የእየሩሳሌም ከተማ ገጽታ የእየሩሳሌም ከተማ ገጽታ  

ጦርነቱ ከጀመረ 200 ቀናት በኋላ ከኢየሩሳሌም ፓትርያርክ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ

የእየሩሳሌም ፓትርያርክ የሆኑት ብጹእ ካርዲናል ፒዛባላ በጋዛ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በማስመልከት እንደተናገሩት ጦርነቱን ለማቆም የሁለቱ ሃገራት መንግስታት የጋራ መፍትሄ ብቻ እንደሚፈልግ በመግለጽ “ይህ ካልሆነ ከጦርነቱ ቀጣይነት በቀር ሁለቱ ሀገራት ሌላ አማራጭ ዬላቸውም” ብለዋል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“ጦርነቱ ከጀመረ ከ30 ቀናት በኋላ በህዳር ወር ላይ በጋዛ ውስጥ ተገናኝተን ሰፊ ውይይት ባደረግንበት ወቅት፥ ለግጭቱ መፍትሄ የሚሆን ነገር ሳይኖር ከ200 ቀናት በኋላ ራሳችንን እዚህ እንደምናገኝ በእርግጠኝነት አላሰብንም ነበር” ብለዋል የኢየሩሳሌም ፓትርያርክ ብጹእ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ የዓለም የ ‘ምድር ቀን’ (Earth Day) ዝግጅት ላይ።

ጥያቄ፦ በዚያ ቃለ መጠይቅ ላይ ስለሚከሰቱት ክስተቶች እና በትክክልም ያልተሳኩ ስለሚመስሉት “ተገናኝቶ መወያየት ስለሚቻሉባቸው መንገዶች” ሀዘንዎን ተናግረው ነበር

እንደ አለመታደል ሆኖ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ብዙ ነገር አልተቀየረም፡ ቀውሱ አሁንም ድረስ አለ። በዚያን ጊዜ ተስፋ አስቆራጭ በሚመስለው ነገር ላይ የተለወጠው የኛ (የኛን ስል የእኔ እና የምመራውን ማህበረሰብ ማለቴ ነው) የአመለካከት እይታ እና አስተሳሰብ ነው፥ እየቀጠለ ያለውን አሳዛኝ ሁኔታ ለመቋቋም ተስፋ እንዳንቆርጥ እና በዓይናችን ፊት እየደረሰ ያለውን አሳዛኝ ሁኔታ ለመታገስ ያለን ፍላጎት ነው፥ ጉዳቱ አንዳንድ ጊዜ በቀጥታ ብዙ ህዝቦቻችንን ይነካል። ያኔ በእውነት ደንግጠን ነበር። በዚህች ምድር ላይ ለ34 ዓመታት ኖሬአለሁ። አሁን እንደ ሃገሬ ነው የማየው፥ ጦርነትን፣ ኢንቲፋዳን (የ1973ቱን ፍልስጤማዊያን በእስራኤል ላይ ያደረጉት አመፅ) እና ብዙ ግጭቶችን አይተናል፥ ግን በጣም እርግጠኛ ነኝ - ይህ እስካሁን ካጋጠሙን ፈተናዎች በጣም ከባዱ ነው። አሁን ስለ ጦርነቱ እርግጠኛ አይደለንም፥ ይህ ጦርነት ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ አናውቅም። ምንም ነገር እንደበፊቱ አይሆንም። እኔ ስለ ፖለቲካ እያወራሁ አይደለም። ስለ እያንዳንዳችንን እያሰብኩ ነው። ይህ ጦርነት የሁላችንንም የህይወት አቅጣጫ ይለውጣል። ከዚህ ጦርነት ለማገገም ብዙ ጊዜ ይወስዳል። ግን ደግሞ እውነት ነው ረጅም ጊዜ እዚህ ተራ ነገር ነው - በመልካም ይሁን በመጥፎ ጊዜ ትዕግስት በጭራሽ አይሳሳትም። ይህ ባይሆን ኖሮ በተለያየ መልኩ ለ76 ዓመታት ሲካሄድ የነበረውን ጦርነት ማንም ማስረዳት አይችልም ነበር።

ጥያቄ፦ እርስዎም እንደተቀየሩ ይሰማዎታል?

እርግጥ ነው፣ ለምሳሌ ካለፈው ጊዜ በበለጠ፣ የማዳመጥ ፍላጎት እንዳለኝ ይሰማኛል። በወንጌል ብርሃን ዘመኑን እንዴት መረዳት እንዳለበት ማወቅ የእረኛው ተቀዳሚ ተግባር ነው። ይህ ደግሞ የሚሆነው በማዳመጥ ብቻ ነው የሚሆነው። በተጨማሪም ህዝቦቼም ይሁኑ ማንም ሰው የማዳመጥን ትርጉም እንዲረዱ እፈልጋለሁ። እያንዳንዱ ሰው የራሱ የሆነ ታሪክ፣ ህመም፣ ስቃይ አለው፥ሆኖም አለመደማመጥ፣ አለመረዳት፣ አለመጽናናት ባለመቻላችን ያሳዝናል። ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እዚህ አከባቢ የመጀመሪያው የበጎ አድራጎት ተግባር ማዳመጥ መቻል ነው። ገሊላ ወደሚገኘው ያፋ አን-ናሴሪዬ ለሃዋሪያዊ ጉብኝት ሄጄ የተመለስኩት በቅርብ ነው፥ ከህዝቦቼ በተጨማሪ የሌላ ሀይማኖት አባቶችን ማግኘት እፈልግ ነበር። ምክንያቶቻቸውን ያለ ቅድመ-ግንዛቤ ማዳመጥ ማለት የእነሱን ስቃይ መጋራት ማለት አይደለም። ግን በማንኛውም ሁኔታ በጣም አስፈላጊ ነው፥ ምክንያቱም ሰዎች መሪዎቻቸው እርስ በእርሳቸው እንደሚነጋገሩ ካዩ፣ ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ እና በመሃላቸው ያለውን አለመተማመንን ያስወግዳሉ።

የአይሁድ ፋሲካ አሁን ተጀምሯል፣ ረመዳንም በቅርቡ ነው ያበቃው። ሃይማኖታዊ በዓላት እርስ በርስ ለመተዋወቅ እና ወደ ውይይት ለመግባት በጣም ጥሩ አጋጣሚ ናቸው። በጣም ጥሩ የሆኑ ንግግሮች አያስፈልግም፥ የሚለያዩንን ግድግዳዎች ለማፍረስ በጋራ መብላት እና መጠጣት በቂ ነው። አንድ ላይ ሆኖ የሚበላ እራት ከኮንፈረንስ ወይም በሃይማኖታዊ ውይይት ከሚወጣ ሰነድ የበለጠ ብዙ ሊሠራ ይችላል። ከሚለያየን ይልቅ በጋራ ያለንን ለመረዳት መሞከር አለብን። በእርግጥ የጋራ መከራ አለብን። ግን መከራ ላይ ቆመን መቅረት ዬለብንም። ተስፋ ሊኖረን ይገባል፥ ይህ ማለት ስለ ወደፊት ሁኔታዎች ያለን ረቂቅ ጽንሰ-ሀሳብ ማለት አይደለም። ነገር ግን የማንነታችን ዋና ዋና ነገሮች የትኞቹ እንደሆኑ መረዳት ነው። እነዚህ ማንነቶች እንዴት አብረው እንደሚኖሩ እና እርስ በርስ ተስማምተው በሰላም አብሮ መኖር እንደሚቻል ለመረዳት ነው። ይህ ለሁሉም ይሰራል፥ ለእኛ ለክርስቲያኖችም ጭምር ነው። እኛም እንደ ክርስቲያን በዚህች ምድር እንዴት መኖር እንዳለብን እንደገና ማሰብ አለብን። ነገር ግን ተጨማሪ መረዳትም አለ ምክንያቱም ክርስቲያን መሆን ከሁሉም በላይ በወንጌል ተመስጦ የመኖር ዘይቤ ነው።

ጥያቄ፦ ይሄ ከባድ ቁርጠኝነት ይጠይቃል ብለው ያስባሉ?

በትክክል! ከባድ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል፥ ከሁሉም በላይ ደግሞ አድካሚ ነው። እራሳችንን እና እያንዳንዳችን በዚህ ጊዜ ውስጥ እንዴት እንደኖርን መጠየቅ እና ማወዳደር አድካሚ ነው። ምክንያቱም ህመም ብዙ ጊዜ “ብቸኛ” ያደርጋል። ያኔ የእኔን መከራ ሌላው ቶሎ ሊረዳ አይችልም፥ በማንኛውም ሁኔታ ከሌላ ሰው መከራ የሚበልጠው የእኔ መከራ ነው ብለህ ነው የምታስበው። ችግሩ እያንዳንዱ የሌላውን ስቃይ እንዲገነዘብ በማድረግ ይህንን ውይይት በማመቻቸት ላይ ነው። ግልጽ እናድርግና፣ ይህን የምለው እንደ ክርስቲያን “ሃይማኖተኛ” ሳይሆን ከዚህ የተሻለ ሌላ አማራጭ ስላላየሁ ብቻ ነው። ከዚህ አሳዛኝ አደጋ በሌላ መንገድ መውጣት እንችላለን? በዚች ምድር ቀደም ሲል አንዳንድ ደፋር ሰዎች ሰላማዊ የፖለቲካ መንገድን ሲሞክሩ ይታዩ ነበር። ነገር ግን ሁልጊዜ ከላይ ወደ ታች የወረዱ ሙከራዎች ነበሩ፡ ስምምነቶች፣ ድርድሮች፣ የዕርቅ ሃሳቦች ሁሉም ከላይ ወደ ታች ነው የተሞከሩት። ሁሉም በሚያሳዝን ሁኔታ አልተሳኩም። ለምሳሌ ኦስሎን እንውሰድ። ስለዚህ አቅጣጫውን ገልብጦ ከታች ወደ ላይ ጉዞ ለመጀመር ጊዜው አሁን ነው። እደግመዋለሁ፡ ያደክም ይሆናል ግን ሌላ መንገድ አላየሁም።

ጥያቄ፦ የእርስዎ ምልከታ የምዕራባውያንን የግጭት አተረጓጎም ይመለከታል?

በትክክል! ምክንያቱም ከዚህ ምድር ውጪ፣ በግጭት አተረጓጎም ላይ ዋልታ ረገጥ የሆነ ትርጉም ነው ያለው፥ ከጉዳቱ በተጨማሪ፣ ከግጭቱ በስተጀርባ ያሉት ምክንያቶች በጣም የተወሳሰቡ እና በአስርተ ዓመታት ውስጥ የተከማቹ ስለሆኑ እጅግ በጣም ሞኝነት ነው። የእስራኤል እና የፍልስጤም ግጭትን በእግር ኳስ ጨዋታ መንፈስ ማስተናገድ ስህተት ነው። በምዕራቡ ዓለምም እርስ በርስ መነጋገር፣ መወያየት፣ የስምምነት ሰነድ ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ለሰላም አጥብቆ ከመጸለይ በተጨማሪ ማለቴ ነው።

ጥያቄ፦ የሚመሩት ቤተክርስቲያንስ?

እርስ በርሳችን መነጋገርም በጣም ያስፈልገናል። ከመስከረም 26 በኋላ፣ የተለያዩ አመለካከቶች ነበሩ እና አሁንም አሉ። ምንም እንኳን በመሰረታዊነት የተለያዩ ቢሆኑም። እና እነሱን አንድ ላይ መጨፍለቅ ጊዜው አሁን ነው ብዬ አላስብም። ግን እንዚህን ለማዳመጥ ጊዜው አሁን ነው። እንዲሁም በተፈጠሩት የተለያዩ አመለካከቶች እና አቋሞች አውድ ውስጥም ቢሆን እንኳን ስለ እነሱ ለመናገር ጊዜው አሁን ነው። ምን ዓይነት የአስተሳሰብ ዘይቤዎች ይሄን እንዲሉ አነሳሳቸው የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ ድፍረት ይጠይቃል። እኛም እንደ ተለወጥን የመቀበል ድፍረት ይጠይቃል። እናም እንዴት እና ለምን እንደሆነ ለመረዳት ያስፈልጋል፥ ይህ ሂደት ቅዱስ ፍራንቺስኮ እንዳስተማረን በአእምሮ እና በልብ ግልጽነት ብቻ ሊሆን የሚችል ሂደት ነው። አእምሮ በራሱ በቂ አይደለም፣ ልብም ብቻውን በቂ አይደለም።ራሳችንን በተሻለ እና በእውነት መግለጽ የምንችለው ከሌላው ጋር ባለን ቅን ግንኙነት ብቻ ነው።

እኔን በግሌ የሚያሳትፍ ሂደት ነው። ማንም እንደዚያው የመቆየት ግምት ሊኖረው አይችልም። ከዚህ አንፃር፣ እኔ እንዳልኩት ከማንነታችን ውስጥ ከሕሊና ብቻ የሚወለድ፣ ሁልጊዜም ከእውነታው፣ ከተጨባጭ ተሞክሮ፣ ከተጨባጭ ልምዳችን የምንጀምርበትን ክርስቲያናዊ ትርክት መከለስ እንደሚያስፈልገን አምናለሁ። እምነት፣ በዋናነት በትንሳኤው ልምድ ላይ የተመሰረተ ተስፋ ነው። የማንነታችንን አወቃቀር ልንገልጸው የምንችለው የበለጸገውን ታሪካችንን መለስ ብለን በማየት ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያት በአብያተ ክርስቲያናት፣ በትምህርት ቤቶች፣ በሆስፒታሎች ግንባታ ውስጥ የእኛ መገኘት እውን ነው። ዛሬ እኛ የተጠራነው መዋቅሮችን ለመገንባት ሳይሆን ግንኙነቶችን ለማሻሻል ነው። እኛ የእነርሱ "ሌሎች" መሆናችንን በመረዳት "ከሌሎች" ጋር ያለን ግንኙነት (ይህ የሌሎችን ሃይማኖት ከማክበር ጋር በተያያዘ ነው) ነገር ግን በቅድስት ሀገር የካቶሊክ ማህበረሰብ ውስጥ ያለውን የበለጸገ ልዩነትን በተመለከተ፣ ሁልጊዜም የአረብ ክርስቲያኖችን ባህሪ እንደ ማይተካ ገጽታ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው።

ጥያቄ፦ ቁጥራቸው ትንሽ ቢሆንም፣ የክርስቲያን ማህበረሰቦች እርስዎን እንደ ጠንካራ እና ግንባር ቀደም መሪ አድርጎ ያዮታል፥ የሚያደርጉትን እያንዳንዱ ህዝባዊ ጣልቃገብነት ላይ ሁል ጊዜ ይወያያል፣ ይከራከራል እና ምናልባትም ከአንዱ ወገን ወይም ከሌላው ወቀሳ ይደርስበታል።

እውነት ነው፥ ከዚህ ጋር ብዙም የምለው ነገር የለኝም። ምናልባት ከአጠቃላይ ህዝቡ ከ2-3 በመቶ የሚሆነውን በቁጥር አናሳ ህዝብ የሚይዘው እና በማንኛውም ወገን ለመደራጀት የማይችል የመሆኑ እውነታ የበለጠ ከባድ ሸክም ይሰጠናል። በአብዛኛው የተመካነው ምንም እንኳን ትንሽ ብንሆንም፣ ዓለም አቀፋዊነትን እንደ ዋና ባህሪው ያደረገ ዓለም አቀፋዊ ተቋም አካል በመሆናችን ላይ ነው። ከዚህም በላይ፣ከሃይማኖታዊ እምነታቸው ራሳቸውን ችለው በሰብአዊነት እሴቶች የተዋቀሩ ናቸው።

ሁሌም ከሚሰቃዩት ጎን መሆናችን ይታወቃል። ለዚህ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ህያው ተምሳሌት ናቸው።

ጥያቄ፦ በእነዚህ ስድስት ወራት ውስጥየርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ያደረጉት የሰላም ጥሪ በቅድስት ሀገር ውስጥ እንዴ እየታየ ነው?

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በዚህ ጦርነት ወቅት የተናገሯቸው ቃላት እስካሁን ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል። ከሁለቱም ወገኖች ትችት በተሰነዘረባቸው ጊዜም እንኳ ቢሆን፣ ትልቅ ተጽዕኖ ነበራቸው። ለታጋቾች መፈታት እና በጋዛ ሰርጥ አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲደረግ የሰጠው ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ በዚህ ጦርነት ታሪክ ውስጥ በጉልህ ታይተዋል። ለማስታወስ የምፈልገው ምንም እንኳን ዛሬ ብዙዎች የተኩስ አቁም ጥሪ ቢያደርጉም፥ ጦርነቱ ከተጀመረ ማግስት ጀምሮ እሳቸው ብቻቸውን ሆነው በድፍረት የተኩስ አቁም ጥሪ ሲያሰሙ ነበር። ይህ ለወገኖቻችን እና ለጋዛ ክርስቲያኖችም ጭምር ነው። በየቀኑ ማለት ይቻላል በሚደረጉ የስልክ ጥሪዎች የተገኘው እፎይታ በጣም ትልቅ እና ከጋዛ ውጭ ሆነው እጣ ፈንታቸውን በጭንቀት ለሚጠብቁትም ትልቅ ጠቀሜታ ነበረው።

ጥያቄ፦ አሁን በደረሶት ዜና መሰረት በጋዛ ያሉ ክርስቲያኖች ሁኔታ ምን ይመስላል?

በምግብ የተሞሉ ሁለት የስብአዊ ዕርዳታ ኮንቴይነሮች ትላንት ጋዛ ደርሰዋል፥ በመጨረሻም ቢሆን ትንሽ የተሻለ ነገር ያገኛሉ፥ ለመላው ማህበረሰብ ጥቅም ሲባል ሁሉም ሰው በአንዳንድ ስራዎች መሳተፍ አለበት። ይህ አስፈላጊ ነገር ነው ምክንያቱም በዚህ መንገድ አሁን ስላሉበት ሁኔታ፣ ስለሚደርስባቸው አደጋ እና ስላለፉት ሰዎች ትውስታ ቋሚ እፎይታን ያገኛሉ። በቦምብና በጠመንጃ የተገደሉት ብቻ ሳይሆኑ ከመድኃኒትና እንክብካቤ እጦት ያልዳኑት እነማን ናቸው? አሁን በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ከ500 በላይ ሰዎች አሉ። የሶስት የማዘር ቴሬዛ እህቶች ድፍረት እና ትጋት በተለይ ልብ የሚነካ ነው። የአካል ጉዳተኛ ልጆችን መንከባከብ አላቆሙም። እነዚህን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በአካል አግኝተን የሚያስፈልጋቸውን ዕርዳታ ለማቅረብ በቅርቡ እንደምናገኝ ተስፋ አደርጋለሁ።

ጥያቄ፦ በእነዚህ 200 ቀናት ውስጥ በጣም አስቸጋሪዎቹ ጊዜያት ምን ምን ነበሩ?

የመጀመሪያዎቹ ቀናት በጣም አስደንጋጭ ነበሩ፥ በቅድሚያ ምን መሆን እንዳለበት ለይቼ ማወቅ አልቻልኩም ነበር፣ ምክንያቱም መጀመሪያ ላይ እየሆነ ያለውን ነገር እና ምን አይነት አሳዛኝ ሁኔታ በፊታችን እንዳለ እንኳን በትክክል መረዳት አልቻልንም። በዚያ ላይ የገና ጊዜ ነበር። የገና በዓል ደስታን ማጣት፣ ሰላምን ለማምጣት የተወለደው የክርስቶስ በዓል ለክርስቲያኖቻችን አስፈሪ ነበር። በተለይ ለልጆች፥ በገና በዓል ላይ የተከሰቱት የቤተልሔም የጥፋት ምስሎች በሚቀጥሉት ዓመታት በቀላሉ አይረሱም፥ የተደረገውን ማንኛውንም ነገር አልክድም። ስህተቶቹ እንኳን የእውነታው አካል ነበሩ። እንዲህ ባለው ውስብስብ ሁኔታ አንድ ሰው ስህተት መሥራት አይችልም፥ ግን አቋማችን ሁል ጊዜ ግልጽ፣ ንጹህ፣ እና ታማኝ ነበር ማለት እችላለሁ።

ጥያቄ፦ በእነዚህ ወራት ውስጥ የብቸኝነት ጊዜያት አጋጥሞዎታል?

ጸሎት ከብቸኝነት የሚያድን ታላቅ እፎይታ ነው፥ ምክንያቱም የጌታን ቋሚ መገኘት እንዲሰማህ ስለሚያደርግ ነው፥ እውነት ለመናገር አዎን እርግጥ ነው፣ ኃላፊነት ሲኖርብህ እና እነዚህ ሃላፊነቶች በአካባቢህ ባሉ ሰዎች ሕይወት ላይ በጣም ከባድ የሆኑ ተጽዕኖ በሚያሳድሩበት ጊዜ ብቸኝነትን ማስወገድ አይቻልም። የብዙ ጓደኞች ስጦታ አለኝ ነገር ግን የተወሰነ መለያየት በውሳኔዎቼ በስሜታዊነት እንኳን ቢሆን ተጽዕኖ እንዳላደርግ ይፈቅድልኛል። በዚህ አጋጣሚ ይህ ከቅዱስ ፍራንቺስኮስ አስተምህሮ የተዋስኩት ዘይቤ ነው።

ጥያቄ፦ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር ያለዎት የማያቋርጥ ግንኙነት ካለብዎት ኃላፊነት የሚመነጨውን ይህን ብቸኝነት ለማቃለል አስፈላጊ ነበር?

እርግጥ ነው! በጋዛ ያሉ ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆኑ ፓትርያርኩም ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ ንቁ ትብብር ተጠቃሚ ሆነዋል። እኔ የቤርጋሞ ከተማ ሰው ነኝ፥ ነገር ግን ለዚህ እና ለሰጡኝ አመኔታ ከልቤ ላመሰግናቸው እንደሚገባ ይሰማኛል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ወደ ማህበረሰቦቻችን መላክ የፈለጉት በቃላት የተደረጉ ቀረቤታ እና ፍቅር ብቻ ሳይሆን ብፁዕ ካርዲናል ክራጄቭስኪ፣ ፊሎኒ እና በቅርቡ ደግሞ ዶላን ባደረጉት ጉብኝት በቀጥታ ወደ እኛ የመጣው ተጨባጭ እርዳታ ነው።

አሁን ቅድሚያ የሚሰጠው የጦርነቱ ማብቃት ነው። ከዚያ በኋላ ግን በጋዛ፣ ፍልስጤም እና እስራኤል የበለጠ አስቸጋሪ ምዕራፍ ይጀምራል።

አዎን፣ ውጤቱ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል፥ ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ጋዛን ለቀው የሄዱት ተመልሰው መምጣት እንደሚችሉ ተስፋ አደርጋለሁ። ጋዛን እንደገና ለመገንባት አሥርት ዓመታት ይወስዳል። ምንም የቀረ ነገር የለም፥ ቤቶች፣ ጎዳናዎች፣ መሠረተ ልማት፣ ሁሉ ወድመዋል። ትልቅ ዓለም አቀፍ ጥረት ያስፈልጋል። ሰዎች በድንኳን ውስጥ ለዓመታት መተኛታቸው የማይታሰብ ነው። ግን እኔ እንደማስበው በአጠቃላይ ሁሉም ነገር እዚያ ብቻ ሳይሆን በፍልስጤም እና በእስራኤልም እንደገና ይመሰረታል፥ ሁሉንም ነገር በአዲስ እና በተለየ መሠረት እንደገና ለመጀመር ጊዜው አሁን ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በእነዚህ ስድስት ወራት ውስጥ የተከሰቱት ነገሮች በሙሉ፣ “የሁለት-ሃገራት መፍትሔ” አለመተግበሩን በግልፅ ያሳየ ይመስለኛል። ህለቱ ሃገራት ካልተስማሙ በስተቀር ጦርነትን ከመቀጠል ውጭ ሌላ አማራጭ የለም። ሁለቱ ሃገራት ከውስጥ መለወጥ አለባቸው፣ እራሳቸውን እንደገና ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው።

በቅርብ ዓመታት ውስጥ ሥር ነቀል እና ፈጣን ለውጦች ቢኖሩም፣ ሁለቱ ሃገራት ማህበረሰባቸውን እንደገና ለማሰብ ድፍረት ሊኖራቸው ይገባል፥ ሁለቱም ማህበረሰቦች እራሳቸውን በከፍተኛ ደረጃ ልዩነት ስለሚያሳዩ ይህ ቀላል ላይሆን ይችላል። ሁለቱም ማህበረሰቦች አዲስ የእሴቶች አድማስ ሊኖራቸው ይገባል ምክንያቱም የእያንዳንዳቸው ማህበራዊ ትሥሥር ከሌላው ይጠብቃል ተብሎ የማይታሰብ ነው። ይህን ካላደረጉ የወደፊት ሕይወታቸውን በእጅጉ ያበላሻሉ። በዓለም ዙሪያ በአሁኑ ጊዜ ጥሩ ከባቢ አየር የለም። በብዙ አገሮች ውስጥ መስመር የሳተ ጭንቀት፣ የማኅበረሰባዊ ትምክህተኝነት መጨመር፣ ግጭት የሚፈጥር የሥልጣን ጥማት እና ተገዥነት አለ። ይህ አይጠቅምም። ስሜታዊ ደጋፊ ልባል እችላለሁ፣ ነገር ግን የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ድምጽ ብቻ ከነዚህ ሁሉ ወደ ተቃራኒው አቅጣጫ ሲሄድ እሰማለሁ።

ጥያቄ፦ ፓትርያርኩ ከሁለቱም ወገኖች ተቋማት ጋር የግንኙነቱን ተግባር ያከናውናሉ፥ የፖለቲካ ሚና፥ ይህን እንዴት ያያሉ?

የፖለቲካ ሚና ስትል ምን ለማለት እንደፈለክ ላይ ይወሰናል። ቤተክርስቲያን የሽምግልና ሚና አትጫወትም፣ ተግባሯና ሥራዋ አይደለም። ይልቁንም ቤተክርስቲያን የማመቻቻ፣ ውይይትን የማመቻቸት እና የጋራ እውቅና ሚናን መወጣት ትችላለች። ይህንንም ከምንም በላይ የምናደርገው በህብረተሰቡ ውስጥ እና እንዲሁም በተቋማት መካከል እንደ ማህበረሰቡ መግለጫዎች ነው።

በእየሩሳሌም ላይ የሚበሩት የእስራኤል ወታደራዊ አውሮፕላኖች በሰሜን ወደሚገኘው “የግጭት መስመር” የሚያሰሙት ጩኸት ለአብዛኞቹ ንግግሮች መነሻ ሆኗል። ብጹእ ካርዲናል ፒዛባላ፣ የጵጵስና ቆባቸውን አስተካክለው ተነሱ። በገሊላ የሚገኙ የክርስቲያኖች ማህበረሰብ ይጠብቋቸዋልና።

 

 

25 April 2024, 18:13