ቅድስት ሥላሴ
የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
«እግዚአብሔር በመለኮቱ ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ በመንግስቱ አለ። እግዚአብሔር በሶስትነቱና በመለኮቱ ሶስት የሥላሴ ሕላዌ የፍጥረት ሁሉ ሕልውና ነው። ፍጡሮች ሁሉ በአብ፣ በወልድ፣በመንፈስ ቅዱስ ፍላጐት ከኢምንት ነገር መጡ። በይበልጥ ደግሞ እኛ በቅድስት በሥላሴ አምሳል የተፈጠርን ነን። «እግዚአብሔር ሰውን በመልካችንና በአምሳላችን እንፍጠር አለ» (ዘፍ.1፣26 ) ይላል ቅዱስ መጽሐፍ። «አዳምን በአምሳሉ ከመፍጠሩ በፊት እግዚአብሔር በመንግሥቱ አለ»(አኰ. ቀር.አምቅጽመዓለም)።
በሥላሴ ስም ክርስቶስን ተቀበልን። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከመውጣቱ በፊት ሐዋርያቱን ወንጌል እንዲሰብኩ ወደ ዓለም ሁሉ ሲልካቸው «ሄዳችሁ አስተምሩዋቸው በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁአቸው» (ማቴ.28፣19) አላቸው። ካህን የጥምቀት ጸጋ ሲሰጠን ሳለ «እኔ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠምቅሃለሁ» እያለ ክርስትናን እንድንቀበል ያደርገናል። በጥምቀት ጸጋ ከሰይጣን ማደሪያነት ወደ የቅድስት ሥላሴ ማደሪያነት እንለወጣለን። በአርአያ ሥላሴ መፈጠራችን፣ በአርአያ ሥላሴ መጠመቃችን ክብራችን በጣም የሚያስቀና ነው። አብ፣ ወልድ፣መንፈስ ቅዱስ በጣም አከበሩን።
ቅድስት ሥላሴን ማመን ብቻ በቂ አይደለም የአምልኮ ስግደትም ማቅረብ አለብን። እነርሱ ማዕረግ ሰጥተው ፈጠሩን፣ እነርሱ ይመሩናል፣ ይጠብቁናል፣እኛ እነርሱ ርስታቸው ነን። ቤተክርስቲያን ሶስት ሳሉ አንድ ሲሆኑ «ለአብ፣ ለወልድ፣ ለመንፈስ ቅዱስ እንስገድ» እያለች እንድናከብራቸው፣ ጸሎታችንንና መስዋዕታችንን፣ ምስጋናችንን እንድቀርብላቸው ታነቃቃናለች። ጸሎታችንንና ሥራችንን «በስመ አብ፣ ወወልድ፣ ወመንፈስ ቅዱስ» ብለን እንድንጀምረውና እንድንጨርሰው ትፈልጋለች። የምናደርገውን ሁሉ ለሥላሴ ክብር ብለን እንድናደርገው ተመክረናለች። በስመ አብ ወይም ስብሐት ለአብ ስንል ራሳችንን ዝቅ አድርገን እንድገም።
በፍጥረታችን የሥላሴ አምሳል ከሆንን በሥራችንም ደግሞ ሥላሴን አንድንመስል ይገባናል። መንፈሳችንንና አካሄዳችንን ከሥላሴ ጋር ልናስማማው ያስፈልጋል። «እንደ ሰማያዊ አባታችሁ ፍጹም ሁኑ» ይለናል ኢየሱስ። ሥራችን መልካም ከሆነ በእውነትም ሥላሴ እንመስላለን። ሕይወታችንን የሚያንጽ ከሆነ ለእነርሱ የሚገባ አክብሮትና ፍቅር እናቀርብላቸዋለን። አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ እንዲኖሩና በእኛ እንዲደሰቱ ከፈለግን በፍቃዳቸው እንጓዝ።