የሚያዝያ 6/2016 ዓ.ም ዘገብርኄር ዕለተ ሰንበት መልዕክቶች እና ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የዕለቱ ንባባት፦
1. 2ጢሞ 2:1-15
2. 1ጴጥ 5:1-11
3. ሐዋ 1:6-8
4. ማቴ 25:14-30
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል
የሰነፉ አገልጋይ ምሳሌ
“የእግዚአብሔር መንግሥት አገልጋዮቹን ጠርቶ ያለውን ንብረት በዐደራ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ሊሄድ የተነሣ አንድ ሰውን ትመስላለች፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው በመደልደል ለአንዱ አምስት መክሊት፣ ለሌላው ሁለት፣ ለሌላው ደግሞ አንድ መክሊት ሰጥቶ ጕዞውን ቀጠለ። አምስት መክሊት የተቀበለው ሰውየ፣ ወዲያው በገንዘቡ ንግድ ጀምሮ አምስት መክሊት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት መክሊት የተቀበለው ሁለት አተረፈ፤ አንድ መክሊት የተቀበለው ግን መሬት ቈፍሮ የጌታውን ገንዘብ ደበቀ።
“የአገልጋዮቹም ጌታ ከብዙ ጊዜ በኋላ ከሄደበት ተመልሶ የሰጣቸውን ገንዘብ ተሳሰበ። አምስት መክሊት የተቀበለውም፣ ሌላ አምስት ተጨማሪ መክሊት ይዞ በመቅረብ፣ ‘ጌታ ሆይ! አምስት መክሊት ዐደራ ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸውልህ አምስት ተጨማሪ መክሊት አትርፌአለሁ’ አለው።
“ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው። “እንዲሁም ሁለት መክሊት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸው ሁለት ተጨማሪ መክሊት አትርፌአለሁ’ አለው።
“ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው። “አንድ መክሊት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ ፈራሁህ፤ ሄጄም መሬት ቈፍሬ መክሊትህን ጕድጓድ ውስጥ ደበቅሁት፤ ገንዘብህ ይኸውልህ’ አለው።
“ጌታውም መልሶ፣ ‘አንተ ክፉ፣ ሰነፍ አገልጋይ፤ ካልዘራሁበት የማጭድ፣ ካልበተንሁበትም የምሰበስብ መሆኔን ታውቅ ኖሯል? ታዲያ፣ በምመለስበት ጊዜ ገንዘቤን ከነወለዱ እንዳገኘው ለለዋጮች መስጠት ይገባህ ነበር።
“ ‘በሉ እንግዲህ መክሊቱን ወስዳችሁ ዐሥር መክሊት ላለው ስጡ፤ ላለው ይጨመርለታል፤ የተትረፈረፈም ይኖረዋል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ይህን የማይረባ አገልጋይ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት’ አለ።
የእለቱ ቃለ እግዚአብሔር አስተንትኖ
በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ! ዛሬ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት አምልኮ አቆጣጠር ዘገብርኄር የተሰኘውን ሰንበትን እናከብራለን። ይህ ስደተኛው የዓብይ ፆም ሰንበት ዘግብርኄር ተብሎ የሚጠራበት ምክንያት በዚሁ ሰንበት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ከዋዜማው ጀምሮ “ገብርኄር ወገብር ምእመን ገብር ዘአሥመሮ ለእግዚኡ፣ ገብርኄር ወገብር ምእመን ዘበውሁድ ምእመን ኮንከ ዲበ ብዙኅ እሰይመከ...” (ጌታውን ያስደሰተ አገልጋይ ታማኝ እና ቸር አገልጋይ ነው፣ በጥቂቱ የታመንክ ቸር አገልጋይ ሆይ በብዙ እሾምሃለሁ፣ ጌታው የሚያገኘውና በገንዘቡ ሁሉ ላይ የሚሾመው ቸርና የታመነ አገልጋይ ማነው?) እየተባለ የሚዜምበት ሰንበት በመሆኑ የተነሳ ነው። በተጨማሪም እንደ እንደ ቸር አገልጋዮች እና በሰማይ ባለው መንግሥተ እግዚአብሔር እስከሚገቡ ድረስ ጌታቸውን ደጅ እንደሚጠኑ እንደ ክርስቶስ አገልጋዮች ሁኑ።ጹም ጸልዩ እንደ በጎ አገልጋዮች ለእግዚአብሔር ተገዙ እያለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የካህናትንና የምእመናንን የጽድቅ ሥራ በመልካም አገልጋይ ሥራ፣ የኃጥያንን የበደል ሥራ በክፉ አገልጋይ ሥራ እያመሳሰለ በወንጌል ያስተማረውን ትምህርት በአጠቃላይ ስለጻድቃንና አጥያን በምሳሌ የተናግረውን ቃለ ወንጌል እየጠቃቀሰና እያነሣሣ ስለሚዘመር ሰንበቱ ገብርሄር ተብሎ ተጠርቷል። ይህ ሰንበት የጻድቃን መታሰቢያ ሰንበት ነው።
በዛሬው እለት በተነበበው የመጀመሪያ መልእክት ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በርታ በማለት የምክር ቃሉን ሲለግሰው እናያለን (2ጢሞ 2፣ 1-15 )። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በርታ የሚለው በራስህ ኃይል በራስህ ጉልበት የነቃህ ወይም የበረታህ ሁን ለማለት ሳይሆን ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኘው ጸጋና ኃይል በርታ ማለቱ ነው።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን እንደሚቀበሉ ብርታትን እንደሚያገኙ ነግሮአቸዋል (ሐዋ. 1፣8) ስለዚህ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በርታ ሲለው ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኘው ጸጋና ከመንፈስ ቅዱስ በሚገኘው ኃይል ተንቀሳቀስ ማለቱ ነው። ይህ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠው ምክር ዛሬ ለእኔና ለእናንተም ያገለግላል የእኔ ማንነት ዕውቀቴም ይሁን ጥንካሬዬ ሁሉ የመጣው ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሚመነጭ ነፃ የጸጋ ስጦታ መሆኑን በመገንዘብ ዘወትር ለሱ ምስጋናና ውዳሴ ልናቀርብለት ይገባል።
በመቀጠልም ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ ወጣቶች እንዲሁም ጎልማሶች ለሽማግሌዎች እንዲታዘዙ ሁልጊዜም በትሕትና እንዲጓዙ ምክሩን ይለግሳል፣ ምክንያቱም ትሑት የሆነ ሰው አለኝ የሚለው ወይም የሚመካው በ1ኛቆሮ 15፡ 10 ላይ እንደምናገኘው በራሱ ጉልበትና አቅም ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር ጸጋና ከእርሱ ከሚያገኘው ኃይል ነው። ትሕትና ዋናው የሰይጣንን ባሕሪ ትዕቢትን አሽቀንጥሮ ለመጣል የሚያገለግል ዓይነተኛ መሣሪያችን ነው። በትሕትና የተሞላ ሰው ምንጊዜም ቢሆን ራሱን ዝቅ ለማድረግ አይከብደውም ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሰው እግዚአብሔርን ከፍ ያደርጋል ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሰው ደግሞ እግዚአብሔርን ዝቅ ያደርገዋል በዚህም ምክንያት በመጽሐፈ ምሳሌ እንደተጻፈው “ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሰው ካለበት ከፍታ ላይ እግዚአብሔር ራሱ ዝቅ ያደርገዋል” (ምሳሌ 3፡34) ይላል። ሰይጣን ከነበረበት ከከፍተኛ የመላእክት ማዕረግ የወረደው በትዕቢቱ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር ማስተካከል በመፈለጉ ነው አዳምና ሔዋንም ዋናው ኃጢአታቸው በትዕቢት እንደ እግዚአብሔር መሆን መፈለጋቸው ነው። ሌላው ትዕቢትን ማስወገጃ መሳሪያቸን በመጠን መኖር ነው በመጠን የሚኖር ሰው ራሱን በብዙ መልኩ ስለሚቆጣጠር ሰይጣን ወደ ውስጡ እንዲገባ ክፍተት አይፈጥርም በዚህ ሁኔታ ራሱን ከኃጢአት ምክንያት ሁሉ ያርቃል ማለት ነው። ሰይጣንን ለማሸነፍ በምናደርገው ትግል በምናደርገው ጾምና ጸሎት በምናደርገው ተጋድሎ ወደ ዘለዓለማዊ ክብሩ የጠራን አምላክ ራሱ ጸጋ ይሰጠናል ፍጹሞች ያደርገናል ያጸናናል ያበረታንማል።
በዛሬው እለት ስርዓተ አምልኮ ላይ የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል የመክሊቶችን ምሳሌ ይገልጽልናል (ማቴ. 25፡14-30)። አንድ ሰው ጉዞ ከመጀመሩ በፊት ለአገልጋዮቹ መክሊቶችን ሰጠ፤ በዚያን ጊዜ ዋጋ ያለው ሳንቲም ነበረ፤ ለእያንዳንዱ እንደ አቅሙ አምስት መክሊት ለሌላው ሁለት ለሌላኛው ደግሞ አንድ መክሊት ሰጠ። አምስት መክሊት የተቀበለው አገልጋይ ዘዴኛ የነበረ ሰው ነበረና ነገደበት ሌላ አምስት መክሊት አተረፈ። ሁለት የተቀበለው አገልጋይም እንዲሁ አደረገ እና ሌላ ሁለት አተረፈ። ሆኖም አንድ የተቀበለው አገልጋይ ጉድጓድ ቆፍሮ የጌታውን ሳንቲም ቀብሮ ደበቀ።
ጌታው ሲመለስ ይህ አገልጋይ ይህን ድርጊት የፈጸሙበትን ምክንያት ለጌታው ገለጸለት:- “ጌታ ሆይ፤ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ ፈራሁህ፤ ሄጄም መሬት ቈፍሬ መክሊትህን ጕድጓድ ውስጥ ደበቅሁት፤ ገንዘብህ ይኸውልህ’ አለው (ማቴ. 24፡ 24-25)። ይህ አገልጋይ ከጌታው ጋር የሚታመን ዝምድና አልነበረውም ነገር ግን ፈራው እና ይህም እንቅፋት ሆነበት። ፍርሃት ሁል ጊዜ አስሮ ሽባ አድርጎ የሚያስቀምጥ እና ብዙ ጊዜ ወደ መጥፎ ምርጫዎች እንድናመራ ይገፋፋናል። ፍርሃት ተነሳሽነትን እንዳይኖረን ያደርገናል፣ አስተማማኝ እና የተረጋገጡ መፍትሄዎች ውስጥ ቢቻ እንድንጠለል ያነሳሳናል፣ እናም ምንም ጥሩ ነገር እንዳናሳካ ያደርገናል። ወደ ፊት ለመራመድ እና በህይወት ጉዞ ላይ ለማደግ ፍርሃት ሊኖረን አይገባም እምነት ግን ሊኖረን ይገባል።
ይህ ምሳሌ የእግዚአብሔር እውነተኛ ጽንሰ-ሐሳብ እንዲኖረን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዳናል። እኛን ለመቅጣት የሚፈልግ ጨካኝ፣ ክፉ እና ቁጡ ጌታ ነው ብለን ማሰብ የለብንም። ይህ የተሳሳተ የእግዚአብሔር መልክ በውስጣችን ካለ ህይወታችን ፍሬያማ ሊሆን አይችልም ምክንያቱም በፍርሃት ውስጥ እንኖራለን እና ይህ ወደ ምንም ገንቢ ወደ ሆነ ሐሳብ አይመራንም። በተቃራኒው ፍርሃት ሽባ ያደርገናል፣ እራሳችንን ማጥፋት ያስከትላል። ስለ እግዚአብሔር ያለን አመለካከት ምን እንደሆነ ለማወቅ እንድናስብ ተጠርተናል። ቀድሞውንም በብሉይ ኪዳን ራሱን “እግዚአብሔር ርኅሩኅ ቸር አምላክ፣ እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ፣ ፍቅርን ለሺዎች የሚጠብቅ፣ ክፋትን፣ ዐመፅንና ኀጢአትን ይቅር የሚል፣መሐሪና ይቅር ባይ፣ ከቍጣ የራቀ ምሕረቱና ታማኝነቱ የበዛ” (ዘፀ 34፡6) በማለት ገልጿል። ኢየሱስም እግዚአብሔር ጨካኝ ወይም ክፉ መምህር ሳይሆን ፍቅር፣ ርኅራኄ፣ በጎነት የተሞላ አባት መሆኑን ሁልጊዜ አሳይቶናል። ስለዚህ፣ በእርሱ ላይ ትልቅ እምነት ሊኖረን ይችላል፤ ደግሞም ሊኖረን የገባል።
ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ልግስና እና እንክብካቤ በብዙ መንገዶች ያሳየናል፡ በቃሉ፣ በምልክቶቹ፣ ለሁሉም ሰው፣ በተለይም ለኃጢአተኞች፣ ለታናናሾች እና ለድሆች ባደረገው አቀባበል . . . ወዘተ። ነገር ግን ሕይወታችንን በከንቱ እንዳናባክን ፍላጎቱን በሚያሳየው ምክርም እንዲሁ ያደርጋል። በእርግጥም እግዚአብሔር ለእኛ ታላቅ ክብር እንዳለው የሚያሳይ ምልክት ነው፡ ይህ ግንዛቤ በድርጊታችን ሁሉ ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች እንድንሆን ይረዳናል። ስለዚህ የመክሊቶቹ ምሳሌ፣ “መክሊቱን ሳንቀብር”፣ ማለትም እግዚአብሔር የሰጠንን ስጦታዎች በቀጣይነት በአዲስ መልክ አዳዲስ መንገዶችን ለመምራት የሚያስችል የግል ሃላፊነት እና ታማኝነት ያስታውሰናል። ለዚያም እኛን ተጠያቂ ያደርጋል።
እግዚአብሔር የሰጠንን መክሊት እያዳበርን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ታማኝ ሆነን እንድንኖር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነቷ አይለየን።
ምንጭ፡ ሬዲዮ ቫቲካን የአማርኛ የስርጭት ክፍል
አዘጋጅ እና አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን