የአሜሪካው የካቶሊክ እርዳታ ድርጅት ከጳጳሳዊ የበጎ አድራጎት አገልግሎት ጋር በአጋርነት እየሰራ ነው
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው “ክሮስ ካቶሊክ አውትሪች” የተሰኘው የሰብአዊ እርዳታ ድርጅት አመራር አባለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በዓለም ዙሪያ ለሚያደርጉት የበጎ አድራጎት ተግባራት የሚያደርገውን ድጋፍ ለማደስ በቅርቡ ቫቲካንን ጎብኝተዋል።
የበጎ አድራጎት ድርጅቱ አዲሱ ፕሬዝዳንት ሚሼል ሳጋሪኖ እና የቀድሞ ፕሬዝዳንት እና መስራች ጂም ካቭናር በመጀመሪያ ከቫቲካን የበጎ አድራጎት አገልግሎት ጽ/ቤት ሃላፊ እና አቃቤ ንዋይ ብፁዕ ካርዲናል ኮንራድ ክራጄቭስኪ ጋር ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ፣ በማስከተልም ረቡዕ ዕለት ከተደረገው ሳምንታዊ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በኋላ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።
በስብሰባዎቻቸው ወቅት የሊቃነ ጳጳሳቱን የበጎ አድራጎት አገልግሎት በመደገፍ አጋርነታቸውን ያደሱ ሲሆን፥ ከነዚህም ውስጥ ለዩክሬን የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን ማቅረብ እና በሶሪያ እና በጋዛ ለሚገኙ እጅግ በጣም የተራቡ ሰዎች የሚደረገው የምግብ ዕርዳታ ይገኙበታል።
ክሮስ ካቶሊክ አውትሪች እ.አ.አ. በ2001 ዓ.ም. ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል ለጳጳሳዊ የበጎ አድራጎት ሥራዎች እገዛ አድርጓል። የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ቀኖናዊ ሕጎቹ በቫቲካን ከተገመገሙ እና ከፀደቁበት ጊዜ ጀምሮ እንደ የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት በይፋ እውቅና አግኝቷል።
ክሮስ ካቶሊክ አውትሪች ፍላጎቶችን፣ አካባቢያዊ ሁኔታዎችን እና እንዴት በተሻለ ሁኔታ ማገልገል እና ህይወትን ማዳን እንደሚችሉ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ በሁሉም አከባቢ በምትገኝ ቤተክርስትያን ሥር በሚገኙ ሀገረ ስብከቶች እና ሃይማኖታዊ ጉባኤዎች ጋር በመስራት በዓለም ዙሪያ የአደጋ ጊዜ እና የድጋፍ እርዳታን ይሰጣል።
የዚህ ድርጅት ዋና ግብ የአካባቢውን ህዝብ በተቻለ መጠን በማገልገል የአካባቢውን ፍላጎቶች ለማሟላት እና ለውጡን ወደ ተሻለ መንገድ እንዲመራ ማድረግ ነው።
ተልእኳቸውም “ዓለም አቀፉን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን በማስተባበር ድሆችን እና ማህበረሰባቸውን በቁሳዊ እና በመንፈሳዊ ህይወት ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብር መለወጥ” ነው።
በጎ አድራጎት ድርጅቱ ከአራት ቢሊዮን ተኩል ዶላር በላይ የሚገመት ሰብአዊ እርዳታ ለአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እርዳታ ያደረገ ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል የምግብ፣ የመኖሪያ ቤት፣ የንፁህ ውሃ አቅርቦት፣ ማይክሮ ፋይናንስ እና የትምህርት ድጋፍ አድርጓል።