ብጹእ ካርዲናል አምቦንጎ በምስራቃዊ ዲ. ኮንጎ ውስጥ የሚደርሰው ጥቃት እየጨመረ መምጣቱ ያሳስባል አሉ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በዲሞክራሳዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኪንሻሳ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ፣ በምስራቁ የሃገሪቱ ክፍል በምትገኘው የሰሜን ኪቩ ዋና ከተማን ለከፍተኛ ጉዳት የዳረገው ብጥብጥ እየጨመረ መምጣቱን አስጠንቅቀዋል።
ካርዲናሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚስዮናውያን የዜና ወኪል ለሆነው ለፊደስ ኒውስ እንደተናገሩት “የኮንጎ ጦር በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ የተለይዩ አከባቢዎች ላይ ግጭቶች በመኖራቸው እና እነዚህን ግጭቶች ለማረጋጋት ሃይሉ በየቦታው ተበታትኖ ባለበት ወቅት ‘ኤም 23’ የተባለው ታጣቂ ቡድን የሃገሪቱን ሰፊ ግዛቱቶች መቆጣጠሩን ቀጥሏል” ካሉ በኋላ “በአሁኑ ሰዓት በጣም የሚፈራው በተለይም በጎማ ክልል፣ በአጠቃላይ በሀገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል የጸጥታ ችግር ሊያጋጥም ይችላል የሚል ነው” ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ከ2013 ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ በተከሰተው ከፍተኛ ግጭት ምክንያት ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ቤታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ በተደረገበት የምስራቃዊ ኮንጎ አካባቢን ከሚያዝያ 8 እስከ 10 2016 ዓ.ም. ድረስ ጎብኝተዋል።
ብፁዕ ካርዲናል አምቦንጎ በሚያዝያ ወር አጋማሽ ላይ በታተመ ሃዋሪያዊ መልዕክት ላይ “የቡካቩ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት በምስራቃዊ ዲሞክራሳዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ አሁናዊ እውነታ ላይ በጣም ግልጽ የሆነ ትንታኔ አቅርበዋል” በማለት ገልጸው፥ ቤተክርስቲያኒቷም ጭምር በዚህ አካባቢ አደገኛ ሁኔታ ላይ እንደሆነች አሳስበዋል። የብጹአን ጳጳሳትን አቋም ሲገልጹ “የቡካቩ ግዛት ጳጳሳት ልክ እንደ እኛ ማለትም በኮንጐ ጳጳሳት ጉባኤ በብሔራዊ ደረጃ የምንገኝ ጳጳሳት ሁሉ ሕዝቡን በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ እንኳን ከጎኑ ለመቆም ወስነዋል” ብለዋል።
ብጹእ ካርዲናሉ አክለውም እንደተናገሩት በዚህ አኳሃን እየተሰቃየ ላለው ህዝብ የምናደርገው ሃዋሪያዊ ጥበቃ “ለእነዚህ በስቃይ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች የእግዚአብሔርን ፍቅር እና ምህረት በጥቂቱ እንኳን እንዴት ማሳየት እንችላለን” የሚለውን መመለስ አለበት ካሉ በኋላ፥ “ያንን ነው ቤተክርስትያን ለማድረግ እየሞከረች ያለችውን፥ ነገር ግን ይህ ሁልጊዜ ቀላል ላይሆን ይችላል” በማለት ሃሳባቸውን ደምድመዋል።