በጋዛ የሚገኘው የሆሊ ፋሚሊ ቤተክርስቲያን ካህን ወደ ደብራቸው በመመለሳቸው በጣም መደሰታቸውን ገለጹ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. የእስራኤል-ሃማስ ግጭት ከተጀመረ ጀምሮ አባ ገብርኤል ሮማኔሊ በጋዛ ከተማ ወደምትገኘው የሆሊ ፋሚሊ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ወደ ሆነችው ሰበካቸው አልተመለሱም።
አባ ገብርኤል ከእስራኤል ወደ ጋዛ መስከረም 25 ላይ ሊደረርጉት የነበረው ጉዞ በአንድ ቀን በመራዘሙ ብቻ መስከረም 26 የእስራኤል-ሀማስ ግጭት ተከስቶ ወደ ደብራቸው መመለስ አልቻሉም ነበር።
የ ‘ኢንስቲትዩት ኦፍ ኢንካርኔትድ ዎርድ’ የተባለው የካቶሊክ ተቋም አባል ካህን የሆኑት አባ ገብርኤል ወደ ጋዛ መመለስ የቻሉት በኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ከግንቦት 8 እስከ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ በአከባቢው ባደረጉት ጉብኝት ወቅት ነው።
የመመለስ ደስታ
በእነዚህ የጦርነት ወራት ጋዛ ወደ ፍርስራሽ ክምርነት ተቀይራለች፣ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ሰብአዊ አደጋ በርካቶችን በተለይም ህጻናትን ገድሏል። በርካቶች በጉዳት ብቻ ሳይሆን በውሃ ጥም እና በተመጣጠነ ምግብ እጦት ህይወታቸውን አጥተዋል።
አባ ሮማኔሊ ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ “ብጹእ ካርዲናል ፒዛባላ በደንብ የሚያውቁትን ደብር እንዲሁም እዛ የሚገኙ ቤተሰቦችን ለመጎብኘት ችለዋል፣ በጉብኝታቸው ወቅትም የበርካታ የካቶሊክ እና የኦርቶዶክስ ቤተሰቦችን ቤት ጎብኝተዋል፥ በዚህም ጌታ እጅግ በጣም ብዙ በረከትን ሰጥቶናል” ብለዋል።
አባ ሮማኔሊ ከፓትርያርኩ ልዑካን ጋር መመለስ በመቻላቸው “ታላቅ ደስታ” እንደተሰማቸው ተናግረው “አሁን በቁምስናዬ ውስጥ ነው ያለውት፥ እዚህም እቆያለሁ” ሲሉ ቃል ገብተዋል።
ሌላኛው የ‘ኢንስቲትዩት ኦፍ ኢንካርኔትድ ዎርድ’ ካህን የሆኑት አባ ካርሎስ ፌሬሮ እና የአንድ ሃይማኖታዊ ቤተሰብ መነኩሲት አባ ሮማኔሊ ወደ ጋዛ ሲመለሱ አብረዋቸው ነበሩ።
ጥፋት ቢኖርም የመንፈስ እርካታ ማግኘታቸው
በጋዛ ውስጥ ያለው ጥፋት እና ጉዳት አንዳንድ ጊዜ የአከባቢው ሰዎች በሚያሳዩት መረጋጋት ቀንሰው ይታያሉ። አባ ሮማኔሊ ስለሁኔታው ሲያብራሩ “ሁኔታው ውስብስብ ነው፥ በብዙ ምእመናኖቻችን መካከል መረጋጋት አለ፥ በእውነቱ እጅግ በጣም ብዙ ስቃይ ቢኖርባቸውም፣ በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ በመቆየት እራሳቸውን በጌታ እጅ ውስጥ ያደርጋሉ። እርግጥ ነው፣ ወደፊት ምን እንደሚሆን በጣም ያሳስባቸዋል፥ አንዳንዶቹ ታመዋል፣ አንዳንዶቹ ቆስለዋል፣ ብዙዎች ለቀው ሄደዋል፣ የተወሰኑት ደግሞ ለመውጣት እያሰቡ ነው፥ ነገር ግን እጅግ በጣም ብዙዎቹ እዛው ለመቆየት አስበዋል” በማለት ገልጸዋል።
ካህኑ ከቁምስናው ምእመናን ጋር በመሆን የቀሩትን ለመርዳት የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ቆርጠዋል።
እስካሁን በሆሊ ፋሚሊ ግቢ ውስጥ የተጠለሉ 500 ክርስቲያኖች እንዳሉ እና የእማሆይ ቴሬዛ እህቶችም እነሱን ለመርዳት እዛው እንደሚገኙ ብሎም የእነርሱ እርዳታ ለጎረቤት ሙስሊሞችም እንደሚደርስ ተናግረዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ድጋፍ
የክርስቲያኖቹ ቁርጠኝነት የሚካሰው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የማያቋርጥ ድጋፍ ነው። ይሄንንም በማስመልከት አባ ሮማኔሊ “ቅዱስ አባታችን የመጽናኛ ቃላትን እና የበረከቱን ቃል ሊሰጡን በየእለቱ ይደውላሉ” ካሉ በኋላ “ህዝቡን እንድንጠብቅ ይጠይቁናል፣ ሁልጊዜም ጠንክረን እንድንቆይ ያበረታቱናል” ብለዋል።
የደብሩ ካህን በማከልም “ሰላም በፍልስጤም እና በእስራኤል ላይ እንዲነግስ እንዲሁም የማይቻል ቢመስልም ለፍትህ እና ለሰላም የመጀመሪያ እርምጃ እንዲሆን አስፈላጊ የሆነውን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲሳካ ቸሩ አምላክ እንዲያግዛቸው እንጸልያለን” ብለዋል።
አባ ገብርኤል ሮማኔሊ በመጨረሻም “የሰብአዊ እርዳታ ሊደርስ ይችላል፣ ታግተው የነበሩ እና ነፃነታቸውን የተነፈጉ ሁሉ ይፈታሉ፣ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የተጎዱ ሰዎች ህክምና ሊያገኙ ይችላሉ” በማለት ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።