ብጹእ ካርዲናል ፒዛባላ በጋዛ ውስጥ የሚገኘው የሆሊ ፋሚሊ ደብር ማህበረሰብ አባል ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ ብጹእ ካርዲናል ፒዛባላ በጋዛ ውስጥ የሚገኘው የሆሊ ፋሚሊ ደብር ማህበረሰብ አባል ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ 

የብጹእ ካርዲናል ፒዛባላ ጉብኝት በጋዛ ውስጥ ተስፋን፣ አንድነትን እና ድጋፍን ያመጣል ተባለ

የእየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብጹእ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ በእስራኤል ጦር የተከበበውን የጋዛ ሰርጥ በመጎብኘት ቤተክርስቲያን ለህዝቡ ያላትን ቅርበት ለማረጋገጥ ብሎም የአብሮነት እና የድጋፍ መልእክት አስተላልፈዋል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በጋዛ ከተማ የሚገኘው የሆሊ ፋሚሊ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሐሙስ ዕለት ከመስከረም 26 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከበባ ውስጥ ወዳለችው የጋዛ ሰርጥ መግባት በቻሉት በብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ በኩል የቤተክርስቲያንን አጋርነት፣ አንድነት እና የተስፋ መልእክት ተቀብለዋል።

የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ የማልታ ሉዓላዊ ግዛት የገዳም አለቃ ከሆኑት ከአባ አሌሳንድሮ ዴ ፍራንሲስ እና የጋዛ ደብር ካህን ከሆኑት ከአባ ጋብሪኤሌ ሮማኔሊ እንዲሁም ከተወሰኑ ልዑካን ጋር ሆነው ነበር ጋዛን የጎበኙት።

ተስፋ ፣ ትብብር ፣ ድጋፍ

በእየሩሳሌም የሚገኘው የላቲን መንበረ ፓትርያርክ በኩል በተለቀቀው መግለጫ እንደተገለጸው፣ ብጹእ ካርዲናሉ “በመከራ ውስጥ የሚገኙትን ሕዝብ ለማበረታታትና የተስፋ፣ የአብሮነት እና የድጋፍ መልእክት ለማድረስ ከህዝቡ ጋር ተገናኝተው ነበር” ብሏል።

መግለጫው ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ በቆይታቸውም የቅዱስ ፖርፊሪየስ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ጎብኝተው እንደነበር በመግለጽ፥ “ብፁዕነታቸው ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመሆን በሆሊ ፋሚሊ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተደረገውን ሥርዓተ ቅዳሴ አሳርገዋል” ብሏል።

በመግለጫው መሰረት የፓትርያርኩ የጋዛ ደብር ጉብኝት የመጀምሪያ ደረጃ የሆነውን የላቲን ፓትርያርክ እና የማልታ ሉዓላዊ ግዛት ከማልቴሰር ኢንተርናሽናል እና ከሌሎች አጋሮች ጋር በመተባበር በጋዛ ውስጥ ላሉ ሰዎች የሕይወት አድን ምግብ እና የሕክምና ዕርዳታ ለማድረስ ያለመ ነው ተብሏል።

ከመንበረ ፓትርያርኩ የተለቀቀው የቪዲዮ መልእክት እንደሚያሳየው ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ ‘በጋዛ የሚገኘውን የክርስቲያን ማኅበረሰብ መጥቼ ለማግኘት ፍላጎቱ ካደረብኝ ብዙ ጊዜ አልፏል፣ በመጨረሻም ይህንን እድል አግኝቻለሁ እናም በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ’ በማለት ነበር በጉብኝቱ መደሰታቸውን የገለጹት።

የጉብኝቱ ዓላማም “ከሁሉም ጋር መሆን፣ ማቀፍ እና መደገፍ፣ ያሉበትን ሁኔታ ማረጋገጥ፣ ሰዎቹን ለማሻሻል ምን መደረግ እንዳለበት ለመረዳት መሞከር ብሎም በሁሉም መንገድ እነሱን ለመርዳት መሆኑን” አብራርተዋል።

ብጹእ ካርዲናሉ በመቀጠል ሁሉም ክርስቲያኖች ‘የጋዛ የክርስቲያን ማህበረሰብ የሚያደርገውን ጸሎት’ እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ የማያቋርጥ አብሮነት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በጋዛ ለሚገኘው የሆሊ ፋሚሊ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ያላቸውን የማያቋርጥ ስጋት እና ጭንቀት በተደጋጋሚ ሲገልጹ እንደነበር፣ እንዲሁም የደብሩ ካህን ከሆኑት አባ ገብርኤል ሮማኔሊ እና ከደብሩ ምክትል አስተዳዳሪ አባ ዩሱፍ አሳድ ጋር በስልክ ይገናኙ እንደነበር ብጹእ ካርዲናሉ ገልጸዋል።

በእስራኤል እና በሃማስ ታጣቂዎች መካከል ያለው የትጥቅ ግጭት በአካባቢው መካሄድ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በየቀኑ ማለት ይቻላል ወደ ሰበካው ስልክ በመደወል ስለሁኔታው ለመጠየቅ እና የተስፋ ቃል እና ያላቸውን መንፈሳዊ ቅርበት ይገልጹላቸው እንደነበርም ተብራርቷል።

በጋዛ የሚገኘው የሆሊ ፋሚሊ ደብር

በ ‘ኢንስቲትዩት ኦፍ ዘ ኢንካርኔት ዎርድ’ በተባለ ተቋም ውስጥ በሚያገለግሉ ካህናት የሚመራው የሆሊ ፋሚሊ ደብር በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ያለ ብቸኛው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ነው።

በመላው ጋዛ እንደታየው ምዕመናኑ የምግብ፣ የውሃ እና የመድኃኒት እጥረት እና የከባዱ የክረምት ወቅት የማሞቂያ እጦት ተጋርጦባቸዋል።

ይህ ሁሉ ችግር ቢጋረጥበትም ትምህርት ቤቱን ጨምሮ የሚያስተዳድረው ይህ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ደብር በጦርነቱ ምክንያት ሁሉንም ነገር ያጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አስጠልሎ ማኖሩን ቀጥሏል።
 

17 May 2024, 14:55