የመጋቢት  08/2016 ዓ.ም ሰንበት ዘቅድስት ዕለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የመጋቢት 08/2016 ዓ.ም ሰንበት ዘቅድስት ዕለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የመጋቢት 08/2016 ዓ.ም ሰንበት ዘቅድስት ዕለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የዕለቱ ምንባባት

 

1.    1ኛ ተሰ. 4፥1-12

2.    1ኛ ጴጥ 1፥13-25

3.    ሐዋ.ሥ. 10፥17-29

4.    ማቴ 6፥16-24

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

“ስትጾሙ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ እነርሱ መጾማቸው እንዲታወቅላቸው ሆን ብለው በፊታቸው ላይ የሐዘን ምልክት ያሳያሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፤ እንዲህ የሚያደርጉ ዋጋቸውን በሙሉ ተቀብለዋል። አንተ ግን በምትጾምበት ጊዜ ፊትህን ታጠብ፤ ራስህንም ተቀባ፤ በዚህም መጾምህ በስውር ያለው አባትህ ብቻ የሚያውቀው፣ ከሰዎች ግን የተሰወረ ይሆናል፤ በስውር የተደረገውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል።

ሰማያዊ ሀብት

“ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በሚችልበት በዚህ ምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ። ነገር ግን ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በማይችልበት በዚያ በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ፤ ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያው ይሆናልና።

“ዐይን የሰውነት መብራት ነው፤ ስለዚህ ዐይንህ ጤናማ ከሆነ መላው ሰውነትህ በብርሃን የተሞላ ይሆናል። ዐይንህ ታማሚ ከሆነ ግን መላው ሰውነትህ በጨለማ የተሞላ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ውስጥ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፣ ጨለማው እንዴት ድቅድቅ ይሆን? “አንድ ሰው ሁለት ጌቶችን ማገልገል አይችልም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወድዳል፤ ወይም አንዱን አክብሮ ሌላውን ይንቃል። እግዚአብሔርንና ገንዘብን በአንድነት ማገልገል አይቻልም።

 

የእለቱ አስተንትኖ

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት ዓምልኮ አቆጣጠር ዘቅድስት የሚለውን ሰንበት እናከብራለን። የዐብይ ጾም ሁለተኛው ሰንበት ዘቅድስት ተብሎ የሚጠራበት ምክንያት ከእዚሁ ሰንበት ዋዜማ ጀምሮ የሚጀመረው ጾመ ድጓ ቀለሙ “ዛቲ ዕለተ ቅድስት ይዕቲ” ይች ቀን የተቀደሰች ናት፣ ያረፍኩባት ቅድስት ሰንበት ናት፣ እኔም ቅዱስ እንደሆንኩኝ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ፣ አብ ሰንበትን አከበራት፣ ቀደሳት፣ እያለ የሰንበትን ቅድስና እያነሳሳ ስለሚዘመር ይህ ሰንበት “ሰንበት ዘቅድስት” ተብሎ ሊጠራ ችሏል።  ስያሜው ሰንበት ቅድስት እንድትሆን በኦሪትም በአዲስ ኪዳንም እግዚአብሔር የባረካት የቀደሳት ዕለት መሆኗን የሚያሳስብና እግዚአብሔር ቅዱስ እንደሆነ የፈጠረውም ሰው ቅድስናን መያዝ እንደሚገባው የሚያሳስብ ነው።

በዚህ ዕለት በተለይም በዐብይ ጾም ወቅት የእግዚአብሔር ቃል በመልዕክቶቹና በወንጌሉ አማካኝነት ወደ እያንዳንዳችን ይመጣል፣ በቃሉም አማካኝነት እንዴት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕይወት መኖር እንደሚገባን ይመክረናል።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በዛሬው መልዕክቱ (1ኛ ተሰ. 4፥1-12) ሲናገር እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው ይኸውም “ለቅድስና ተጠርተናልና ለቅድስና እንድንኖር” በማለት ይናገራል።

“እግዚአብሔር ቅዱስ ነው” ለዚህም ነው መላእክትና ቅዱሳን ዘወትር እርሱን “ቅዱስ ቅድስ ቅዱስ” እያሉ የሚያመሰግኑትና የሚሰግዱለት።

እኛ በእርሱ አምሳል የተፈጠርን እንደመሆናችን መጠን እግዚአብሔር ለጠራን የቅድስና ጉዞ እርሱ በሰጠን ጸጋ በመታገዝና ልቦናችንን በማዘጋጀት የድርሻችንን በመወጣት የእርሱ ቅድስና ተካፋዬች እንሁን፤ ይህንንም ቅድስና እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ እንዲኖር ይፈልጋል፤ በመሆኑም በቅድስና ለመኖር የሚያስችለንን ጸጋ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት አብዝቶ ይሰጠናል።

ፍጹም ቅድስናና ፍጹም መልካምነት ከእግዚአብሔር ብቻ ይመነጫል፣ እኛም ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት በመፍጠር ይህንን ቅድስናና መልካምነት እንድንካፈል ዘወትር ይጋብዘናል።

ቅድስናችንን የሚያጐድፈው አንድ ነገር ብቻ ነው፣ ይኸውም “ኃጢአት” ነው፤ የቅድስና ሕይወት ማለት እንከን የለሽ ሕይወትን መኖር፣ አልያም ምንም ኃጢአት ሳይሰሩ መኖር ማለት አይደለም። ይልቁንም በኃጢአት ቀንበር በምንያዝበት ወቅት እና ከቅድስና ሕይወት መስመር በምንስትበት ጊዜ ከኃጢአት ጋር ተጋድሎ የምናደርግበት መሣርያ ነው። ይህንንም ቃል ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን መልዕክቱ አበክሮ ይገልጽልናል። “ስለዚህ የእግዚአብሔርን የጦር መሣርያ በሙሉ አንሱ፣ በዚህ ሁኔታ ክፉ ቀን ሲገጥማችሁ የጠላትን ኃይል መቃወምና እስከመጨረሻም ከተዋጋችሁ በኋላ ጸንታችሁ መቆም ትችላላችሁ” (ኤፌ 6፥13) ይለናል።  

ሙሉ ለሙሉ የቅድስና ሕይወታችንን ታጥቀን በተጋድሎ እንኖር ዘንድ ክርስቲያናዊ ኃላፊነት አለብን፤ ይህም ትጥቃችን የእግዚአብሔር ቃል እና ምስጢራት ናቸው። በሕይወታችን የእግዚአብሔርን ቃል ከከበረው ዕንቁ በላይ ልንከባከበው የሕይወታችን መሣርያ ልናደርገው ይገባል፣ ምክንያቱም ቃሉ ለሕይወታችን ስንቅ ለመንገዳችን ብርሃን ነውና። በኃጢአት በምንወድቅበት ወቅት እንደገና ኃይል የሚሰጠን ከጸጋው ሙላት እርሱ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ስለዚህም ለቅድስና ሕይወታችን ጉዞ ስንቅ ይሆነን ዘንድ በተለይም በዚህ ጾም ወቅት በቃሉና በምስጢራቱ በሙላት በመሳተፍ ከሁሉ አብልጠን በልባችን ልንይዘው፣ ልንለማመደውየእራሳችን ልናደርገው እና ዕለት በዕለት መሣርያችን ልናደርገው ይገባል።

የዛሬው ቅዱስ ወንጌል (ማቴ. 6፡16-22) ላይ ተወስዶ የተነበበ ሲሆን በአጠቃላይ በእዚህ በማቴዎስ ወንጌል በምዕራፍ 6 ላይ በመሰረታዊነት ኢየሱስ ስለ ሦስት ነገሮች ተናግሯል- ስለ ምጽዋት አስጣጥ (ማቴ 6.1-6)፣ ስለ ጸሎት (ማቴ 6.5-15) እና ስለ ጾም (ማቴ 6.16-18)። የአይሁዶች ሦስቱ የአምልኮት ተግባሮች ነበሩ። ኢየሱስ “ሰዎች እንዲያዩላችሁ፣ መልካም ሥራችሁን በፊታቸው ከማድረግ ተጠንቀቁ፤ እንዲህ ካደረጋችሁ ከሰማዩ አባታችሁ ዋጋ አታገኙም” በማለት አይሁዳዊያንን ተችቷቸዋል (ማቴ 6፡2.5.16)። በኢየሱስ ቃላቶች ውስጥ፣ ከእግዚአብሔር ጋር አዲስ ዓይነት ግንኙነት ታየ እናም ለእኛም አዲስ መንገድ ይከፍትልናል። “በስውር የሚያይ አባትህ ይከፍልሃል” (ማቴ 6፡4) ይላል። "አባታችሁ ማንኛውንም ነገር ሳትለምኑት የሚያስፈልጋችሁን ያውቃል" (ማቴ 6:8) "ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋል" (ማቴ 6:14) ብሎ በመናገር ኢየሱስ ወደ እግዚአብሄር ልብ የምንደርስበት አዲስ መንገድ አቅርቦልናል፣ የአምልኮ ስራዎችን በሚመለከት በተናገራቸው ቃላት ላይ ማሰላሰላችን ይህንን አዲስ መንገድ እንድናውቅ ይረዳናል።

ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ሰዎች እንዲያዩላችሁ፣ መልካም ሥራችሁን በፊታቸው ከማድረግ ተጠንቀቁ” ኢየሱስ የተናገረው ፍትህ እግዚአብሔር ወደ ሚፈልገው ቦታ መድረስን ያካትታል። ወደዚያ የሚወስደው መንገድ በእግዚአብሔር ሕግ ውስጥ ተገልጿል፡ ኢየሱስ አንድ ሰው በሰዎች ዘንድ ለመወደስ ሕግን መጠበቅ እንደሌለበት አስጠንቅቋል። ቀደም ሲል “ጽድቃችሁ ከፈሪሳውያንና ከኦሪት ሕግ መምህራን ጽድቅ ልቆ ካልተገኘ መንግሥተ ሰማይ መግባት አትችሉም” (ማቴ 5፡20) ብሎ ተናግሮ ነበር።

ይህንን ዓረፍተ ነገር ስናነብ በኢየሱስ ዘመን የነበሩትን ፈሪሳውያን ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዳችን ውስጥ በሚገኘው የፈሪሳዊነት መንፈስ ሁሉ ላይ ማሰብ አለብን። የማርያም እጮኛ የነበረው ዮሴፍ የፈሪሳውያንን ሕግ ፍትህ ቢከተል ኖሮ ማርያምን ማውገዝ ነበረበት። እርሱ ግን “ጻድቅ” ነበር (ማቴ 1፡19)፣ አስቀድሞ በኢየሱስ የተነገረውን አዲስ ፍትህ አግኝቷል። ለዚህም የጥንቱን ሕግ በመተላለፍ የማርያምንና የኢየሱስን ሕይወት አዳነ። ኢየሱስ ያወጀው አዲሱ ፍትህ ከሌላ ምንጭ ይፈሳል። ደህንነታችንን በውስጣችን መገንባት ያለብን ለእግዚአብሔር በምንሰራው ውጫዊ የሆነ ተግባር ሳይሆን እግዚአብሔር በሚሰራልን ላይ ነው። ይህ የኢየሱስን የአምልኮ ሥራዎችን ለመገንዘብ አጠቃላይ ቁልፍ ነው። ወንጌላዊው ማቴዎስ ይህንን አጠቃላይ መርሆ ለምጽዋት፣ ለጸሎት እና ለጾም ልምምዶች ይጠቀማል። ከእዚህ አስተምህሮ እይታ አንጻር በመጀመሪያ ምን ማድረግ እንደሌለብን ይናገራል፣ ከዚያም ምን ማድረግ እንዳለብን ወዲያውኑ ያስተምረናል።

ማቴ 6፡5፡ እንዴት መጸለይ እንደሌለበት።

ኢየሱስ ስለ የተሳሳተ የጸሎት መንገድ ሲናገር በዚያ ዘመን ስለነበሩ አንዳንድ እንግዳ ልማዶችና ተግባሮች ጠቅሷል። ለጠዋት፣ የቀትርና የከሰአት ጸሎት ጥሩንባ ሲነፋ እጆቻቸውን ከፍተው ለመጸለይ በመሀል መንገድ ላይ እራሳቸውን ለማቅረብ የሞከሩ ሰዎች ነበሩ፣ በዚህም ራሳቸውን ለሁሉም እንዲታዩ በማድረግ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ሆነው ተቆጥረዋል። በምኩራብ ውስጥ ያሉ ሌሎች የማህበረሰቡን ቀልብ ለመሳብ ከልክ ያለፈ አመለካከት ነበራቸው።

ማቴ 6፡6፡ እንዴት መጸለይ እንደሚቻል።

ምንም ጥርጣሬ ሳይገባን እንዴት መጸለይ እንዳለብን ኢየሱስ ያለጥርጥር ያሰተምረናል። በምስጢር መጸለይ ያለብን በእግዚአብሔር አብ ፊት ብቻ ነው ይላል። ማንም አያይህም። በእርግጥ ምናልባት ለሌሎች የማትጸልይ ሰው ልትሆን ትችላለህ። ምንም አይደል! ስለ ኢየሱስም እንኳን ይህ ሰው “ከእግዚአብሔር አይደለም!” ብለው ተናግረው ነበር። ይህም የሆነው ኢየሱስ በሌሊት ብዙ ይጸልያል እንጂ ስለሌሎች አስተያየት ግድ ስላልነበረው ነው። ዋናው ነገር ሰላማዊ ሕሊና እንዲኖረኝ እና የሚቀበለኝ እግዚአብሔር አብ መሆኑን እርግጠኛ መሆን ነው።

ማቴ 6፡16፡ መልካም ያልሆነ ጾም

ኢየሱስ የጾምን የተሳሳቱ ድርጊቶች ነቅፏል። ፊታቸው ያዘነ፣ ያልታጠቡ፣ የተቀደደ ልብስ የለበሱ፣ ጸጉራቸውን የምያንጨበርሩ፣ ሁሉም ሰው ጾመኛ መሆናቸውን ያይ ዘንድ ፍጹም በሆነ መንገድ ለመሄድ የሚፈልጉ ሰዎች ነበሩ። እንዲህ ዓይነቱን የታይታ ጾም እግዚአብሔር አይቀበለውም። እግዚአብሔር በነቢዩ ኢሳያስ አማካይነት እንዲህ ሲል ተናግሯል፣ “እንግዲህ እኔ የመረጥሁት ጾም፣ የጭቈናን ሰንሰለት እንድትበጥሱ፣ የቀንበርን ገመድ እንድትፈቱ፣ የተጨቈኑትን ነጻ እንድታወጡ፣ ቀንበርን ሁሉ እንድትሰብሩ አይደለምን? ምግብህን ለተራበ እንድታካፍለው፣ ተንከራታቹን ድኻ ወደ ቤትህ እንድታስገባው፣ የተራቈተውን ስታይ እንድታለብሰው፣ የሥጋ ዘመድህንም ፊት እንዳትነሣው አይደለምን? ይህ ከሆነ ብርሃንህ እንደ ንጋት ጮራ ይፈነጥቃል፤ ፈውስህ ፈጥኖ ይደርሳል፤ ጽድቅህ ቀድሞህ ይሄዳል፤ የእግዚአብሔር ክብር ደጀን ይሆንልሃል። የዚያን ጊዜ ትጣራለህ፤ እግዚአብሔርም ይመልስልሃል፤ ለርዳታ ትጮኻለህ፤ እርሱም፣ ‘አለሁልህ’ ይልሃል። “የጭቈና ቀንበር የክፋትን ንግግርና ጣት መቀሰርን ከአንተ ብታርቅ፣ ለተራበው ብትራራለት፣ የተገፉት እንዲጠግቡ ብታደርግ፣

ብርሃንህ በጨለማ ያበራል፤ ሌሊትህም እንደ ቀትር ፀሓይ ይሆናል። እግዚአብሔር ሁልጊዜ ይመራሃል፤ ፀሓይ ባቃጠለው ምድር ፍላጎትህን ያሟላል፤ ዐጥንትህን ያበረታል፤ በውሃ እንደ ረካ የአትክልት ቦታ፣ እንደማይቋርጥም ምንጭ ትሆናለህ (ኢሳያስ 58፡ 7-11)።

ማቴ 6፣17-18፡ እንዴት መጾም እንዳለብን

ኢየሱስ ተቃራኒውን ይመክራል:- ስትጾሙ በሰማያት ያለው አባታችሁ ብቻ በስተቀር እንደ ጾማችሁ ማንም እንዳያውቅ “አንተ ግን በምትጾምበት ጊዜ ፊትህን ታጠብ፤ ራስህንም ተቀባ” በማለት ይናገራል። አስቀድመን እንደተናገርነው፣ በፊታችን የሚከፈተው አዲስ ወደ እግዚአብሔር ልብ የመድረሻ መንገድ ነው። በውስጣችን ሊያረጋግጥልን፣ ኢየሱስ ለእግዚአብሔር የምናደርገውን አይጠይቅም፣ ይልቁንም እግዚአብሔር ለእኛ የሚያደርገውን ነው የሚጠይቀው። ምጽዋት፣ ጸሎት እና ጾም የእግዚአብሔርን ሞገስ ለመግዛት የምንጠቀምባቸው ገንዘቦች አይደሉም፣ ነገር ግን ለተቀበልነው እና ለተለማመድነው የእርሱ ፍቅር የምስጋና ምላሽ ነው።

ወንጌላዊ ማቴዎስም ይህንኑ በመደገፍ ሃብታችንን ብልና ዝገት በማያጠፋው በእግዚአብሔር ዘንድ እንድናከማች ይነግረናል። ለኛ ለክርስቲያኖች ሃብታቸን ምንድን ነው? ሃብታችን የእግዚአብሔር ቃል ነው፣ ከእግዚአብሔር የወሰድነውን መልካምነትና ቅድስና ናቸው።

ይህንን መልካምነት በሕይወታችን ከኖርነው ቃሉንም ከጠበቅን በእርግጥም ሃብታችንን በእግዚአብሔር ዘንድ አከማችተናል ማለት እንችላለን። ምክንያቱም ሃብትህ ባለበት ቦታ ልብም በዛ ይሆናልና ነው።

እግዚአብሔር በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ነፍሳችን፣ በፍጹም ሃሳባችን፣ በፍጹም ኃይላችን እንጂ በከፊል እንድናገለግለው አልጠራንም።

በአንድ ጊዜ ሰው ለሃብትና ለእግዚአብሔር ቅድሚያ የሚሰጥ ከሆነ የእግዚአብሔርም የገንዘብም ተገዢ ሊሆን አይችልም። አንዱን መምረጥ ይኖርብናል ለዚህም መንፈሳዊና የእምነት ዓይናችንን ከፍተን መልካም የሆነውን ነገር ልንከተል ይገባናል።

ሰው በክርስትና ሕይወት ውስጥ እግዚአብሔርን በጽናት ለመከተል እንዲችል በተጠራበት ሕይወት በመኖር ተጋድሎን ማድረግ ያስፈልገዋል። ተጋድሎአችን ደግሞ በጾምና በጸሎት ሲታገዝ ውጤታማ ይሆናል። ስለዚህ ጾማችንም ይሁን ጸሎታችን እንደ አይሁዳውያኑ ለታይታ ሳይሆን እግዚአብሔርን የሚያስደስት ለእኛም በረከትን የሚያመጣ ሊሆን ይገባዋል። እግዚአብሔር የሚፈልገው ጾም ደግሞ ትንቢተ ኢሳ. 58 ላይ እንደተጠቀሰው ትሕትናና መልካም ሥራ የታከለበት ጾም እንዲሆን ያስፈልጋል።

ይህንንም ለማድረግ እንድንችል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታግዘን፣ ጸጋና በረከቱን ከልጇ ታሰጠን።

የሰማነውን ቃል በሕይወት መኖር እንድንችል ጸጋና በረከቱን ያብዛልን !

አዘጋጅ እና አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን 

 

 

 

16 March 2024, 14:54