ከክርስቶስ ጋር ከሞት ከተነሣችሁ የሰማይን ነገር አስቡ ከክርስቶስ ጋር ከሞት ከተነሣችሁ የሰማይን ነገር አስቡ 

ከክርስቶስ ጋር ከሞት ከተነሣችሁ የሰማይን ነገር አስቡ

ከትንሣኤ በኋላ ሐሙስ

ኢየሱስ ከሞት ሲነሣ እኛንም ከኃጢአት ሞት አስነስቶ ሰማያዊ ሕይወት ሰጠን። የመንግሥተ ሰማያትን በር ከፈተልን። «እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከሞት ተነሣችሁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ በሰማይ ያሉትን ነገሮች በብርቱ ፈልጉ። ዘወትር በላይ በሰማይ ስላሉት ነገሮች አስቡ እንጂ በምድር ላይ ስላለው ነገር አታስቡ» (ቄላ.3፣1) ይለናል ቅዱስ ጳወሎስ።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን  

ኢየሱስ ከተነሣ በኋላ ምድርን ትቶ ወደ ሰማይ ዐረገ። እኛም ደግሞ ከእርሱ ጋር ስለተነሣን በመንፈስ እንድንከተለው ወደ ሰማይ መመልከት ይገባናል። እኛ ከክርስቶስ ትንሣኤ በኋላ የሰማይ እንጂ የምድር አይደለምን። የክርስቶስ ልጆች እንጂ የዓለም ልጆች አይደለንም። «እኔ የዓለም ስላልሆንኩ እነርሱም የዓለም አይደሉም» (ዮሐ.17፣16) ይላል ኢየሱስ። «እኛ በሞት የመለየትን ያህል ከኃጢአት የተለየን ሆነን ሳለ እንዴት በኃጢአት ጸንተን እንኖራለን? ከኢየሱስ ጋር አንድ ለመሆን መጠመቃችንን አታውቁምን? በጥምቀት ከእርሱ ጋር በተቀበርን ጊዜ የእርሱ ሞት ተካፋዮች ሆነናል» (ሮሜ 6፣2-5) እያለ ቅዱስ ጳውሎስ ይመክረናል።

ከኃጢአት ሞት ከክርስቶስ ጋር ከተነሣን ከምድራዊ ሕይወት ከፍ ብለን ከእርሱ ጋር እንድንኖር መንግሥተ ሰማያት በብርቱ መመኘት ያስፈልገናል። እኛ ለሰማይ ነውና የተፈጠርነው። የክርስቶስ ትንሣኤ ከዝቅተኛ ኑሮ ወደ ከፍተኛ ኑሮ ከፍ አደረገን፣ ከጨለማ ወደ ሰማያዊ ብርሃን አሸጋገረን። የሰማይን ነገር አስፈላጊነትና ጣዕሙን ገለጸልን። እንግዲህ ወደ ሰማይ እንመልከት። ክርስቶስ ራሱ የሰጠንን ሰማያዊ ሀብት እናስብ አዲስ ሕይወት እንልበስ።

  «ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ የሰማይን ነገር ፈልጉ። የሰማይን ነገር አስቡ። የትኛው ነው የላይኛው ነገር? ራሱን እግዚአብሔርን ጸጋዎቹን መንፈሳዊ ሀብቶቹን … ነው በሰማይ በላይ እመቤታችን ድንግል ማርያም መላእክትና ቅዱሳን አሉ። በሰማይ ሙሉ ፍቅር፣ ሰላም፣ ደስታ አለ። ዓይን ያላየው፣ ጆሮ ያልሰማው፣ የሰው ልብ ያላሰበው ዘለዓለማዊ ብፅዕና አለ። እዚያ ሐዘን፣ ስቃይ፣… የሚባል ነገር ፈጽሞ የለም።

  የምድርን ነገር አታስቡ። ምድራዊ ነገር ሁሉ አላፊና ሞኝነት ነው። ምድር የጭንቀት ሥፍራ ለጥቂት ጊዜ የምንቀመጥበት የኃጢአት ሥፍራ ናት። ማንኛውም የምድራዊ ነገር እኛን ሊያረካን አይችልም። ምክንያቱም ስለ ሰማያዊና ለማያልፍ ዘለዓለማዊ ሀብት ለሰማያዊ ክብር የተፈጠርን ስለሆንን በዚህ ምድርን አንርሳት። ወደ ሰማይ እንመልከት በምድራዊ ነገር አንዘናጋ።

09 May 2024, 19:29