ዓርብ ስቅለት
የሕማማቱና ዋና ቀን ዓረብ ስቀለት ነው። በዚህ ቀን በተለየ መንገድ የኢየሱስን ውርደት፣ ሰቃይ፣ ሞት እናስባለን። «እናምናለን እናምናለን እናምናለን የማይታመመው መታመሙን እናምናለን፣ ጐኑን መወጋቱ እጆቹ መቸንከራቸውን እናምናለን ሞቱንም እናምናለን» (1) እያልን በመንፈሳዊ ሐዘን የአርብ ስቅለት ስግደታችንን እንጀምራለን።
«ሲነጋ የካህናት አለቆች ኢየሱስን በቀራኒዮ ኮረብታ ሊሰቅሉት ተመካከሩ»። ኢየሱስን ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ስለ አዳም ልጆች ሕይወት የሚሰቀልበት ጊዜ በተስፋ ይጠባበቅ ነበር። አይሁዳውያን (በይበልጥ ጸሐፊዎችና ፈሪሳውያን ካህናት) ኢየሱስ ይጠሉት ስለነበር በመስቀል ሰቅለው ከፊታቸው የሚያስወግዱበት አመቺ ጊዜ ይፈልጉ ነበር። በእጃቸው ሲወድቅ በሐሰት ከሰው በፍጥነት ሞት ፈረዱበት። ፍርዳቸው ግን ያለ ጲላጦስ ቃል ሊጸና ስለማይችል ወደ እርሱ አቀረቡት። «ወመጠውዋ ለጲላጦስ´ እርሱም ኢየሱስን በእርጋታ መረመረው። በደል ሳይኖረው ብቻ በቅንዓት እንደ ከሰሱት ታወቀው፣ ስለዚህ ሊያድነው ፈለገ።
በርባን የሚባል ብዙ ብጥብጥ የሚፈጥር ሽፍታ ነፍሰ ገዳይ በክፋቱ ሰውን ሁሉ ያዥሰቀቀ ሰው በእስር ቤት ነበር። «በርባንን ወይስ ኢየሱስን በነፃ እንዲለቀቅላችሁ ትፈልጋላችሁ?» (ማቴ. 27፣17፣ማር.15፣7) አላቸው። ከኢየሱስ ይልቅ በርባንን የሚጠሉ ይመስለው ስለ ነበር። ግን ተሳሳተ ሕዝቡ በካህናት አለቆች ተመርቶ «ባርባን ይለቀቅ ኢየሱስ ይሰቀል» (ማቴ.27፣21) አሉ። ይህም ጲላጦስን ገረመው ለመጨረሻ ጊዜ ኢየሱስን ሊያድነው ጣረ። በጣም አስገረፈው፤ ሰውነቱም ሁሉ ቆሰለ። ደም ከሰውነቱ ሁሉ ፈሰሰ መልኩ ሁሉ ተለዋወጠ።
በዚህ አሳዛኝ ሁኔታ በሞት አፋፍ ላይ ደርሶ ሲያዩት «ምንም እንደማያደርጋቸው አይተው ራርተው ይተውታል» የሚል ተስፋ ነበረው። «እነሆ ይኸው ሰውዬው» ሲላቸው ተናደው «ስቀለው! ስቀለው!» (ዮሐ. 19፣5) እያሉ ጮኹ። «ይህን ሰው ከለቀቅኸው የቄሣር ወዳጅ አይደለህም» () እያሉ አስፈራሩት። ጲላጦስ ነገሩ እንደማይሆንለት ስለተገነዘበ ኢየሱስን ማዳን ማለት ራሱን መጉዳት እንደሆነ ስለታወቀው የሚፈልጉትን አደረገላቸው።
«አርዑተ መስቀሉ ጾረ ይስቅልዎ ሖረ ከመ ኪያነ ይቤዙ እግዚእ ኮነ ገብረ» (ዮሐ. 19፣12)። «የመስቀሉን እንጨት ተሸክሞ እንዲሰቀሉት ሄደ። የእኛ መስዋዕት ቤዛ እንዲሆን ጌታ አገልጋይ ሆነ»። አይሁዳውያን ይፈልጉት የነበረውን ፈቃድ ሲያገኙ ኢየሱስን ከባድ መስቀል አሸክመው ወደ ቀራኒዮ ወሰዱት። ልክ እንደሚታረድ ከብት ተደስተው ወደ ሞቱ ሥፍራ ነዱት። በመንገድ ሶስት ጊዜ ወደቀ። አይሁዳውያን እየሰደቡና እያስፈራሩት አስነሱት። ከብዙ ድካምና ስቃይ በኋላ ወደ ቀራኒዮ ተራራ ደረሰ። እዚያ አይሁዳውያን ልብሱን ገፍፈው መሬት ላይ አስተኙት። በትልልቅ ምስማሮች ከመስቀሉ ጋር ቸነከሩት መከራው እንደገና ባሰ።
«ተሰቅለ! ተሰቅለ! ተስቅለ! ወሐመ ቤዛ ኩሉ በመስቀሉ ቤዘዘወነ እሞት ባልሐነ» (ዘ6ቱ ሰዓት) «ተሰቀለ ተሰቀለ ተሰቀለ ታመመ የሁሉም ቤዛ ሆነ። በመስቀሉ ቤዛ ሆነ ከሞትም አዳነን» እንደ በደለኛ በመስቀል ላይ ተሰቀለ። የመስቀልን ውርደት በትዕግሥት ተቀበለ። በሁለት ሌቦች መካከል ተሰቀለ ከበታች ሆነው «ሌሎችን ያድናል እስቲ ራሱን ያድን» እያሉ ያላግጡበት ነበር። ሲሰቅሉት ፀሐይ ጨለመች ጨረቃም ደም መሰለች፣ መሬት ተንቀጠቀጠች። ከብዙ ስቃይ (ጣር) በኋላ «ሁሉ ተፈጸመ አባቴ ሆይ ነፍሴን በእጅህ አስረክባለሁ» በማለት ሞተ። ስለ ነፍሳችን ብሎ በመስቀል ላይ ተሰዋ። የኃጢአታችንን ዕዳ ሊክስ ሞተ። ኢየሱስ በመስቀሉ ስላዳነን እናመስግነው። ከአሁን በኋላ በኃጢአታችን በመስቀል ላይ እንዲሰቀል (እንዲሰቃይ) እንድናስገድደው ቁርጥ ፈቃድ እናደርግ።