አምስት ዓመታትን ያስቆጠረው የስሪላንካው የዕለተ ትንሳኤ ጥቃት እስከ አሁን ፍትህ አለማግኘቱ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ከአምስት ዓመታት በኋላ በስሪላንካ የትንሳኤ ዕለት የተፈጸመው የቦምብ ጥቃት ወንጀለኞቹ ለፍትህ እንዲቀርቡ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን የሚደረገው ጥሪ አሁንም እየተሰማ ቢሆንም፥ እስካሁን ድረስ ተሰሚነት እንዳላገኙ እና ምንም ዓይነት ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ተነግሯል።
ሚያዝያ 13 ቀን 2011 ዓ.ም. በክርስቲያን አምላኪዎች የታጨቁ ቤተክርስቲያናት ላይ እና በሦስት ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ላይ በትንሹ 290 ሰዎችን ለሞት የዳረገው እና በመቶዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ ያቆሰሉት የተቀናጁ ጥቃቶች ፍትህ እና እውነታው እንዲወጣ የሚጠይቁ የሲሪላንካ ህዝቦች ላይ ከፍተኛ ፍርሃትን አሳድረዋል።
ቆራጡ እና ደፋሩ የኮሎምቦ ብጹእ ካርዲናል ማልኮም ራንጂት እና የሲሪላንካ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አመራር ገለልተኛ የሆነ ምርመራ እንዲደረግ እና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጉዳዩ ላይ ተሳትፎ እንዲያደርግ ግንባር ቀደም ሆነው በጋራ ሲሰሩ ነበር።
በጣሊያን የቦሎኛ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ማትዮ ዙፒ በበኩላቸው ፍትህን ለማግኘት ለሚደረገው ትግል ድጋፍ እደሚያደርጉ ቃል በመግባት “ለፍትሕ በአንድነት መቆም” የሚለውን ጥሪ ተቀላቅለዋል።
የስሪላንካ ከተማ በሆነችው ኮሎምቦ የሚገኘው የማህበረሰብ እና የሃይማኖት ማእከል ዋና ዳይሬክተር አባ ሮሀን ሲልቫ የጅምላ ግድያው 5ኛ ዓመት ሊከበር ጥቂት ሳምንታት ሲቀረው፣ የጥቃቱ ሰለባዎችን በጣሊያን ከሚገኘው ሰፊ የስሪላንካ ማህበረሰብ ጋር አብሮ ለማስታወስ እና በዚያውም በደቡብ እስያ ደሴት ለምትገኘው ቤተክርስቲያን አጋርነታቸውን ላሳዩት ከብጹእ ካርዲናል ዙፒ ጋር ተገናኝተው ለመወያየት በጣሊያን ተገኝተዋል።
አባ ሲልቫ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስረዱት፣ በኮሎምቦ የሚመሩት ማእከል ሰብአዊ መብቶችን፣ ፍትህን እና ሰላምን ለማስፈን የሚያገለግል ሲሆን፥ በቦምብ ፍንዳታው ለተጎዱ ወገኖች፣ ለቤተሰቦቻቸው እና አጠቃላይ ለስሪላንካ ህዝብ ፍትህን ለማስፈን የሚሰራ ቡድን ያካተተ መሆኑን አስረድተዋል።
ፍትህን አላገኙም
የቦምብ ጥቃቶች ከደረሱ በኋላ ባሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ፍትህ ተግባራዊ እንዳልተደረገች ገልጸው፣ “ብዙ የምርመራ ሪፖርቶች እና ለዚሁ ጉዳይ የተዋቀሩ ኮሚሽኖች ቢኖሩም” ከጥቃቶቹ በስተጀርባ ያለው እውነት እና የሴራው ስፋት አሁንም ድረስ ድብቅ ሆኖ ሆኖ ቆይቷል።
ትጉሁ ካህን እንደተናገሩት በመንግስት ለተሰየመው ኮሚሽን የተሰጡትን የተለያዩ የምርመራ ውጤቶች፣ ከማላልጎዳ ሪፖርት እስከ በፓርላማ የተመረጠው ኮሚቴ ግኝቶችን ጨምሮ ለፕሬዚዳንታዊ ኮሚሽኑ የቀረቡ ቢሆንም፥ እነዚህ ሁሉ ጥረቶች ቢደረጉም በፖለቲካ ጣልቃገብነት እና ጥልቅ ምርመራ አለመኖር ምክንያት ፍትህ በፍፁም ሊገኝ እንዳልቻለ እንዲሁም ወንጀሎቹ ተሸፋፍነው እንደቀሩ ጠቁመዋል።
አብዛኛዎቹ የፓርላማ አባላት በሆኑበት ኮሚቴ የተደረጉት ሁሉም ምርመራዎች የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እና ግልጽነት የጎደላቸው ውንጀላዎች እንዲከሰቱ ምክንያት ሆኗል ሲሉ አባ ሲልቫ አስረድተዋል።
ከጥቃቱ በፊት በስለላ ኤጀንሲዎች የተሰጡ የመጀመሪያ ማስጠንቀቂያዎች ቢኖሩም መንግስት አደጋውን መከላከል ባለመቻሉ ላይ አወዛጋቢ ጥያቄዎችን ማስነሳቱ በብዙዎች ዘንድ የታወቀ ነው ብለዋል።
ከሪፖርቶቹ ጀርባ ያሉ ፖለቲካዊ ምክንያቶች
በጊዜው ጥቃቶች እንደሚከሰቱ የሚጠቁሙ ግልጽ ምልክቶች እንዳሉ በስለላ ድርጅቶች የተሰጡ ማስጠንቀቂያዎች ላይ ባለሥልጣናቱ ያሳዩት ቸልተኝነት እና ቆራጥ እርምጃ አለመውሰዳቸው በቃል ሊገለጽ አይችልም ሲሉ አባ ሲልቫ አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
“ፕሬዚዳንት ማይትሪፓላ ሲሪሴና መረጃው አልተነገረኝም ቢሉም፥ እኛ ግን ቀድሞ እንደተነገራቸው እናምናለን”
የቦምብ ጥቃቱ አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን ለስሪላንካ የማንቂያ ደወል ነው ያሉት አባ ሲልቫ በህብረተሰባችን ውስጥ ያሉ ተጋላጭ ሰዎችን ይበልጥ ያጋለጠ እና የአስተዳደር እና የጸጥታ ጉዳዮች አስቸኳይ ማሻሻያ እንደሚያስፈልጋቸው ያሳየ ነው ብለዋል።
“ጥቃቶቹ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በፖለቲከኞች ጎልተው ሲነገሩ እንደነበር እናውቃለን”
አባ ሲልቫ ቀጣይነት ባለው የኢኮኖሚ ፈተናዎች እና የፖለቲካ አለመረጋጋት ውስጥ፣ የፖለቲካ ግንኙነት ምንም ይሁን ምን ከገለልተኛ ወገን ነፃ የሆነ ምርመራ እና ተጠያቂነት እንዲኖር በሚደረገው ጥረት መጽናት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ፍትህን መሻት የሞራል ግዴታ ብቻ ሳይሆን የፈውስ እና የእርቅ መንገድ ነው ያሉት ካህኑ፥ በተቋማቱ ላይ የነበረውን እምነት ወደ ነበረበት ለመመለስ እና በስሪላንካ የተለያዩ ማህበረሰቦች መካከል አንድነትን ለመፍጠርም አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ወሳኝ ሚና
ካህኑ በቃለ ምልልሳቸው ወቅት ለፍትህ በመሟገት፣ በሃይማኖቶች መሃከል ውይይት እንዲኖር በማበረታታት እንዲሁም መከፋፈልን እና ሁከትን በመከላከል ረገድ ሰፊ ሥራ ይሰሩ በነበሩት በብጹእ ካርዲናል ራንጂት መሪነት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ያበረከተችውን ሚና አንስተዋል።
“ጭፍጨፋው ሲፈጸም አጠቃላይ በሀገሪቱ ደም መፋሰስ ይከሰት ነበር” ያሉት ካህኑ፥ ይህ የጥቃቱ አቀነባባሪዎች ፀረ ሙስሊም ስሜትን ለመቀስቀስ እና መራጮች እንዲመርጧቸው ተስፋ ካደረጉት ዓላማዎች አንዱ መሆኑን አስረድተዋል።
“ይህ እንዳይሆን ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ ብጹእ ካርዲናል ማልኮም ራንጂት ወደ ፊት በመውጣት በአካባቢው ከሚገኙት የሙስሊም መሪዎች ጋር በመነጋገር በማህበረሰባቸው ላይ ምንም እንደማይደርስ አረጋግጠውላቸዋል” ሲሉ ተናግረው፥ “እናም ከጅምላ ጭፍጨፋ በኋላ በሀገሪቱ ውስጥ ሁለተኛው ደም መፋሰስ እንዳይከሰት አድነዋል” በማለት የካርዲናሉን ወሳኝ ሚና ጠቅሰዋል።
በስሪላንካ ውስጥ በተለያዩ የእምነት ማህበረሰቦች መካከል ያለው ጥሩ ትብብር መቀጠሉን በመግለጽ፣ የፖለቲካ ጣልቃገብነት መከፋፈልን ሊፈጥር ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
“እንደ አለመታደል ሆኖ ያለው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት በህብረተሰቡ ውስጥ አላስፈላጊ መከፋፈል እንደሚፈጥር እና እነሱም (ፖለቲከኞቹ) በዚህ ሊጠቀሙ እንደሚችሉ እናያለን!”
አባ ሲልቫ ቡድናቸው ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ያደረገውን ጠቃሚ ትብብር እና ለፍትህ ፍለጋ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ያለውን ድጋፍ ጠቁመዋል። በተለይም በጄኔቫ ከሚገኘው የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ጋር ያለው ትብብር ለቡድናቸው ጥረት ወሳኝ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ለፍትህ መቆም
በሲሪላንካም ሆነ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የስሪላንካ ማህበረሰቦች ዘንድ ይህ አሰቃቂ ክስተት በየዓመቱ እንደሚታወስ እና እንደሚከበር አባ ሲልቫ በመግለጽ፥ ዓላማው “ሻማ ለማብራት ብቻ ሳይሆን ሰዎች ለፍትህ እንዲቆሙ መጋበዝ ነው” ብለዋል።
“ጥቃቱ በተፈፀመባቸው ቦታዎች አምባሳደሮች እና ሁሉም የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት ሻማ የማብራት እና ፍትህ ለማምጣት በጋራ ለመስራት ቃል የመግባት ሥነ ስርዓት ይካሄዳል” ያሉት ካህኑ በዕለቱ ሰልፍ እንደሚደረግ እና መንግስት ይህን ምርመራ በገለልተኝነት እንዲቀጥል ጥያቄ ይቀርባል” ብለዋል።
“እነሱ ጉዳዩ አልቋል ይሉናል... ግን አላለቀም፣ ይህንን እኛ እናውቃለን!” ሲሉ ተናግረዋል።
አባ ሲልቫ ሁሉም ሲሪላንካውያን በመሪዎቻቸው ላይ ጫና ማሳደራቸውን እንዲቀጥሉ ግብዣቸውን በድጋሚ በማቅረብ፥ መጋቢት 30 በጣሊያን ውስጥ ካገኟቸው ብጹእ ካርዲናል ዙፒ እና “ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሰዎች” ጋር ስላደረጉት ቆይታ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
“እርሳቸው (ካርዲናሉ) አቀባበል ካደረጉልን በኋላ የዚህ ትግል አካል በመሆናቸው ደስተኛ እንደሆኑ ገልፀው ፍትህን ለማስፈን በሚቻለው መንገድ ሁሉ እንደሚደግፉን ቃል ገብተውልናል” ሲሉ፥ በቅርብ ጊዜም ከብፁዕ ካርዲናል ራንጂት ጋር በኮሎምቦ የመገናኘት እቅድ እንዳለ እና ይሄም ግንኙነት የጣሊያን መንግስትን ድጋፍ እንደሚያመጣ ተስፋ እናደርጋለን በማለት ገልፀዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ዙፒ ሚያዝያ 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ሰለባዎቹን ለማስታወስ የሚደረገውን የመታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴ በቦሎኛ ካቴድራል ከስሪላንካ ማህበረሰብ ጋር አሳርገዋል።
“ይህ ለህዝባችን ትልቅ ድጋፍ እንደሚሆን እናምናለን፣ እንዲሁም ተመሳሳይ ድጋፍ ከሌሎች እንደሚመጣ እናምናለን”