉዳዮች ብቻ የተመዘገቡ ሲሆን፥ 18 ክሶች መሰብሰባቸውን አንድ የፑንጃብ ፍርድ ቤት ሰራተኛ ተናግሯል። በዚህ መረጃ መሰረት የክርስቲያኑ ማህበረሰብ በአካባቢው ፖሊስ ላይ ያለው እምነት ዝቅተኛ መሆኑን አባ ኢቅባል ከጠቆሙ በኋላ፥ ፍትህ እናገኛለን ብለን ብዙም ተስፋ የለንም ብለዋል።

በፓኪስታን የሚገኙ የቤተክርስትያን ተወካዮች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ባለፈው ዓመት በቁጥር አናሳ በሆኑ ክርስትያኖች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ተባብሶ እንደነበር፣ የሀሰት የስድብ ውንጀላ፣ የአካል ጥቃት፣ አፈና፣ መደፈር እና በርካታ ሰዎች በግዳጅ እምነት መለወጣቸውን ሪፖርት አድርገዋል።

የፓኪስታን ጳጳሳት ጉባኤ የህግ አካል የሆነው የብሔራዊ ፍትህ እና ሰላም ኮሚሽን ዳይሬክተር የሆኑት ናኢም ዩሳፍ ጊል “በ2015 ዓ.ም. የክርስቲያን ማህበረሰብ በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ነበረ” ብለዋል።

እምቅ የህብረተሰብ መለወጫ ነጥብ

አንዳንድ የጃራንዋላ ነዋሪዎች፣ ሙስሊሞችን ጨምሮ፣ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ዝርዝር መረጃ በማጋራት፣ መረጃውን አሰረጭተዋል ሲሉ የሃድራባድ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ሹካርዲን ለኤሲኤን ተናግረዋል። እነዚህ ዜጎች “ነገሮች በዚህ መንገድ መቀጠል እንደማይችሉ አሳይተዋል” በማለት በጃራንዋላ ከክርስቲያኖች ጋር ያለው ትብብር እንደሚቀጥል ያላቸውን ተስፋ ገልጿል።

የላሆር ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ሴባስቲያን ፍራንሲስ ሾው በበኩላቸው ፀረ-ክርስቲያን አመጽ በፓኪስታን በክርስቲያኖች እና በሙስሊሞች መካከል ቅራኔ ሊፈጠር የሚችል ለውጥ አድርገው እንደሚመለከቱት ተናግረዋል።

ጳጳሱ በ2015 ዓ.ም. መገባደጃ ላይ ከኤሲኤን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “በርካታ ሙስሊሞች ጃራንዋላ ላይ የተከሰተው ክስተት የአጠቃላይ የአገሪቱን ገጽታ መግለጽ እንደሌለባቸው ይሰማቸዋል ። ለመጀመሪያ ጊዜ የሙስሊም ምሁራን ከጎናችን ቆመዋል” በማለት መንግስትን ለውይይት እና ለተሻለ ማህበረሰብ እንዲፈጠር የሚያነሳሱ የእስልምና ሀይማኖት አባቶች ምልክቶች ናቸው ብለዋል።

ሰብአዊ ክብርን እና የጋራ መከባበርን ማበረታታት

አባ ኢቅባል ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በጃራንዋላ የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የክርስቲያኑን እና የሙስሊሙን ትብብርን አወንታዊ ምሳሌዎችን ጠቅሰዋል። በፓኪስታን ያሉ ክርስቲያኖች ላይ አድልዎ እና ፈተናዎች ቢኖሩም ውይይት እና ሰላም የማስፈንን አላማ እንዳላቸው አፅንዖት ሰጥተውም ተናግረዋል።

"በፓኪስታን ብዙ ችግሮች ያጋጥሙናል፥ በሰው ልጅ ክብር ላይ መድልዎ፣ የፍትህ መዛባት፣ የኢኮኖሚ ቀውስ ያጋጥሙናል፥ ይህ ሁሉ ቢሆንም እኛ ክርስቲያኖች በሰላምና በፍቅር እንመሰክራለን፥ እንዲሁም እንሰብካለን። ተስፋ አንቆርጥም፥ እያንዳንዱ ሰው በክብር የሚታይበትና ክብራቸው የሚረጋገጥበት ሁኔታ ለመፍጠር የበኩላችንን ድርሻ እየተወጣን እንገኛለን” ሲሉ ተናግረዋል።
 

13 March 2024, 13:51