የሆሣህና በዓል በእየሩሳሌም በሚገኙ ኢትዮጲያዊያን ክርስቲያኖች ዘንድ ሲከብር የምያሳይ ምስል የሆሣህና በዓል በእየሩሳሌም በሚገኙ ኢትዮጲያዊያን ክርስቲያኖች ዘንድ ሲከብር የምያሳይ ምስል   (AMIR COHEN)

ኢየሱስ በታላቅ ክብር ወደ እየሩሳሌም ገባ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ቀን እንደ ተራ ሰው ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ይገባ ነበር። በዚህ ቀን ግን የአይሁድ ንጉሥ ሆኖ በክብር ገባ። ከቢታንያ ተነሥቶ ደብረ ዘይት ሲደርስ ከሐዋርያቱ ሁለቱን ከቤተ ፋጌ (ከኢየሩሳሌም አጠገብ የምትገኝ) ሰው ተቀምጦባት የማያውቅ ውርንጭላ እንዲያመጡለት ላካቸው። «በፊታችሁ ወዳለችው ሀገር ሂዱና ሰው ተቀምጦባት የማያውቅ የአህያ ውርንጭላ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ። ባለቤቶቹ ቢጠይቋችሁ ጌታችን ፈልጓት ነው በሏቸው» (ማቴ.21፣1—17፣ ፣ማር.11፣1—15፣ ሉቃ.19፣29—44፣ዮሐ.12፣12—19) አላቸው።

ወደ ቤተፋጌም ሄደው አህያዪቱን አገኙአት። ሲፈቱአትም ሳለ ባለቤቶቹ መጡባቸውና አስቆሟቸው። እነርሱም ኢየሱስም እንደፈለጋት ነገሩአቸው። ባለቤቶቹ ይህንን ሲያውቁ ተውአቸው። ሐዋርያትም የአህያዪቱን ውርንጭላ ፈትተው ወደ ኢየሱስ ወሰዱ። አጠገቡም ሲደርሱ ልብሳቸውን በአህያዪቱ ውርንጭላ ላይ አንጥፈው ኢየሱስን አስቀመጡት።

«አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፤ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፤ እልል በዪ፤ እነሆ፤ ጻድቁና አዳኙ ንጉሥሽ፣ ትሑት ሆኖ፣ በአህያ ላይ ተቀምጦ፣ በአህያ ግልገል፣ በውርንጫዪቱ ላይ ሆኖ ወደ አንቺ ይመጣል” (ዘካሪያስ 9፡9) የሚለውን የዘካሪያስ ትንቢት ተፈጸመ። ሕዝቡም ኢየሱስ በመምጣት ላይ እንዳለ ሲያውቅ ሊቀበለው ወጣ። አንዳንዶቹ ያልፉበት በነበረው መንገድ ልብሳቸውን አንዳንዶቹ ደግሞ የዘንባባ  ዝንጣፊ ያነጥፉ ነበር። ከፊትና ከኋላ ያሉትን ደግሞ «ሆሣዕና በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፣ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ» እያሉ በታላቅ ድምጽ ይጮሁ ነበር። ኢየሱስ በሕዝቡ እልልታና ደሰታ ታጅቦ ሲገባ ተጠንቅቀው ይታዘቡትና ይመለከቱት የነበሩ ፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርቱን ዝም እንዲያሰኛቸው ተናገሩት። እርሱም ሕዝቡ ዝም ቢል ድንጋዮች እንደሚጮሁ አስታወቃቸው። ኢየሱስ ኢየሩሳሌምን ሲያያት አለቀሰላት። «አንቺ ኢየሩሳሌም ለሰላምሽ የሚያስፈልገውን ነገር ምነው አውቀሽ ቢሆን ኖሮ! አሁን ግን ይህ ነገር ከዓይንሽ ተሰውሮብሻል ጠላቶችሽ በዙሪያሽ እንደ አጥር ከብበው በዚህም በዚያም አንቺን የሚያስጨንቁበት ጊዜ ይመጣል… ምክንያቱም እግዚአብሔር ሊያድንሽና ሊጐበኝሽ የመጣበት ጊዜ ባለማወቅሽ ነው» እያለ ረገማት።

ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው ስለ ደኀንነቷ ሊያሳስታት ፈልጐ ነው። በማያወላዳ መንገድ ንጉሷና መድኃኒቷ እንደሆነ ገለጸላት። ወደ ራሷ ተመልሳ ጸጋዋን እንድትቀበል የልቧን ድንዳኔ ትታ እርሱን እንድትሰማ አስጠነቀቃት። ግን አልተጠነቀቀችም። ለጊዜው በክብር ተቀበለችው። ከጥቂት ቀን በኋላ ግን ተወችው፤ በመስቀል ላይ ሰቀለችው። የደኀንነቷን ቀን ማወቅ ተሳናት። በዚህም ደግሞ ከብዙ ዓመታት በኋላ መዓት ወረደባት።

ያቺን ውርንጭላ ፍቱልኝ እፈልጋታለሁ የተሰኘው መዝሙር

ይህ የሚያሳዝን የኢየሩሳሌም ሥራ የእኛም ሥራ ነው። ኢየሱስን መድኃኒታችንን መቀበል አንፈልግም ወይም ተቀብለን በኃጢአታችን ከእኛ እንዲርቅ እናደርገዋልን። በቅዱስ ቁርባን ወደ እኛ ሲመጣ በደስታ እንቀበለዋለን። ትንሽ ቆየት ብለን ደግሞ እናዋርደዋለን። ከእርሱ ጋር እንጣላለን። ከኃጢአት ጋር ጓደኝነት እንይዛለን። በኃጢአት ስንወድቅ እርሱን እንደገና እንሰቅለዋለን። ኢየሱስ እኛን «አቤት! በዚህ ቀን ለደኀንነት የሚደረገውን ብታውቅ ኖሮ …፣ ይህ ሁሉ ከዓይንህ ተሰውሮብሃል ማወቅን አልፈልግህም። ይህን እወቅ ግን አንድ ቀን…» እያለ አዝኖ ይፈርድብናል። ይህንን በማሰብ ሲመጣና ሲናገረን እምቢ አንበለው አናባርረው። በኋላ እርሱ ቂም ይዞ እንዳይለንና እንዳያባርረን ደኀንነታችንን ራሳችን አናጥፋት።

 

27 April 2024, 16:25