2020.04.09 Santuario della Divina Misericordia, Vilnius (Evaldas Lasys)

ሰባቱ አካለዊ የምሕረት ተግባራት

አሁን ያለንበት ወቅት የዓብይ ጾም ወቅት እንደ ሆነ ይታወቃል። በዚህ የዐብይ ጾም ወቅት ጉዞ ላይ በጣም አስፈላጊ ወደ ሆኑ ነገሮች መመለስ እንችል ዘንድ፣ ከግብዝነት እና ትክክለኛ ካልሆኑ ነገሮች እንድንቆጠብ የሚረዱንን ሦስት እርምጃዎችን እንወስድ ዘንድ ቅዱስ ወንጌል ሐሳብ ያቀርብልናል፡ እነዚህም ምጽዋዕት መስጠት፣ ጸሎት እና ጾም ናቸው። ጸሎት ከእግዚኣብሔር ጋር፣ ምጽዋዕት ከባልንጀራዎቻችን ጋር እና ጾም ደግሞ ከራሳችን ጋር ተመልሰን በአዲስ መልክ ሕብረት እንድንፈጥር ይረዱናል።

የእዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

በዚህ የዓብይ ጾም ወቅት ከምናደርገው መንፈሳዊ ተጋድሎ በተጨማሪ ጾማችን እና ጸሎታችን ተጨባጭ በሆነ መልኩ መግለጽ የሚገባን ሲሆን በተለይም ደግሞ ኢየሱስ በማቴዎስ ወንጌል 25፡13- ጀምሮ በግልጽ ያስቀመጠውንና “የሰው ልጅ ከመልአክቱ ሁሉ ጋር በክብሩ ሲመጣ፣ በክብሩ ዙፋን ላይ ይቀመጣል፤ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እርሱም እረኛ በጎችን ከፍየሎች እንደሚለይ፣ ሕዝቡን አንዱን ከሌላው ይለያል፤ በጎቹን በቀኙ፣ ፍየሎቹን ግን ደግሞ በግራው ያቆማቸዋል፣ ከዚያም በመቀጠል ተርቤ አብልታችሁኛል፣ ተጠምቼ አጠጥታችኋኛል፣ ታርዤ አልብሳችሁኛል፣ እንግዳ ሆኜ መጥቼ ደግሞ ተቀብላችሁኛል. . .” ወዘተ በማለት ለሚያቀርብልን ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ያስችለን ዘንድ የሚረዱንን መንፈሳዊና አካለዊ የምሕረት ተግባራትን መፈጸም ይገባናል።

በዛሬው እለት ዝግጅታችን አካለዊ የምሕረት ተግባራት የሚባሉት እነማን እንደ ሆኑ እንመለከታለን፣ ተከታተሉን።

አካለዊ የምሕረት ተግባራት

አካላዊ የምሕረት ወይም የበጎ ሥራ ተግባራት የሚባሉት መሰረታቸውን ያደረጉት በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 25: 31 ጀምሮ በጠጠቀሰው የኢየሱስ አስተምህሮ ላይ የተመረኮዙ ሲሆኑ እነዚህም በዓለም መጨረሻ የሚሆነውን የፍርድ ሂደት የሚያመልክትና “ኢየሱስ በመለአክቱ ታጅቦ በፍርድ ወንበር ላይ በመቀመጥ፣ እረኛው በጎችን ከፍዬሎች  እንደሚለይ እርሱም ሕዝቦችን ይለያል፣ በጎቹን በቀኙ ፍዬሎቹን ደግሞ በግራው ያቆማቸዋል” እንደ ሚለው በመጨረሻው ቀን በኢየሱስ ፊት በምንቆምበት ወቅት ለሚያቀርብልን ጥያቄዎች በድፍረት በቂ የሆነ ምላሽ መስጠት እንድንችል እና ከፍየሎቹ ተርታ ሳይሆን ከበጎቹ ጎራ መሰለፍ እድንችል የሚያግዙን ተግባራትን መፈጸም ይገባል። እነዚህ አካላዊ የምሕረት ተግባራት የሚባሉት እነማን ናቸው?

1.           የተራበን ማብላት

አሁነ በምንገኝበት ዓለማችን በጣም ብዙ የሚባሉ ሰዎች በምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ይገኛሉ። በተቃራኒው ደግሞ የበለጸጉ በሚባሉ አገራት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የምግብ ብክነት የሚታይ ሲሆን በማንኛውም ረገድ ምግብን ማባከን ተገቢ አለመሆኑን በመረዳት በአግባቡ እንድንጠቀም እና የተራቡ ወገኖቻችንን፣ ጎሬቤቶቻችንን፣ እንዲሁም በተለያዩ አጋጣሚዎች በየመንገዱ ወይም ደግሞ የቤታችንን በር ለሚያንኳኩ ሰዎች አስፈላጊውን ምላሽ በመስጠት መንፈሳዊ ሕይወታችንን ያጠናክራል፣ ከእግዚኣብሔር በረከትን ያስገኛል። የተራበን ማብላት በረከትን ያስገኛል። በሉቃስ ወንጌል 16.19-31  ላይ የተጠቀሰውን የሀብታሙን ሰውና የድኻውን የአልዓዛር ታሪክ ማንበብና ያነበብነውን በተግባር በሕይወታችን መፈጸም ይገባናል።

2.    የተጠማን ማጠጣት

በተለያየ የዓለም ክፍል ውስጥ የሚገኙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን መሰረታዊና ለሰው ልጆች ሕይወት አስፈላጊ ከሚባሉ ነገሮች በቀዳሚነት በሚጠቀሰው የንጹህ ውሃ እጥረት ይሰቃያሉ። በንጹሕ ውሃ እጥረት የሚሰቃዩ ወንድም እና እህቶቻችንን የተቻለንን ያህል እገዛ በማድረግ የክርስቲያናዊ ግዴታችንን ልንወጣ ይገባል። ይህንን የንጹህ ውሃ እጥረት ለተጠሙ ሰዎች ብቻ ውሃን በመስጠት የምንወጣው ተግባር ብቻ ሳይሆን ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የተቻለንን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅብናል። ኢየሱስ በቃሉ “ እውነት እውነት እላችኋለሁ የኔ ደቀ መዝሙር በመሆኑ ከነዚህ ታናናሾች ለአንዱ አንድ ብርጭቆ ቀዝቃዛ ውሃ እንኳን የሚሰጥ ሰው ዋጋውን አያጣም” (የማቴዎስ ወንጌል 10.42)፣ በተጨማሪም የእኛን ፍቅር የተጠሙ ሰዎችን፣ ፍቅር በመለገስ ልናበረታቸው ይገባል።

3.    የታረዘን ማልበስ

ቤተ ክርስቲያናችን በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ የተጠቀሱትን 10ቱን ትዕዛዛት እንድናከብርና በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያን ምስጢራትን እንድንሳተፍ ጸሎት ማድረግም አስፈላጊ እንደ ሆነ ታስተምረናለች።  ብዙን ጊዜ በመኖሪያ ቤቶቻችን የሚገኙትን ቁም ሳጠኖችን ከፍተን በምናይበት ወቅት በጣም ብዙ ሊባሉ የሚችሉ የማንጠቀምባቸው አልባስት ያለምንም ተግባር ተቀምተው እናያለን። ከእነዚህ ውስጥ ለታረዙ ሰዎች ማካፈል ይኖርብናል።

4.   መጠለያ የሌላቸውን ሰዎች ማስጠለል

የሰው ልጆች በተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች የተነሳ ለመጠሊያ እጥረት ይጋለጣሉ። ይህንንም ሁኔታ ለመረዳት ርቀን መሄድ አይጠበቅብንም። ምክንያቱም በየመንገዱ ላይ ወድቀው የሚገኙ ብዙ ሰዎችን ማየት የተለመደ በመሆኑ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን በመኖሪያ ቤት እጥረት የሚሰቃዩ ሰዎችን በተለይም በየጎዳናው ላይ ሰፍረው የሚገኙ የወደፊት የአገር ተረካቢ የሚሆኑ ሕጻናትን ማገዝ እንደ ሚገባን ጥሪ ያደርግልናል።

በሉቃስ ወንጌል 16: 19-31 ላይ የተጠቀሰውን የሐብታሙን ሰው እና የድኸውን የአልዓዛርን ምሳሌ መመልከት ተገቢ ነው። ድኻው አልዓዛር በሐብታሙ ሰው በር ሥር ተኞቶ በብርድ እና በርሃብ ሲሰቃይ ሐብታሙ ሰው ግን ሁሌ ማታ ማታ በቤቱ ድግስ ያዘጋጅ ነበር። አልዓዛርን ግን አላሰበውም ነበር። በመጨረሻው ቀን ግን ሁሉም የተገላቢጦሽ ሆኖ ነበር። ድኻው አልዓዛር በምድራዊ ሕይወቱ በጣም ተሰቃይቶ የነበረ ሰው ሲሆን በሰማያዊ ቤቱ ግን የቅዱሳን መኅበር አባል በመሆን አዲስ የደስታ ሕይወት መኖር ሲጀምር በተቃራኒው ደግሞ በእዚህ ምድር በደስታ እና በፍስሐ የኖረው ሐብታሙ ሰው ግን ወደ ገሐነም እሳት ተጣለ። በጾማችን ወቅት በየቤቶቻችን ደጅ ላይ የሚገኙትን መጠለያ ያጡትን ሰዎች መርዳት ይኖርብናል።

5. ሕሙማንን መጎብኘት (ማቴ። 25.36 ታምሜ አስታምማችኋኛል)

ብዙን ጊዜ የታመሙ ወገኖቻችንን እንዘነጋቸዋለን። ማስተውል የሚገባን ጉዳይ እነዚህ ታማሚዎች የእኛን ትኩረት እና እርዳት እንደ ሚሹ ማወቅ ግን ያስፈልጋል። የተመሙትን ለመርዳት ምን ምን ተጨባጭ የሆኑ ተግባሮችን መፈጸም ይገባና?

1.      ደም መለግስ

2.    በማይድን በሽታዎች የሚሰቃዩትን ሰዎች ወደ አሉበት ሥፍራ ሄዶ ማጫወት፣ ማዋራት፣ ስቃያቸውን ለጊዜውም ቢሆን እንዲረሱ ማድረግ ያስፈልጋል።

3.    በአከባቢያችን የሚገኙትን የእድሜ ባለጸጎችን መጎብኘት ያስፈለጋል።

4.    ምግብ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ካሉ፣ መድኋኒት የሚፈልጉ ካሉ የመሳሰሉትን እርዳታዎችን ማድረግ ይጠበቃል።

6. የታሰረን መጎብኘት (ማቴ። 25.36)

በእሥር ላይ የሚገኙ ሰዎች ምንም እንኳን ከጥፋታቸው ይታረሙ ዘንድ በማሰብ የታሠሩ ቢሆንም በእግዚኣብሔር ምልክ እና አምሳያ የተፈጠሩ ወንድም እህቶቻችን መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም። ምንም ዓይነት ስህተት ይፈጽሙ የእግዚኣብሔር ቃልን እንዲሰሙ ማድረግ እና እንዲጸጸቱ መርዳት አስፈላጊ ነው።

7. የሞተን መቅበር (መ. ጦቢት 1.17-19)

የቀብር ሥነ-ሥረዓትን በምንታደምበት ወቅት ሁሉ ለአዘኑት ሰዎች ሁሉ በእዚህ ወሳኝ እና አስቸጋሪ በሆነ ወቅት የማጽናናትና እና የማበረታታት የመግለጫ ምልክት ነው። እንዲሁም በቀብር ሥነ-ሥረዓት ላይ ተገኝተን ጸሎት ማቅረብ ለሕይወት ያለንን ክብር እንገልጻለን ።

 

 

 

21 March 2024, 16:01