የወንጌል ደስታ የወንጌል ደስታ   (©khanchit - stock.adobe.com)

ሰው ለሰው

ቤተ ክርስቲያን ጥልቅ የሆነ ሚሲዮናዊ ተሐድሶ በምትሻበት በአሁኑ ወቅት፣ ለእያንዳንዳችን የየዕለት ኃላፊነት የሚሰጠን የስብከት ዓይነት አለ። እርሱም ለምናገኛቸው ሰዎች፣ ለባልንጀሮቻችንም ሆነ ለእንግዶች ወንጌልን ከማዳረስ ጋር የተያያዘ ነው። ይህም በውይይት መካከል የሚካሄድ መደበኛ ያልሆነ፣ አገልግሎት ነው። ደቀ መዝሙር መሆን ማለት የኢየሱስን ፍቅር ለሌሎች ለማዳረስ ሁልጊዜ ዝግጁ መሆን ነው። ይህም በድንገትና በማናቸውም ቦታ፣ በመንገድ ላይ፣ በከተማ አደባባይ፣ በሥራ ወቅት ወይም በጉዞ ላይ ሊሆን ይችላል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ- ቫቲካን

ሁልጊዜ በአክብሮትና በጨዋነት በሚካሄድ በዚህ ስብከት ውስጥ የመጀመሪያው እርምጃ ሌላው ሰው የራሱን ደስታ፣ ተስፋና ጭንቀት፣ ወይም ሌሎች ከልብ የመነጩ ፍላጎቶቹን ለሚወዳቸው የሚናገርበት የግል ውይይት ማድረግ ነው። የእግዚአብሔርን ቃል፣ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በማንበብ ወይም አንድ ታሪክ በማውራት፣ ማምጣት የሚቻለው ከዚያ በኋላ ብቻ ነው። ነገር ግን፣ ሁል ጊዜ መሠረታዊ መልእክቱን፣ ይኸውም ሰው የሆነውን ስለ እኛ ራሱን አሳልፎ የሰጠውን፣ ሕያው የሆነውንና ደኅንነቱንና ወዳጅነቱን የሚሰጠን የእግዚአብሔርን የግል ፍቅር፣ ማስታወስ ያስፈልጋል። ይህ መልእክት፣ ሁል ጊዜ ለመማር በሚፈልግ ሰው ስም እንደሚሰጥ ምስክርነት፣ መልእክቱም እጅግ ጥልቅና ሰፊ ከመሆኑ የተነሣ ዘወትር ከማስተዋል ችሎታችን በላይ እንደሆነ በመገንዘብ በትህትና መቅረብ አለበት። አንዳንድ ጊዜ መልእክቱ በቀጥታ፣ አንዳንዴ በግል ምስክርነት ወይም እንቅስቃሴ፣ ወይም መንፈስ ቅዱስ ለዚያ ሁኔታ በሚያቀርበው ሃሳብ መሠረት ሊቀርብ ይችላል። ጥንቃቄ የሚሻ ሲመስልና ሁኔታዎቹ ምቹ ከሆኑ፣ ይህ የወንድማማችነትና የተልአኮ ግንኙነት ሰውየው ከገለጻቸው ጭንቀቶች ጋር በተያያዘ አጭር ጸሎት በማድረግ ሊጠናቀቅ ይችላል። በዚህ ዓይነት በሌሎች ዘንድ የመደመጥና የመግባባት ልምድ ይኖራቸዋል፤ እነርሱ ያሉበት ልዩ ሁኔታ በእግዚአብሔር ፊት እንደቀረበና የእግዚአብሔር ቃል በእውነት በሕይወታቸው እንደሚናገር ያውቃሉ።

ይሁን እንጂ፣ የወንጌል መልእክት ሁል ጊዜ መተላለፍ ያለበት አስቀድመው በተቀነባበሩና በቃል በተጠኑ ወይም ፍጹም የማይለወጥ ይዘቱን በሚገልጹ የተወሰኑ ቃላት ነው ብለን ማሰብ የለብንም። ይህ ግንኙነት በብዙ የተለያዩ መንገዶች ሊካሄድ ስለሚችል ሁሉንም ማብራራት ወይም መዘርዘር አይቻልም። በመሆኑም ሕዝበ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነት እንቅስቃሴዎችና ምልክቶቻቸው አቀራረቡን በራሳቸው ይወስናሉ። ወንጌል በባህል ላይ በጽናት የተገነባ ከሆነ መልእክቱ ከሰው ወደ ሰው መተላለፍ ብቻ መሆኑ ይቀራል። የክርስቲያኖች ቁጥር አናሳ በሆነባቸው አገሮች ግን እያንዳንዱ ተጠማቂ ወንጌልን እንዲሰብክ ከማበረታታት ጎን ለጎን የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ቢያንስ መነሻ የሚሆኑ ወንጌልን ከባህል ጋር የማዋሐድ ዘዴዎችን በትጋት ማስተዋወቅ ይኖርባቸዋል። የመጨረሻው ዓላማ፣ ለእያንዳንዱ ባህል በተገባ መልኩ የተሰበከው ወንጌል ከዚያ ከተለየ ባህል ጋር አዲስ ትስስር እንዲፈጥር ማድረግ መሆን አለበት። ይህ ሁሌም ረጅም ጊዜ የሚወስድ ሂደት ስለሆነ ከመጠን በላይ እንፈራው ይሆናል። ነገር ግን፣ አዲስ ፍርሃትና ጥርጣሬ ካበዛን ድፍረታችን ይቀንሳል፤ አዲስ ሃሳብ በማፍለቅ ፈንታ ባለን ስለምንረካ ምንም ዓይነት መሻሻል አናመጣም። በዚህ ረገድ በታሪካዊ ሂደቶች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ  ስለማይኖረን ቤተክርስቲያን ቀስ በቀስ ባለችበት ትቆምና  እኛ ተመልካቾች ብቻ እንሆናለን።

ወንጌልን ለሚሰብክ የሚያገለግሉ ማኀበራዊ ጸጋዎች

መንፈስ ቅዱስ መላውን ወንጌል የምትሰብክ ቤተክርስቲያን በልዩ ልዩ ጸጋዎች ያበለጽጋታል። እነዚህ ስጦታዎች ቤተክርስቲያንን ለማደስና ለመገንባት የታለሙ ናቸው። በሚገባ የሚያዝና በትንሽ ቡድን በአደራ የሚጠበቅ የቅርስ ዐይነት ሳይሆኑ ከቤተ ክርስቲያን አካል ጋር የተዋሐዱ፣ ወደ ማዕከል ማለትም ወደ ክርስቶስ የሚመሩ፣ የሚያደርሱ፣ የሚስቡ …. ወደ ስብከተ ወንጌል ግፊት የተላለፉ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ናቸው። የአንድ ጸጋ እውነተኛነት ማረጋገጫ ምልክቱ ቤተክርስቲያናዊ ባህርዩ እና  ለሁሉም ጥቅም ይሆን ዘንድ በእግዚአብሔር የተቀደሰና አማኙ ሕዝብ ሕይወት ጋር በሚገባ የመዋሐድ ችሎታው ነው። በመንፈስ የመጣ አዲስ ነገር ሲከሰት ሌሎች ስጦታዎችንና መንፈሳዊነትን መጋረድ የለበትም። አንድ ጸጋ በተሻለ መልኩ የወንጌልን መንፈስ እስካመለከተ ድረስ፣ ተግባራዊነቱ ይበልጥ ቤተ ክርስቲያናዊ ይሆናል። አንድ ጸጋ እውነተኛና ምሥጢራዊ በሆነ መንገድ ፍሬያማ የሚሆነው በማኅበር ውስጥ ነው። ቤተክርስቲያን ለዚህ ተግዳሮት በምትሰጠው ምላሽ መሠረት በዓለማችን የሰላም ምሳሌ መሆን ትችላለች።

አንዳንድ ጊዜ በሰዎችና በማህበረሰቦች መካከል ያለው ልዩነት ምቾት የማይሰጥ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን፣ የዚያ ልዩነት ምንጭ የሆነው መንፈስ ቅዱስ ከሁሉም ነገር መልካም ነገር ሊያወጣና ወደ ድንቅ የስብከተ ወንጌል መሣሪያነት ሊለውጠው ይችላል። ልዩነት ምን ጊዜም በመንፈስ ቅዱስ ረድኤት ሊታረቅ ይገባል። ልዩነትንና ብዝሃነትን ሊያነሣ፣ ከዚሁ ጋር አንድነትን ሊያመጣ የሚችለው እርሱ ብቻ ነው። እኛ በበኩላችን ልዩነትን ስንመኝ ራስ ወዳድ፣ ገለልተኛና ከፋፋይ እንሆናለን። እንደዚሁም በሰብአዊ ስሌት ተነሣሥተን አንድነትን ለመፍጠር ስንሞክር በመጨረሻ ወጥ የሆነ ተመሳሳይነትን በኃይል እንጭናለን። ይህ ለቤተክርስቲያን ተልእኮ አይጠቅምም።

ባህል፣ ሃሳብና ትምህርት

የወንጌልን መልእክት ለባለሙያዎች፣ ለሳይንቲስቶችና ለምሁራን መስበክንም ያካትታል። ይህ ማለት ተአማኒነትንና፣ በሁሉም በኩል ለወንጌል ይበልጥ ክፍት መሆንን የሚያበረታታውን አዲስ ይቅርታ መጠየቅን በተመለከተ የተሻለ አቀራረብና ውይይትን ለማጠናከር ይቻል ዘንድ በእምነት፣ በምክንያትና በሳይንስ መካከል ግንኙነት መፍጠር ነው። አንዳንድ የምክንያትና የሳይንስ ፈርጆች የወንጌል መልእክትን ለማስተላለፍ የሚረዱ የስብከተ ወንጌል መሣሪያ ይሆናሉ፤ ውሃ ወደ ወይን ይለወጣል። የተጀመረ ነገር ሁሉ የሚድን ሳይሆን ዓለምን የሚያበራና የሚያድስ የመንፈስ መሣሪያ ይሆናል።

የወንጌል ሰባኪያን እያንዳንዱን ሰው ለመድረስ መጨነቅ ወይም ወንጌልን ለባህሎች በሙሉ መስበክ  በራሱ በቂ አይደለም። ሐዋርያዊ ነገረ መለኮት ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ሳይንሶችና ሰብአዊ ልምዶች ጋር በውይይት ላይ ያለው ነገረ መለኮት የወንጌልን መልእክት ለተለያዩ ባህላዊ አገባቦችና ቡድኖች በተሻለ መልኩ ለማቅረብ የምንችልበትን መንገድ ለማወቅ  ይረዳናል። ቤተ ክርስቲያን ለስብከተ ወንጌል ባላት ዝግጁነት የነገረ መለኮት ሊቃውንትን የጸጋ ስጦታ እንዲሁም ሊቃውንቱ በዓለም ባህሎችና ሳይንሶች መካከል  ውይይት እንዲካሄድ  የሚያደርጉትን ምሁራዊ ጥረት ታደንቃለች፣ ታበረታታለችም። የነገረ መለኮት ሊቃውንት ይህን አገልግሎት ቤተክርስቲያን እንደ ማዳን ተልእኮ አካል አድርገው እንዲፈጽሙት አደራ እላለሁ። ይህን ሲያደርጉ ግን ቤተ ክርስቲያንና ነገረ መለኮት ወንጌልን ለመስበክ እንጂ በጠረጴዛ ላይ በተወሰነ ነገረ መለኮት ብቻ ረክተው ለመቀመጥ አይደለም።

ዩኒቨርሲቲዎች ይህን የስብከተ ወንጌል ዝግጁነት በተቀናጀና በፈርጀ ብዙ ጥናት መልክ ለመግለጽና ለማዳበር ምቹ አካባቢዎች ናቸው። የትምህርት ሥራቸውን ግልጽ ከሆነ ስብከተ ወንጌል ጋር ለማገናኘት ጥረት የሚያደርጉ የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች፣ ጥላቻ በሚያሳዩ አከባቢዎች ሳይቀር የተሻለ ዘዴ እንድንፈልግ በሚፈታተኑን በእነዚያ አገሮችና ከተሞች ጭምር፣ ባህልን በወንጌል ትምህርት ለመለወጥ የሚረዱ እጅግ ጠቃሚ መሣሪያዎች ናቸው።

ስብከት

አሁን ደግሞ የመንፈሳዊ እረኞችን ብርቱ ትኩረት የሚሻውን በሥርዓተ አምልኮ ውስጥ የሚካሄደውን ስብከት እንመልከት። እኔም በተለየና በጥንቃቄ ስለ ስብከትና ስለ ዝግጅቱ ለመናገር እፈልጋለሁ፤ ምክንያቱም ይህን ጠቃሚ አገልግሎት በተመለከተ ብዙ ስጋቶች እንዳሉ ስለሚገለጽ በቀላሉ ችላ ልንላቸው ስለማንችል ነው። ስብከት አንድ መንፈሳዊ እረኛ ከሕዝቡ ጋር ያለው ቅርበትና መልእክት የማስተላለፍ ብቃት መለኪያ ነው። ምእመናን ለዚህ ትልቅ ዋጋ እንደሚሰጡና እነርሱም ሆኑ ካህናት አገልጋዮቻቸው በስብከት ምክንያት እንደሚቸገሩ እናውቃለን። ይህም የሆነው ምእመናን ካህናትን መስማት ስላለባቸው ካህናት ደግሞ ለምእመናን ስለሚሰብኩላቸው ነው። ጉዳዩ እንዲህ መሆኑ ያሳዝናል። ስብከት በመሠረቱ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የሚያጽናና ግንኙነት እንዲፈጠር የሚያደርግ፣ ዘላቂ የተሐድሶና የዕድገት ምንጭ እንዲሁም ጥልቅና አስደሳች የመንፈስ ተሞክሮ ሊሆን ይችላል።

በወንጌል ሰባኪዎች በኩል ወደ ሌሎች ሰዎች ለመድረስ የሚሻው እግዚአብሔር እንደሆነና እርሱም ኃይሉን የሚያሳየው በሰው አንደበት አማካይነት መሆኑን አምነን ለስብከት ያለንን እምነት እናድስ። ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ስብከት አስፈላጊነት በአጽንኦት ይናገራል፤ ምክንያቱም ጌታ ወደ ሌሎች ሰዎች ለመድረስ የሚፈልገው በመልእክታችን አማካይነት ስለሆነ ነው (ንጽ.ሮሜ.10፡14-17)። ጌታችን በመልእክቱ የሰዎችን ልብ አሸነፈ፤ ከሁሉም ስፍራ እርሱን ሊሰሙ መጡ (ንጽ.ማር.1፡45)፣ በትምህርቱ ተደነቁ (ንጽ.ማር.6፡2 )፣ በሥልጣን የተናገረ መሰላቸው (ንጽ.ማር.1፡27)። ‹‹ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ፣ ለስብከትም ይልካቸው ዘንድ›› (ማር.3፡14) ክርስቶስ የሾማቸው ሐዋርያት አህዛብን ሁሉ ወደ ቤተክርስቲያን እቅፍ አመጡ (ንጽ.ማቴ.16፡15-20)።

የሥርዓተ አምልኮ አገባብ

‹‹በተለይ በመሥዋዕተ ቅዳሴ ወቅት የሚካሄደው የእግዚአብሔር ቃል ሥርዓተ አምልኮ በአብዛኛው የአስተንትኖና የትምህርተ ክርስቶስ ጊዜ ሳይሆን በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል ውይይት የሚደረግበት ትልቅ የደኅንነት ሥራ የሚሰበክበትና ቃል ኪዳኑ ያለማቋረጥ የሚታደስበት ወቅት መሆኑን››  ማስታወስ ተገቢ ነው። ስብከት ቁርባናዊ አገባብ ስላለው ልዩ ጠቀሜታ አለው። ወደ ምሥጢራዊ ሱታፌ የሚመራ በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል ውይይት የሚካሄድበት  ከሁሉ ብልጫ ያለው ወቅት በመሆኑ ከማናቸውም የትምህርተ ክርስቶስ ዓይነቶች ይበልጣል። ስብከት ጌታ ከሕዝቡ ጋር የጀመረውን ውይይት እንደገና ያነሣል። ለእግዚአብሔር ያለው ፍላጎት ሕያውና የጋለ ሆኖ የሚገኘው የት ላይ እንደሆነ፣ እንዲሁም በአንድ ወቅት ተወዳጅ የነበረው ያ ውይይት ወዴት እንደተቀለበሰና አሁን እንዴት ባዶ እንደቀረ ለመረዳት ሰባኪው የማህበረሰቡን ልብ ማወቅ ይኖርበታል።

ስብከት በመገናኛ ብዙሃን እንደሚቀርቡት የመዝናኛ ዓይነቶች  ሊሆን አይችልም። ሆኖም ለሥነ ሥርዓቱ ሕይወትና ትርጉም የሚሰጥ እንዲሆን ያስፈልጋል። በሥርዓተ አምልኮ መዋቅር ውስጥ የሚካሄድ ስብከት በመሆኑ ልዩ ነው። ስለዚህ፣ አጭርና የንግግር ወይም የትምህርታዊ መግለጫ መልክ የሌለው ሊሆን ይገባል። አንድ ሰባኪ የአድማጮቹን ቀልብ ለአንድ ሙሉ ሰዓት ሊስብ ይችላል፤ ነገር ግን በዚህ ረገድ ቃሉ ከእምነት አምልኮ የበለጠ ዋጋ ይኖረዋል። የሥርዓተ አምልኮ ስብከት ለረጅም ጊዜ ከቀጠለ ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን ይኸውም ሚዛኑንና እንቅስቃሴውን ይጎዳል። ስብከቱ በሥርዓተ አምልኮ አገባብ ሲካሄድ ለአብ የሚቀርብ መሥዋዕት አካልና ክርስቶስ በሥርዓተ አምልኮ ወቅት የሚያፈስሰው ጸጋ መተላለፊያ  መንገድ ይሆናል። በዚህ መሠረት፣ ስብከት ሕዝበ ምእመናኑንና  ሰባኪውን ጭምር በቁርባን ከሚገኝ ክርስቶስ ጋር ሕይወትን የሚለውጥ ሱታፌ እንዲመሠርቱ የሚረዳ መሆን አለበት። ይህ ማለት፣ ከአገልጋዩ ይልቅ ጌታ ዋና የትኩረት ነጥብ ይሆን ዘንድ የሰባኪው መልእክት የተወሰነ ሊሆን ይገባል።

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የወንጌል ደስታ በተሰኘ አርዕስት በዛሬው ዓለም ወንጌልን ስለ መስበክ

ለጳጳሳት፣ ለካህናት፣ ለደናግልና ለምእመናን ያስተላለፉት ሐዋርያዊ  ምክር ከአንቀጽ 121-138 ላይ የተወሰደ!

 

31 May 2024, 13:51