ታሊታ ኩም 15ኛ ዓመቱን አከበረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን በመዋጋት ላይ የተሰማሩ ከ200 በላይ የታሊታ ኩም ሴቶች እና ወንዶች ገዳማዊያን፣ ምእመናን ወጣቶች እና ከአደጋው የተረፉ ተወካዮች ለታሊታ ኩም 2ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ተሰባስበዋል። ጠቅላላ ጉባኤው የሚካሄደው ይህ ፀረ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ዓለም አቀፍ የገዳማዊያን ትስስር እ.አ.አ በ2009 ዓ.ም. በዓለም አቀፉ የበላይ አለቆች ህብረት (UISG) ስር የተመሰረተበትን 15ኛ ዓመት በሚያከብርበት ወቅት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል የተባለ ሲሆን፥ ጉባኤው ከግንቦት 10 እስከ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ከሮም ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው በሳክሮፋኖ መንደር ውስጥ ባለው ‘ፍራተርና ዶመስ’ ይካሄዳል።
የታሊታ ኩም ታሪክ
ታሊታ ኩም የሚለው ቃል በማርቆስ ወንጌል ላይ ካለው እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልጃገረዷን ከሞስ ያስነሳባት ታሪክ ላይ የተመሰረተ የአርማይክ ቃል ሲሆን፥ አቻ ትርጉሙም 'ድንግል ሆይ ተነሽ" እንደማለት ነው። የዓለም አቀፉ የበላይ አለቆች ህብረት አባል የሆነው ይህ ተቋም ወይም ትስስር እ.አ.አ. ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጎጂዎችን በማገልገል ላይ ይገኛሉ። የመጀመሪያውንም አስተዋፅዖ ያደረጉት በፍትህ እና ሰላም ኮሚሽን ስር በተቋቋመው የጥናት ቡድን በኩል የስልጠና ጽሁፎችን በማዘጋጀት ነበር። እነዚህ ጽሁፎች ወደ 11 የተለያዩ ቋንቋዎች የተተረጎሙ ሲሆን፥ በወቅቱ ስለ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ተግዳሮት ግንዛቤን በማሳደግ ረገድ ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክተዋል።
እ.አ.አ. በ2001 በሮም በተካሄደው የዓለም አቀፉ የበላይ አለቆች ህብረት ምልአተ ጉባኤ ላይ የተገኙት ሃላፊዎች የሴቶች እና ህጻናትን በደል እና ጾታዊ ብዝበዛ ብሎም የሚደርስባቸውን ችግር ለመፍታት በጋራ ለመስራት ቃል ገብተዋል። ይህም በመሆኑ በወቅቱ የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ተብሎ ይጠራ ከነበረው ጋር በመተባበር የሥልጠና ፕሮግራም እንዲዘጋጅና በርካታ የክልል ትስስሮች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል። የተለያዩ ገዳማዊያን እና የአይ.ኦ.ኤም አባላት ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተዘዋውረው ወርክሾፖችን በማካሄድ እና ገዳማዊያኑን ህገወጥ የሰዎች ዝውውር በሀገራቸው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለሚያደርሰው ችግር ግንዛቤ አስጨብጠዋል።
በኋላም በ2009 ዓ.ም. የዓለም አቀፉ የበላይ አለቆች ህብረት ታሊታ ኩምን በይፋ ያቋቋመ ሲሆን፥ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሲሰለጥኑ የነበሩ ገዳማዊያት እህቶች አንድ ላይ መሰባሰብ ጀመሩ። ዓለም አቀፉ የበላይ አለቆች ህብረት በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ትግል ላይ መሳተፍ ከጀመረ በ26 ዓመታት ውስጥ እና በታሊታ ኩም በኩል ደግሞ በ15 ዓመታት ውስጥ፣ ብዙ ገዳማዊያን እህቶች ይህንን ወንጀል ለማስወገድ ጥረታቸውን አንድ ላይ በማድረግ ታግለዋል።
የዓለም አቀፉ የበላይ አለቆች ህብረት ዋና ፀሐፊ ሲስተር ፓት መሬይ በታሊታ ኩም ጉዞ ላይ በማስመልከት እንደተናገሩት “በተገኘው ስራ በጣም ኩራት ይሰማናል፥ ደስተኞችም ነን፣ ነገር ግን ይህንን የሰው ልጆች ላይ የሚፈፀመውን ግፍ ለመዋጋት ብዙ መስራት እንደሚያስፈልግ እናውቃለን” ብለዋል።
ታሊታ ኩም ዛሬ ላይ ያለው ገጽታ
ልክ እንደ ምስረታ ተልእኮው፣ ታሊታ ኩም አሁንም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ባሉት ጉዳዮችም እንደሚሳተፍ የታሊታ ኩም ዓለምአቀፍ አስተባባሪ የሆኑት ሲስተር አቢ አቬሊኖ ሲገልጹ፥ “‘ታሊታ ኩም’ የሚለው አገላለጽ የሚያመለክተው የተስፋን፣ የርህራሄ እና የምሕረትን የመለወጥ ኃይልን ነው፣ ይህም የዓለም አቀፍ ትስስራችንን ተልእኮ ይገልጻል” ብለዋል።
የአባላት ትስስሮቹ በሰው እና በማህበረሰብ ላይ ያተኮረ አካሄድ እንደሚከተሉ እና ይህም በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወጥመድ ውስጥ የገቡትን ወይም ከጉዳቱ በማገገም ላይ ያሉትን ሴት እና ወንድ ህፃናትን እንዲሁም ወጣት ሴቶች እና ወንዶችን እንዲቀርቡ ይረዳቸዋል።
ሲስተር አቢ ይሄን አስመልክተው ሲናገሩ፥ “ስለ ህገ ወጥ የሰው ዝውውር ስንናገር የተወሳሰበ እና የተለያየ ገጽታ ያለው የመሆኑን እውነታን ነው። በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህፃናት ልጆች፣ ወንዶች እና ሴቶች የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች ናቸው። የሴት ገዳማዊያኑ እና የአጋሮቻችን ድምጾች ከአደጋው የተረፉትን ይደግፋሉ ብሎም መልሰው እንዲያገግሙ እና ሰብአዊ ክብራቸውን እንዲያገኙ ይረዷቸዋል” ብለዋል።
ታሊታ ኩም የትስስሮች ህብረት ነው
‘ታሊታ ኩም ኢንተርናሽናል’ አሁን ላይ የተለያዩ ትስስሮች ህብረት ሆኗል። ይሄም ብሄራዊ፣ ክልላዊ እና አህጉራዊ ትስስሮችን የሚያጠቃልል ሲሆን፥ በትስስሮች ላይ ያለውን ከፍተኛ ችሎታ ማዳበሩንም ቀጥሏል። በሁሉም አህጉሮች ውስጥ በሚገኙ 107 አገሮች ላይ 60 የሚሆኑ ትስስሮች ይገኛሉ። ከዚህም ባለፈ ታሊታ ኩም በቅርቡ በተለይም በእስያ እና በአፍሪካ የክፍለ አህጉራዊ ማዕከሎችን ያቋቋመ ሲሆን፥ በ 2023 ደግሞ በቶጎ እና በፖርቶ ሪኮ ውስጥ አዳዲስ የትስስር ማዕከሎች ተመስርተዋል።
የታሊታ ኩም ትስስር 5,871 ንቁ አባላት እና ተባባሪዎች ያሉት ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል 777 ሴት ገዳማዊያን እና ወደ 93 የሚጠጉ ካህናት፣ እንዲሁም 48 የተለያየ ሃይማኖት ያላቸው ተባባሪዎች አሉት። ይህ ትስስር ታሊታ ኩም በ2023 ብቻ 753,392 ሰዎችን እንዲደርስ አስችሎታል፥ ይህም ከ2022 ዓ.ም. በ34.4 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ከራሱ የትስስር አባላት እና ተባባሪዎች በተጨማሪ የታሊታ ኩም ትስስር ከካቶሊክ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ እና መንግሥታዊ ድርጅቶች ጋር አስደናቂ አጋር ግንኙነቶችን ፈጥረዋል። በዚህም መሰረት እ.አ.አ. በ2023 የታሊታ ኩም ትስስር ከ297 የካቶሊክ ድርጅቶች፣ 219 መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ከ204 መንግሥታዊ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ከቀድሞው ዓመት በ14.6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
የገዳማዊያት እህቶች የፀረ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሽልማቶች
የዓለም አቀፉ የበላይ አለቆች ህብረት ፕረዚዳንት የሆኑት ሲስተር ሜሪ ባሮን ሲያብራሩ የገዳማዊያን እህቶች የፀረ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሽልማት (SATA) በ2023 በለንዶን መካሄዱን ጠቅሰው፥ "ሽልማቱ ወይም ሳታ- SATA ማህበረሰባቸውን ከህገወጥ የሰዎች ዝውውር ለመጠበቅ ለታገሉ ልዩ ድፍረትን፣ ፈጠራን፣ ትብብርን እና ስኬትን ላሳዩ እንደ ጉባኤያቸው እና ትስስራቸው ተወካይ በመሆን የቀረቡ የሶስት እህቶች ዓመታዊ በዓል ነው” ብለዋል።
የታሊታ ኩም ወጣት አምባሳደሮች
የወጣቶች ተሳትፎ በታሊታ ኩም ፀረ-ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወጣት አምባሳደሮች ፕሮግራም በኩል በመስከረም 2021 በእስያ የተጀመረ ሲሆን፥ ይህ ፕሮግራም ወደ ኦሽንያ፣ አፍሪካ እና ላቲን አሜሪካ በመሸጋገር በዓለም ዙሪያ በማደግ ተስፋፍቷል። ባለፈው ዓመት በአፍሪካ ብቻ በዚህ ፕሮግራም 14,800 ወጣቶች ተሳትፈዋል።
የወጣት አምባሳደሮቹ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በመዋጋት ረገድ ከእኩዮቻቸው በተለየ መልኩ እንደ ተልእኳቸው አንድ አካል፣ ከየካቲት 1 ቀን 2022 ዓ.ም. ጀምሮ ‘የጸሎት ማራቶን’ በተባለው ዝግጅት ላይ እየተሳተፉ ሲሆን፥ እነዚህ ወጣቶች በ2024 በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ቀርበው በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
በፖርቱጋል ርዕሰ መዲና ሊዝበን በተካሄደው የዓለም ወጣቶች ቀን ላይ ወጣት አምባሳደሮቹ ታሊታ ኩም ባዘጋጀው የማሳያ ድንኳን ውስጥ ተገኝተዋል። በወቅቱም ከቀን ወደ ቀን የተለያዩ ወጣቶች ወደ ታሊታ ኩም ድንኳን በመምጣት በፀረ-ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ዘመቻ ላይ መሳተፍ ስለሚችሉበት ሁኔታ ወጣት አምባሳደሮቹን አነጋግረዋል። እንዲሁም እጃቸውን በቀለም በመንከር እና የእጅ አሻራቸውን “ህገወጥ የሰው ዝውውርን እንከላከል” የሚል መልዕክት የተፃፈበት እና 16 ሜትር በሚረዝመው ባነር ላይ እንዲያሳርፉ ተጋብዘዋል። ይህ ባነር በዓለም የወጣቶች ቀን ወቅት በዓለም ዙሪያ ያሉ ወጣቶች ለፈጸሙት ተግባር እንደ ተጨባጭ ማሳያ ምልክት ተደርጎ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ተሰጥቷል።
ባለፈው ጥር 21 የታሊታ ኩም ወጣት አምባሳደሮች በ2023 በተሰራው አዲሱ ‘የዎኪንግ ኢን ዲግኒቲ’ (Walking in Dignity) መተግበሪያ በኩል ወጣቶችን ለህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች በሚደረገው እንክብካቤ ላይ እንዲሳተፉ ግብዣ አቅርበውላቸዋል። መተግበሪያው ወጣቶችን እኩዮቻቸው ከሆኑ ከወጣት አምባሳደሮቹ ጋር አብረው እንዲራመዱ ይጋብዛል። ተጠቃሚዎች በየደረጃው የመተግበሪያውን ይዘትን በሚከፍቱበት ሰዓት ለተቋሙ “ልገሳ” እንደሚያደርጉ እና ታሊታ ኩም እንዴት ተልእኮውን እንደሚፈጽም ሲገነዘቡ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ለመሳተፍ ያስችላቸዋል።
የታሊታ ኩም ራዕይ
ታሊታ ኩም ኢንተርናሽናል ዓለማችን ይህን ተግዳሮት ለመፍታት ላላት ታላቅ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት ትስስሩን ማስፋፋቱን እንደሚቀጥል ተስፋ ያለው ሲሆን፥ በዚህ ዓመት ታሊታ ኩም በፓስፊክ ደሴቶች፣ አንጎላ፣ ኮንጎ፣ ኩባ፣ ማላዊ፣ ብሩንዲ እና ማሌዥያ ውስጥ ትስስሩ እንዲመሰረት ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እየሰራ ይገኛል።