2021.12.15 Gruppo di cristiani che pregano insieme davanti la Bibbia

እምነትህን በሚገባ ማወቅ ትፈልጋለህ?

አንዳንድ ጊዜ ስለ እምነትና ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ከጓደኞችህ፤ ከስራ ባልደረቦችህ፤ ከቤተሰቦችህ ጋር መወያየት ትፈልጋለህ ግን ቢጠይቁኝ ምን እመልሳለሁኝ? የሚል ስጋት ይከብሃል፡፡ እምነትህን ለሌሎች መመስከር ትፈልጋለህ ነገር ግን ፍርሃት አለብህ፤ ፍርሃትህ ከቤተክርስቲያን አስተምህሮ ጋር ያለህ ቁርኝት የሳሳ ከመሆኑ የመነጨ ነው፡፡ በማህበረሰቡ መካከል “እኔ ካቶሊክ ነኝ!” ብለህ ራስህን በይፋ ለመገለጽ ያሳፍርህና ያሰፈራህ ይሆናል፡፡ ዋናው ነገር የመጀመርያው መስመር ላይ የቀረበልህን ጥያቄ በሚገባ መመለስህ ነው፤ እምነትህን በሚገባ ማወቅ፤ ማድነቅ፤ መንከባከብና ለሌሎች በሙላት ማካፈል ትፈልጋለህ? መልስህ “አዎን እፈልጋለሁ” የሚል ከሆነ እነሆ እንጀምር፡፡

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ይህ የሕንፀት መርሐ-ግብር በአይነቱ ለየት ያለ ነው፤ በዚህ መርሐ-ግብር ውስጥ የምንነጋገረው እምነታችንን በሚመለከት ለሌሎች እንዴት አድርገን ማስረዳት እንደምንችል ነው፡፡ የምናምነውን ነገር ለማመን ምክንያታችን ምንድን ነው? ስለ ቤተክርሰቲያን፤ ስለ ስርዓተ-አምልኮ፤ ስለ አማላጅነት፤ ስለ መዳን፤ ስለ መፅሐፍ ቅዱስ፤ ስለ ሐጢአት፤ ስለ ፈውስ፤ በእምነት ብቻ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ስለመዳን፤ ስለ ምንኩስና ክህነታዊ ሕይወት ወ.ዘ.ተ... የሚነሱብንን ጥያቄዎች በምን መልኩ መመለስ አለብን? ለሚጠራጠሩ፤ በከፍተኛ ግራ መጋባት ውስጥ ለሚገኙ፤ በጭራሽ ሊያምኑን ለማይፈልጉ፤ ቀድሞ ካቶሊክ ለነበሩ እና አሁን ሌላ ቤተ-እምነት ለተቀላቀሉ፤ ከካቶሊክ ቤተክርሰቲያን ለመውጣት ጠርዝ ላይ ለደረሱ ሁሉ አሳማኝ መልስ መስጠት የምንችለው እንዴት ነው? በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ጠለቅ ያለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ፤ ታሪካዊ፤ ምክንያታዊ እና ማህበራዊ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

ይህንን ዝግጅት በድምጽ ለማዳመጥ ተጫወት የሚለውን ምልክት ይጫኑ

ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ እምነታችንን በሚመለከት ምን ማድረግ እንዳለብን በግልፅ ይነግረናል፡፡ ይህ አሁን የምንወስደው ስልጠና ሁሉ ፍፃሜ የሊቀ ሐዋርያት የቅዱስ ጴጥሮስ ሓሳብ ነው፡፡ ሐዋርያው እንዲህ ይላል፡-

“ዳሩ ግን ጌታ ክርስቶስን በልባችሁ ቀድሱት፤ በእናንተ ስላለው ተስፋ ምክኒያት ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን በየዋህነት እና በፍርሃት ይሁን” (1 ጴጥ 3፡15)

በዚህ ቃል በመመስረት ካቶሊካዊ እምነታችንን በሚመለከት ለሚነሱብን ማናቸውም አይነት ጥያቄዎች በጨዋነት እና በየዋህነት ለሁሉም ተገቢ የሆነ መልስ መስጠት አለብን፡፡ ይህንን ዓይነት ዝግጁነት እንዲኖረን ከሁሉ በፊት እኛ በበቂ ደረጃ መታነጽ ይገባናል፡፡ መጽሐፍ እንደሚያስተምረው ሰው የሚናገረው ከልቡ ሞልቶ የተረፈውን ነው፡፡

ስለ እምነትህ መልስ ለመስጠት በርካታ መጽሐፍትን ማንበብ፤ መልዕልተ ባሕርያዊ የሆነ ዕውቀት፤ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ አይነት የስብከት ችሎታ ወ.ዘ.ተ. አያስፈልግህም፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመረጣቸው እና ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት የላካቸው ሐዋርያት ልክ እንደ እኛ ተራ ሰዎች እንደነበሩ አስታውስ፡፡ ስለክርስትናህ ለመመስከር ተጠርተሃል፡፡ ዋናው ነገር ስለ እግዚአብሔር ቃል ሚዛናዊ የሆነ ግንዛቤ ያለህ መሆኑ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስን ማወቅ ያስፈልግሃል፡፡ ስለምታምነው ነገር ለሌሎች ማስረዳት ግዴታህ ነው፤ የክርስትና ትምህርት ያልሆነውን አስተሳሰብ ምክንያታዊ በሆነ ወንድማዊ ውይይት ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲመለስ መጣር አለብህ፡፡ ይህንን ስታደርግ ግን ጨዋነት መታወቂያህ ይሁን! ምንም ጊዜ ቢሆን የተሳሳተውን አመለካከት በገርነት ለማቅናት መሞከር እንጂ ግለሰቡን ማሳዘን አይገባም፡፡ የዋንጫውን ዝገት ለማስለቀቅ ዋንጫውን በምትፍቅበት ጊዜ ዋንጫው ራሱ እንዳይሰበርብህ ተጠንቀቅ፡፡ ለዚህ ሁሉ ስራ አንተ አስቀድመህ መዘጋጀት አለብህ፡፡

ምንጭ፡ “የእምነት ቀናኢነት፣ ካቶሊካዊት እምነትን ማወቅ፣ መጠበቅ እና መንከባከብ፥ ካቶሊካዊ እምነታችንን ለሌሎች ማካፈል” በሚል አርዕስት የአዲስ አበባ ካቶሊካዊ ሰበካ የሐዋርያዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በ2010 ዓ.ም ካሳተመው መጽሐፍ ከገጽ 3-4 ላይ የተወሰደ።

 

16 May 2024, 16:20