የኤማሁስ መንገደኞች ከኢየሱስ ጋር በተገናኙበት ወቅት የኤማሁስ መንገደኞች ከኢየሱስ ጋር በተገናኙበት ወቅት  

የግንቦት 11/2016 ዓ.ም ዘትንሣኤ 3ኛ ዕለተ ሰንበት ቅዱስ ወንጌል እና አስተንትኖ

የዕለቱ ምንባባት

1.     2ቆሮ 5፡ 11-21

2.     2ጴጥ 3፡14-18

3.     ሐዋ 21፡ 31-40

4.     ሉቃ 24፡ 13-35

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

በኤማሁስ መንገድ ላይ

በዚሁ ቀን ከደቀ መዛሙርት ሁለቱ፣ ከኢየሩሳሌም ዐሥራ አንድ ኪሎ ሜትር ያህል ወደሚርቅ፣ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር፤ እነርሱም ስለ ሆነው ነገር ሁሉ እርስ በርስ ይነጋገሩ ነበር። እየተነጋገሩና እየተወያዩ ሳሉም ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ጀመር፤ ነገር ግን እንዳያውቁት ዐይናቸው ተይዞ ነበር።

እርሱም፣ “እየሄዳችሁ፣ መንገድ ላይ እርስ በርስ እንዲህ የምትወያዩት ምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱም በሐዘን ክው ብለው ቆሙ። ከእነርሱም አንዱ፣ ቀለዮጳ የተባለው፣ “በእነዚህ ቀናት እዚህ በኢየሩሳሌም የሆነውን ነገር የማታውቅ፣ አንተ ብቻ ለአገሩ እንግዳ ነህን?” ሲል መለሰለት።

እርሱም፣ “የሆነው ነገር ምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “በእግዚአብሔርና በሰው ሁሉ ፊት በተግባርና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ ነው፤ እርሱን የካህናት አለቆችና ገዦቻችን ለሞት ፍርድ አሳልፈው ሰጡት፤ ሰቀሉትም። እኛ ግን እስራኤልን ይቤዣል ብለን ተስፋ ያደረግነው እርሱን ነበር፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው። ደግሞም ከእኛው መካከል አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤ እነርሱም ማልደው ወደ መቃብሩ ሄደው ነበር፤ ሥጋውንም ባጡ ጊዜ መጥተው እርሱ በሕይወት እንዳለ የነገሯቸውን መላእክት በራእይ እንዳዩ አወሩልን። ከእኛም መካከል አንዳንዶች ወደ መቃብሩ ሄደው፣ ልክ ሴቶቹ እንዳሉት ሆኖ አገኙት፤ እርሱን ግን አላዩትም።”

እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የማታስተውሉ ሰዎች፣ ልባችሁም ነቢያት የተናገሩትን ሁሉ ከማመን የዘገየ፣ ክርስቶስ ይህን መከራ መቀበልና ወደ ክብሩም መግባት አይገባውምን?” ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እርሱ የተጻፈውን አስረዳቸው።

ወደሚሄዱበትም መንደር በተቃረቡ ጊዜ፣ ኢየሱስ አልፎ የሚሄድ መሰለ። እነርሱ ግን፣ “ምሽት እየተቃረበ፣ ቀኑም እየመሸ ስለ ሆነ ከእኛ ጋር እደር” ብለው አጥብቀው ለመኑት፤ ስለዚህ ከእነርሱ ጋር ለማደር ገባ። አብሮአቸውም በማእድ በተቀመጠ ጊዜ እንጀራውን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ሰጣቸው። በዚህ ጊዜ ዐይናቸው ተከፈተ፤ ዐወቁትም፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ። እነርሱም፣ “በመንገድ ሳለን፣ እያነጋገረን ቅዱሳት መጻሕፍትንም ገልጦ ሲያስረዳን፣ ልባችን እንደ እሳት ይቃጠልብን አልነበረምን?” ተባባሉ።

በዚያኑም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዐሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም በዚያ በአንድነት ተሰብስበው አገኟቸው፤ “እነርሱም ጌታ በእርግጥ ተነሥቶአል! ለስምዖንም ታይቶአል” ይባባሉ ነበር። ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም በመንገድ ላይ የሆነውንና ኢየሱስ እንጀራውን በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንዳወቁት ተረኩላቸው።

 

የእለቱ አስተንትኖ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ! ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር የትንሣኤ ሦስተኛ  የተሰኘውን ሰንበትን እናከብራለን።

በዚህም ዕለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሕይወታችን እንዲቀደስና በበረከቱም እንዲጠግብ ሕይወታችንን ለማስትካከልና በትክክለኛ መንገድ ለመምራት በኑሮአችን በአካሄዳችን እውነተኛ ክርስቲያኖች ሆነን የእርሱን አቅጣጫ የእርሱን ፈለግ በሙላት መከተል እንድንችል በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባት አማካኝነት ወደ እኛ ወደልጆቹ ይመጣል በዚሁም መሠረት እንግዲህ ቅድስት ቤተክርስቲያን በዚህ ሰንበት እንድናነባቸው እንድናስተነትንባቸው የዕለቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባት ወደ እኛ ታደርሳለች።

በዛሬው በመጀመሪያ ንባብ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በሁለተኛው መልዕክቱ ለቆሮንጦስ ሰዎች በእነሱም በኩል አድርጎ ሁላችን በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ አምነን ለተጠመቅን ሁሉ በውጫዊና ዓለማዊ ነገር ወይንም ደግሞ በጊዜያዊ ነገር ላይ እምነታችንን አንዳናስቀምጥ ይመክረናል። በሚታየውና በሚያምረው ገፅታችን ወይንም በመልካችን ሳይሆን እምነታችን ሁሌም በማይታየው ልባችን ባለው በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በእርሱና በእርሱ ላይ ብቻ ሊሆን እንደሚገባ ይነግረናል። ምክንያቱም እርሱ የሌለበት ሕይወት የተሟላ ሕይወት ሊሆን አይችልም እርሱ የሌለበት ሥራ የሰመረ ሥራ ሊሆን አይችልም እርሱ የሌለበት እርምጃ የተቃና እርምጃ ሊሆን አይችልም እርሱ የሌለበት ዕረፍት ሰላማዊና የተረጋጋ ዕረፍት ሊሆን አይችልም እርሱ የሌለበት ትዳር እርሱ የሌለበት ቤተሰብ በይቅርታና በመተሳሰብ ላይ የተመሠረተ እውነተኛ ፍቅርን የሚንፀባርቅ ትዳር ወይንም ቤተሰብ ጉዞ ሊሆን አይችልም።

ስለዚህ እውነተኛ መመኪያችን እውነተኛ ማረፊያችን የአብ አንድያ ልጅ የሆነው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። የሰማይና የምድር ፈጣሪ የነገሮችና የጊዜያት ሁሉ ባለቤት እርሱ ነው። እርሱ ጊዜን ካልሰጠ እርሱ ሕይወትን ካልሰጠ እርሱ ማስተዋልን ካልሰጠ ሁሉም ከንቱ ነው። ቅዱስ ዳዊት በመዝሙር 21፡1 እንዲህ ይላል እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል ይላል።

ስለዚህ ይህንን እውነታ በመረዳት ከሁሉ ነገር ይልቅ ቅድሚያ ለእርሱ መስጠት ግድ ይለናል። በተለይም ደግሞ በዐሥርቱ ትዕዛዛት ላይም ሰፍሮ እንደምናገኘው በሰንበት ቀን የአንድ ክርስቲያን ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን የሚገባው ወደ ቤተክርስቲያን በመሔድ እግዚአብሔርን ስለሰጠው መልካም ነገር ሁሉ እርሱን ማመስገን ነው። እግዚኣብሔር ለኛ ከሰጠን ነገር አንፃር ሲታይ የእኛ በሰንበት ቀን ለእርሱ ቅድሚያ መስጠት ከምንም ነገር የሚቆጠር አይደለም። ሁላችንም እንደምናቀው እግዚአብሔር ፍጹም አምላክ ነው የእኛ እርሱን ማመስገን በእርሱ ላይ የሚጨምረው ወይንም ደግሞ የሚቀንሰው ነገር የለም። ይልቁንም እኛ ከእርሱ ከሚመጣ ጸጋና በረከት ከእርሱ ከሚመጣ አባታዊ ቡራኬ ከእርሱ ከሚመጣ አምላካዊ ጥበቃ ተካፋዮች እንሆናለን።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን ነገር በመረዳቱ ይመስላል ራሱን ሙሉ በሙሉ ለጌታችን እየሱስ ክርስቶስ አሳልፎ ሰቷል ፣ አስገዝቷል። ይህንን በመመልከት የቆሮንጦስ ሰዎች አብዷል ራሱን ስቷል በማለት አሉባልታ ሲሰነዝሩበት ሰምተናል ነገር ግን ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ሲመልስላቸው ይህ ያላችሁትን ብሆንም እንኳን ስለ እርሱ ፍቅር ስል ነው ይል ነበር።

ሰዎች ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን በተለያየ መንገድ እንደተቃወሙት ሥሙን እንዳጠፉት እንዲሁ ደግሞ ለሐዋርያት ተመሳሳይ ነገር እንዳደረጉባቸው ዛሬም ለእኛ ተመሳሳይ ነገር ያደርጉብን ይሆናል ነገር ግን ይህ ሁሉ በክርስትና የእምነት ጉዞአችን ይበልጥ እንድንጠነክር ብሎም ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለንን መቀራረብ እንድናጎለብት ልዩ አጋጣሚ ይፈጥርልናል።

ይህንን ካደረግን ይላል ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በሁለተኛ መልዕክቱ የአዲሲቷ ምድር የአዲሲቷ ሰማይ እጩዎች ነን ይላል ምክንያቱም በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጸጋ አድገናልና እርሱም ማን እንደሆነ በሚገባ ተረድተናልና በማለት ይጠቅሰዋል።

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን አውቀናል እርሱን በሚገባ ተረድተናል ብለን ስንናገር ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በዛሬው መልዕክቱ ራሳችንን ሙሉ በሙሉ ለእርሱ አስገዝተናል የራሳችንን ፈቃድ በመተው የእርሱን ፈቃድ ለመፈጸምና ለእርሱ ፈቃድ ሙሉ በሙሉ ተገዢ ሆነናል ማለታችን ነው። ይህንን በማድረጋችን ደግሞ ክርስቶስ ወደደረሰበት ወደ ዘለዓለማዊ ክብር ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት እንሸጋገራለን። የዕለቱ የሐዋርያት ሥራ ንባብም ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን መከተል በእርግጥ ብርቱ ጥንካሬና ብርቱ ተጋድሎ እንደሚያስፈልግ ይነግረናል። ሐዋርያቶችም ሆኑ ቅዱሳን ሰማዕታት ይህንን ጉዞ በማድረጋቸው የመስቀሉ ጉዞ ተካፋዮች በመሆናቸው ዛሬ በታላቅ ክብርና ሞገስ በእግዚአብሔር ፊት ይገኛሉ።

በዛሬው ዕለት የሰማነው የሉቃስ ወንጌልም የሚያተኩረው በተመሳሳይ ሓሳብ ነው ይኸውም የእግዚአብሔርን ቃል በታላቅ ማስተዋልና በታላቅ ቅንነት ልንመለከተው በታላቅ ቅንነት ልናዳምጠው እንደሚገባ ይነግረናል።

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የኤማሁስ ተጓዦችን በመንገዳቸው ተገልጾ ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ያለውን እየጠቀሰ ቢያስረዳቸውም አንድ ጊዜ መንፈሳዊ ዓይናቸው ታውሯልና በፍጹም ማን እንደሆነ ሊያውቁት አልቻሉም። ምን አልባት ይህ ተመሳሳይ ሁኔታ በእኛም ሕይወት ውስጥ ብዙ ጊዜ ያጋጥም ይሆናል። ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጋር አብረን እየተጓዝን ከማን ጋር እየተጓዝን እንዳለ የማንረዳበት አጋጣሚ ሊከሰት ይችላል። እነዚህ ሁለቱ የኤማሁስ ተጓዦች በውስጣቸው ከተፈጠረ ፍርሃት አንፃርና ከእምነታቸው አለመጠንከር የተነሣ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን እንዳላወቁት ሁሉ ዛሬ እኛም ከእርሱ ጋር አብረን ብንጓዝም ሙሉ እምነታችንን በእርሱ ላይ ካላስቀመጥን ፍርሃት ወደውስጣችን ይገባል ይህ ፍርሃትም ጥርጣሬንና የመሳሰሉትን ሁሉ በውስጣችን በማሳደር አብረነው የምንጓዘውን ክርስቶስን በሙላት እንዳንረዳ ይጋርደናል። በምስጢራት አማካኝነት የምንቀበለውን ክርስቶስን በሙሉ ልባችን እንዳንረዳ ይሆናል በስተመጨረሻም ከመንገዳችን ያሰናክለናል።

እነዚህ የኤማሁስ ተጓዦች በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሞት ልክ እንደሌሎቹ ደቀመዝሙሮች ተስፋ ቆርጠው ነበር ነገር ግን በስተመጨረሻ እርሱ መሆኑን ሲያውቁ ተስፋቸው ለመለመ የደከመ ሰውነታቸውም ጉልበትን አገኘ ስለዚህም በወንጌሉ ሲነበብ እንደሰማነው በዚያችም ሰዓት ተነስተው ወደ እየሩሳሌም ተመልሱ። ይህም የሚያስረዳን እውነታ ይህ ነው ሁል ጊዜ ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጋር ስንጓዝ ተስፋችን የለመለመ ጉልበታችን የበረታ እምነታችንም የጠነከረ ይሆናል። ይህም ደግሞ በሙሉ ቁርጠኝነት ልክ እንደ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ራሳችንን ሙሉ በሙሉ ለእርሱ እንድንሰጥና በእርሱ ፍቅር ብቻ እንድንመላለስ ያደርገናል። እንግዲህ እኛም እንደ ቃሉ ይህንን ሁሉ ፈፅመን የክብሩ ተካፋዮች እንድንሆን የደካሞች አፅናኝና የክርስቲያኖች ረዳት የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ይህንን ጸጋና በረከት ለእያንዳዳችን ታሰጠን።

የሰማነውን ቃል በሕይወት መኖር እንድንችል ጸጋና በረከቱን ያብዛልን!

ምንጭ፡ ሬዲዮ ቫቲካን የአማርኛ የስርጭት ክፍል

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

18 May 2024, 22:07