ብጹእ አቡነ ማርቲኔሊ በአቡ ዳቢ በሚገኘው የአብርሃም ቤተሰብ ቤት ውስጥ ያለውን የቅዱስ ፍራንቺስኮ ቤተክርስቲያንን ሲጎበኙ ብጹእ አቡነ ማርቲኔሊ በአቡ ዳቢ በሚገኘው የአብርሃም ቤተሰብ ቤት ውስጥ ያለውን የቅዱስ ፍራንቺስኮ ቤተክርስቲያንን ሲጎበኙ  

የብጹእ አቡነ ማርቲኔሊ ‘የአብርሃም ቤተሰብ ቤት’ን ጉብኝት ውይይት እና አንድነትን ያበረታታል ተባለ

አባ እስጢፋኖ ሉካ የደቡብ አረቢያ ሐዋርያዊ አስተዳደር የሆኑት ብጹእ አቡነ ፓኦሎ ማርቲኔሊ በአቡ ዳቢ ከተማ የሚገኘውን ‘የአብርሃም ቤተሰብ ቤት’ ቅጥር ጊቢ ውስጥ የሚገኘውን የቅዱስ ፍራንቸስኮ ቤተ ክርስቲያን ለመጎብኘት ያደረጉትን የመጀመሪያ ሃዋሪያዊ ጉብኝት አስፈላጊነት አብራርተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የአብርሃም ቤተሰብ መኖሪያ በአቡ ዳቢ በምትገኘው የሳዲያት ደሴት ላይ የተገነባ የሶስቱ አብርሃማዊ ሃይማኖቶች ማለትም የክርስቲያን፣ የሙስሊም እና የአይሁድ ሃይማኖቶች ማምለኪያ ቦታ (ቤተክርስቲያን፣ መስጊድ እና ምኩራብ) መገኛ ነው። የዚህ ቤት ውጥን እ.አ.አ. የካቲት 4 ቀን 2019 የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን በመወከል በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እና በአቡ ዳቢ የሚገኘውን የአል-አዝሃር መስጊድን በመወከል አህመድ ኤል-ታይብ በተፈራረሙት የሰብአዊ ወንድማማችነት ሰነድ ላይ የተመረኮዘ ነው።

ብጹእ አቡነ ፓውሎ ማርቲኔሊ ያደረጉትን ሃዋሪያዊ ጉብኝት በማስመልከት ከባለፈው አንድ ዓመት ጀምሮ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ከሚያገለግሉት ከአባ እስጢፋኖ ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ይቀርባል፦

ጥያቄ፦ የደቡብ አረቢያ ሐዋርያዊ ሃገረ ስብከት ጳጳስ የመጀመሪያቸው የሆነውን ሃዋሪያዊ ጉብኝት ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. እሁድ ዕለት አድርገዋል። በአብርሃም ቤተሰብ መኖሪያ ውስጥ ለሚገኘው ለቅዱስ ፍራንቺስኮ ቤተክርስቲያን ያለው ጠቀሜታ ምንድነው?

መልስ፦ የአብርሃም ቤተሰብ መኖሪያ ከአንድ ዓመት በፊት በይፋ እንደተከፈተ መታወስ አለበት፥ ስለዚህ ከዚህ የመጀመሪያ ዓመት ሃዋሪያዊ እንቅስቃሴ በኋላ ይህ ጉብኝት ልዩ ጠቀሜታ አለው። እኔ እንዳማስበው የብጹእ አቡነ ፓውሎ ማርቲኔሊ ሃዋሪያዊ ጉብኝት ቢያንስ በሦስት ደረጃዎች መግለጽ ይቻላል።

በመጀመሪያ፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሰብዓዊ ወንድማማችነት አድማስ በተመለከተ ያላትን ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ እና የሚመሰክር እንደሆነ፣ እንዲሁም ለአብርሃም ቤተሰብ መኖሪያ ያላትን ልምድ ለማካፈል ጭምር ነው። በእርግጥም ብጹእ አቡነ ፓኦሎ ማርቲኔሊ አበረታች ለሆነው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን አስተምህሮ ያላቸውን ድጋፍ እና የሃገረ ስብከታቸውን ምኞት በጉብኝታቸው ወቅት አጋርተዋል።

በሁለተኛ ደረጃ፣ ጉብኝታቸውን ያደረጉበት ስልት ራሱ በእውነት ወንድማማችነት የሚንጸባረቅበት ሲኖዶሳዊ ልምምድ ነው። በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ለሚገኙ ምእመናን ብቻ ሳይሆን በመላው አብረሃማዊ ቤተሰብ ቤት ውስጥ ለሚሰሩት ሁሉ በሰጡት ትኩረት እና አባትነት፣ የውይይት እና በክብር የመደማመጥን እድል ፈጥረዋል። ይህ ጉብኝት ሌላውን የማዳመጥ፣ በመንገዱ ላይ አብሮ ለመራመድ፣ አንዱ ሌላውን በአዎንታዊ ስሜት ለመቀበል የሚመረጥ የትምህርት ዘዴን የመሰከረ ነበር ማለት እንችላለን። ልዩነቶችን በመቀበል ማስተናገድ የሚችል ወንድማማችነት። ለዚህም ነው ጉብኝቱ ሲኖዶሳዊነትን በመለማመድ እና ከሁሉም በጎ ፈቃድ ካላቸው ሰዎች ጋር በመነጋገር ትልቅ ልምድ ሆኖልናል ያልነው።

በሶስተኛ ደረጃ፣ ምእመናን ከብጹእነታቸው ጋር ባደረጉት ውይይት የሰሙት የማበረታቻ እና የክርስቲያናዊ ተስፋ በአብርሃም ቤተሰብ ቤት ውስጥ ንቁ እና ተሳታፊ አካል ሆኖ ለመቀጠል ትልቅ እገዛ እና ጥንካሬ ሰጥተዋል።

ጥያቄ፦ አባ እስጢፋኖ፣ በዚህ ልዩ ቦታ አገልግሎትዎን ከጀመሩ አንድ ዓመት ሆኖታል፥ እንዴት እንደነበረ ሊነግሩን ይችላሉ?

መልስ፦ በጣም ጥሩ ነበር እላለሁ፣ በአከባቢው የሚገኘው የክርስቲያኑ ማህበረሰብ በቁጥር ብቻ ሳይሆን እያደገ ያለው የባለቤትነት ስሜትን እና በአሁኑ ጊዜ “እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው ፍላጎት” የሆነውን ልዩነቶችን በማክበር በሰላም አብሮ የመኖር ጥሪን እያሳደገ ነው።

እዚህ ያለው አገልግሎቴ በጣም የተጠናከረ እና በተለያዩ ዘርፎች የተዋቀረ ነው ፤ በመጀመሪያ ደረጃ በቅዱስ ፍራንቺስኮ ቤተ ክርስቲያናችን የሚመጡ ምእመናን የቅዱስ ቁርባን እና የሃዋሪያዊ ሥራ እንክብካቤ ማግኘታቸውን ማረጋገጥ ነው፣ በመቀጠልም የማዕከሉ ቀዳሚ ተግባር የሆነውን በትምህርት እና በሃይማኖቶች መካከል ለሚደረጉ የውይይት እንቅስቃሴዎች ድጋፍ እና ትብብር ማድረግ ነው። በመቀጠል በክርስቲያናዊ ሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይት አለ (በየወሩ የታይዜን ጸሎንት እናስተዋውቃለን) እና በመጨረሻም፥ ከመላው ዓለም ከተውጣጡ ግለሰቦች ጋር የሚደረጉ በርካታ ተቋማዊ ስብሰባዎችን መርሳት የለብንም፥ እነዚህ እኔ ያለኝ የአገልግሎት ገጽታ ነው።

ጥያቄ፦ ወደ ቅዱስ ፍራንቺስኮስ ቤተክርስቲያን በብዛት ማን እንደሚሄድ ቢነግሩን?

መልስ፦ አንድ በጣም ደስ የሚያሰኝ እና የሚያነቃቃው ነገር ወደ ቤተክርስቲያናችን የሚመጡት የክርስቲያን ማህበረሰብ ድብልቅ ነው። እንደሚታወቀው በመላው ሃገረ ስብከቶቻችን ያሉት የእምነት ማህበረሰባችን በስደተኞች የተዋቀረ ነው። ሁላችንም እዚህ ያለነው ካህናትም ሆኑ ምዕመናን ስደተኞች ነን። ብጹእ አቡነ ፓኦሎ ማርቲኔሊ በተለያዩ ጊዜያት ‘የጴንጤቆስጤ ሥነ መለኮት’ ስደተኞች ቦታን እና እራሳቸውን የሚገልጹበት የስደተኛ ቤተ ክርስቲያን ስፍራ የመሆንን ታላቅ እና አስደሳች ጥሪ አድርገዋል። በተለምዶ በሃገረ ስብከቶቹ ደብሮች ውስጥ ለሚገኙ የተለያዩ ቋንቋ እና ባህል ላላቸው ማህበረሰቦችን ልዩ ሃዋሪያዊ እንክብካቤ በመስጠት ለመደገፍ እንሞክራለን፥ ይህ በጣም አስፈላጊ ነው ምክንያቱም አንድ ሰው የራሱን ማንነት መጠበቅ አለበት፥ ወንጌል ውስጥ ለመካተት እና መስሎ ለመኖር የባህል ማንነትን ይጠይቃል። ይሁን እንጂ ይህ በቂ ሊሆን አይችልም፣ በእውነቱ፣ የአንዲት ቤተክርስቲያንን አካል ሆኖ ለመቀጠል ሁል ጊዜ ሚዛን መጠበቅ አስፈላጊ እውነታ ነው። በአንድ የጥምቀት ጥሪ ውስጥ ያለው አንድነት ራሱን መግለጥ እና ሁል ጊዜም መንከባከብ አለበት። እዚህ ላይ፣ የቅዱስ ፍራንቺኮ ቤተ ክርስቲያን ልዩ ኃላፊነት ለዚህ የጥምቀት አንድነት ጠንካራ ምልክት የሚሆን ይመስለኛል። በሌላ አነጋገር፣ ለሁሉም የካቶሊክ ማህበረሰባችን በፍራንቺስካዊያን መንፈሳዊነት ክርስቶስን የምንከተልበት የጋራ መንገድ እናቀርባለን። በዚህ መንገድ ከህንድ፣ ከፊሊፒንስ፣ ከአፍሪካ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ ወይም ከምዕራቡ የዓለም ክፍል ያሉ ምእመናን ለቅዱስ ቁርባን ብቻ ሳይሆን ለምናስተዋውቃቸው ሌሎች ተግባራትም አብረውን ይጣመራሉ።

ጥያቄ፦ የፍራንቺስካዊያንን መንፈሳዊነት ጠቅሰዋል፣ እባክዎ ለምን እንደሆነ ቢነግሩን? በተጨማሪም በዚህ የመጀመሪያ ዓመት ተግባራዊ ስላደረጓቸው ተግባራት አንዳንድ ተጨባጭ ምሳሌዎችን ሊሰጡን ይችላሉ?

መልስ፦ የፍራንቺስካውያን መንፈሳዊነት የሚመነጨው እዚህ ያለው ነገር ሁሉ ከአሲሲው ከቅዱስ ፍራንቺስኮ ጋር ሊያያዝ ስለሚችል ነው። እንደውም እ.አ.አ. በ2019 ቅዱስ አባታችን እና የአል-አዝሃሩ ታላቅ ኢማም በጋራ ለመጻፍና ለመፈራረም የወሰኑት ቅዱስ ፍራንቺስኮ እና የግብጹ ሱልጣን የተገናኙበትን ስምንት መቶኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ሲሆን፥ ይሄንን ‘የሰው ልጅ ወንድማማችነት ለዓለም ሰላም እና አብሮ መኖር’ በሚል ርዕስ የወጣው ታሪካዊ የጋራ ሰነድ የወጣበትም ጭምር ነው ማለት እንችላለን። በዚህ ሃሳብ፣ የኤምሬትስ መንግስት የአብርሃም ቤተሰብ ቤት እውን እንዲሆን ወሰነ። በዚህም ምክንያት የፍራንቺስካውያን መሰረት ያለው በመሆኑ ነው በአብርሃም መኖሪያ ቤት ውስጥ የሚገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ፕሬዝዳንት ክቡር ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል-ናህያን ለአሲሲ “ምስኪን” እና ለቅዱስ አባታችን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ስጦታ ያበረከቱት።

ሆኖም፣ በአሲሲው ፍራንቺስኮ እና በሱልጣን አል-ማሊክ አል-ከሚል መካከል በተከሰተው ያለፈ ክስተት ምክንያት ብቻ ሳይሆን ፍራንሲስካዊ ገጽታ እንዲኖረን እየመራን ያለነው፣ ነገር ግን የውይይት አቅም እና ሁለንተናዊ ወዳጅነት የፍራንሲስካውያን መንፈሳዊነት ግንዛቤም ጭምር ስለሆነ ነው።

ይህን ካልኩ በኋላ፣ አንድ ምሳሌ ልስጥ «አሥሩ የፍራንቺስካውያን ቃላት» በሚል ርዕስ የአዋቂዎች የትምህረት መርሃ ግብር አለ። በጥቂት ቃላት፣ የፍራንቺስኮን መንፈሳዊነት በአሥር ቃላት ተግባራዊ በማድረግ እንሻገራለን። ፕሮግራሙ በጣም ሰፊ ነው (ለሁለት ዓመታት ያህል የሚፈጀው ጊዜ ነው) እና እያንዳንዱን ቃል በአራት ፍራንቺስካውያን ምሰሶዎች በሆኑት የአእምሮ እውቀት፣ ጸሎት፣ መንፈሳዊ መጋራት እና ወንድማማችነትመሰረት በጥልቀት መገንዘብን ያካትታል።

ጥያቄ፦ እነዚህ ከቤተክርስቲያኑ ተግባራት ጥቂቶቹ ናቸው፥ እኔ እንደምገምተው ምኩራብ እና መስጊድ የየራሳቸው መብት አላቸው። በሃይማኖቶች መካከል ስለሚደረጉ ውይይቶችስ ምን ይላሉ? አሁን ስለጠቀሷቸው የውይይት እንቅስቃሴዎች ትንሽ ተጨማሪ ነገር ቢነግሩን?

መልስ፦ እርግጥ ነው። እያንዳንዱ የአምልኮ ቦታ ራሱን የቻለ እና ለእያንዳንዱ ማህበረሰቦች የራሱ የሆነ “የሃዋሪያዊ ሥራ ፕሮግራሞች እና ተግባራት” አለው፥ ይህ በጣም አስፈላጊ ነው፥ ምክንያቱም ልዩነታችንን ስለምንጠብቅ እና ስለምናከብር፣ እያንዳንዱም የሶስቱ ሃይማኖቶች የተለያየ እና የተለየ ቦታ አላቸው፥ ከእምነት እና ከሃይማኖት አንጻር ምንም አይነት ውህደት ወይም የተመሳሰለ ነገር በፍጹም የለም። ስለዚህ ያንን ካረጋገጥን በኋላ ‘ፎረም’ ብለን የምንጠራው አራተኛ ቦታ አለን። እዚህ ሁሉም ማህበረሰቦች ተገናኝተው የተለያዩ የእምነት ማህበረሰቦችን አንድ ላይ ለማምጣት፣ ለመነጋገር፣ ለመተዋወቅ እና የጋራ መግባባትን ለማጎልበት በተዘጋጁ አውደ ጥናቶች ላይ ይሳተፋሉ። ከሥነ ጥበባዊ ድርጊቶች ወደ ፓናል ውይይቶች ወይም የእሳት ዳር ውይይቶች የሚሄዱ ትምህርታዊ አውደ ጥናቶች አሉን። አንዳንድ ተግባራት በተለይ ለህጻናት ወይም ለወጣቶች የተነደፉ ናቸው ምክንያቱም ወጣቶች የአሁኑ እና የወደፊቱ ተስፋዎች ናቸው!

በፎረሙ ውስጥ የተከናወኑት ታላላቅ ስራዎች በሰው ልጅ ወንድማማችነት ሰነድ ውስጥ የተካተቱትን እሴቶች በማስተዋወቅ ላይ ይሽከረከራሉ፥ አስደሳች እና አነቃቂ ሆኖ ያገኘሁት ነገር ሰነዱን በሁለት የተግባር ደረጃዎች ማስተዋወቅ በመቻላችን ነው፡ የበለጠ ቲዎሬቲካል ወይም ትምህርታዊ እና በሰዎች የእለት ተእለት ህይወትን ያማከለ ነው። በትክክል ፎረም ተብሎ በሚጠራው በዚህ አራተኛው ቦታ የምንተገብረው ይህንን ነው፥ ምክንያቱም የመሰብሰቢያ እና የውይይት ቦታ ነው።

የአብረሃማዊ ቤተሰብ ቤት የባህል ማዕከል ወደሆነው በአቡ ዳቢ ግዛት አማካይ ቦታ ውስጥ ይገኛል፥ ምክንያቱም የውይይት ባህልን እና የሰውን ወንድማማችነት ባህል ስለምናስተዋውቅ ነው።

ጥያቄ፦ የሚገርመው 'የአብርሀም ቤተሰብ ቤት' የሚለው ስም የቤተሰብ እና የቤት ጽንሰ ሃሳብ መያዙ ነው። እነዚህ ቃላት ምን ትርጉም አላቸው?

መልስ፦ የአብርሀም ቤተሰብ ቤት ሶስት የአምልኮ ቤቶች እና አንድ 'ፎረም' ወይም መድረክ ያሉበት ተቋም፣ መሰብሰቢያ እና ማእከል ብቻ ሳይሆን፣ በትክክል እንደገለጽከው ቤተሰብንም የሚያካትት ነው፣ ከዛም ቤት የሚለውን ያካትታል።

በመጀመሪያ፣ የአብርሃም ቤተሰብ ቤት ሦስቱ የሃይማኖት መሪዎች የሚኖሩበት ቤት ነው ማለት አስፈላጊ ነው። እኔ ከቤተክርስቲያኑ ጀርባ መኖሪያ አለኝ፣ ረቢው ከምኩራብ ጀርባ፣ ኢማሙም ከመስጂዱ ጀርባ መኖሪያ ቤት አላቸው። ሶስታችንም የምንኖረው እዚህ ነው፣ የአብርሀም ቤተሰብ ቤት የኛ ቤት ነው። ይህ ወሳኝ ነገር ነው፥ ምክንያቱም በዓለም ዙሪያ ልዩ ነው ብዬ የማስበው ለጎረቤት፣ ለጓደኝነት ያለን ጥልቅ አክብሮት ትልቅ ምስክር ነው። በእኛ መካከል ያለው ይህ የቤት ስራ በአማኞች እና በቀኑ ውስጥ የአብርሃም ቤተሰብ ቤትን በሚጎበኙ ሰዎች መካከል ይሰማል ወይም ያስተጋባል። ሁሉም ሰው ከሃይማኖታዊ ትስስር ባሻገር “እነሆ እንደዚህ ያለ የሰላም፣ የወንድማማችነት እና አብሮ የመኖር መንፈስ ከዚህ በፊት ተሰምቶ አያውቅም” እያለ ተመሳሳይ አስተያየት መስጠቱን ይቀጥላል።

እዚህ ጋር በተጨባጭ እራሳችንን የምንገነዘበው ሁሉም የአንድ ሰው ቤተሰብ አባላት መሆናችንን እና ልዩነቶችን የሚያከብር ቤት ማቅረባችን በየራሳቸው እምነት መኖር እንዲችሉ የተለያየ ቦታዎችን እንደሚሰጥ ነገር ግን በተመሳሳይ ጊዜ ሁልጊዜ የውይይት እና የሰላም ቦታንም መፍጠር እንችላለን ብዬ አምናለሁ። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በአንድ ወቅት ‘አሁን እጅ ለእጅ ተያይዘን አንድ ላይ ለመጓዝ ትክክለኛው ጊዜ ነው፣ በተመሳሳይነት ሳይሆን አንድነትን በልዩነት፣ የምንኖርበት ማህበረሰቦችን እና ህብረተሰብን የምንፈጥርበት ጊዜው አሁን ነው” ብለው የተናገሩትን እውን የማድረጊያው ጊዜ ደርሷል ለማለት ነው።

ጥያቄ፦ ወደ ብጹእ አቡነ ማርትኔሊ ሃዋሪያዊ ጉብኝት ስንመለስ በጉብኝቱ ወቅት ለማህበረሰቡ ያስተላለፉት መልዕክት ምንድነው?

መልስ፦ ብጹእነታቸ በንግግራቸው ወቅት ሶስት ዋና ዋና ጭብጦችን አስተላልፈዋል። በመጀመሪያ ደረጃ የቤተ ክርስቲያናችንን ልዩ ገጽታ አጉልተው ሲገልጹ “ይህች ቤተ ክርስቲያን የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ፕሬዝዳንት ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ነኸያን ለቅዱስ አባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ያበረከቱት እና ለሐዋርያዊ ሥራ ለደቡብ አረቢያ አህጉረ ስብከት በአደራ የተሰጠች ቤተ ክርስቲያን ናት" ብለው ነበር። ስለዚህ በዓለም ላይ ልዩ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ነች ማለት ነው። ይህ ማለት ደግሞ የቅዱስ ፍራንቺስኮ ቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ማዕቀፍ የሚገልጹትን ፍትሕን፣ ሰላምን፣ ነፃነትን፣ ትምህርትን፣ ወንድማማችነትን እና ውይይትን የሚቀርጹትን እሴቶች የመምራት እና የመኖር አስደሳች ኃላፊነትንም ያመለክታል። ብጹእነታቸው የኖሩትም በውይይት ባህል ውስጥ ነው፡ ብጹእነታቸውም “ከተለያዩ እምነት ተከታዮች ጋር የሚደረግ ውይይት በመሻት ብቻ የሚደረግ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊም ጭምር ነው። ይህ የጥቂት ምሁራን ቡድንን ብቻ የሚመለከት ጉዳይ ሳይሆን፥ ሁሉንም ምዕመናን ይመለከታል” በማለት አበክረው ተናግረዋል።

ሁለተኛው ያነሱት ነጥብ መላውን የእምነቱን ማህበረሰብ በጥልቅ ያነሳሳ ጉዳይ ነው፥ ይህም የመጀመርያው የክርስቲያን ማህበረሰብ የተገለፀበት የሐዋርያት ስራ ምንባብ ማብራሪያ ነበር፣ ብጹእነታቸው ከዚህ ፅሁፍ ሶስት ተጨባጭ የማህበረሰቡን ህይወት አቅጣጫዎችን የሚያሳዩ ነጥቦችን አውጥተዋል፡-የመጀመሪያው አንድ አምላክን ማምለክ እና ጸሎት ሲሆን ሁለተኛው የክርስቲያን ምስረታ ነው፥ ሶስተኛው እና የመጨረሻው በጎ አድራጎት እና የህይወት ምስክርነት የሚሉት ናቸው።

ብዙ ብሄረሰቦች እና የተለያየ ባህል ያላቸው ማህበረሰቦች እንደነበሩባት የመጀመሪያዎቹ የክርስቲያን ማህበረሰቦች፣ እንደዚሁም እዚህ ያለችው ቤተክርስቲያን የተጠራችው በአንድ ጥልቅ ወንድማማችነት ህብረት ውስጥ እንድትኖር በክርስቶስ ውስጥ የአንድ ሰማያዊ አባት ወንድ እና ሴት ልጆች መሆናቸውን በማወቅ ነው።

ሦስተኛው ነጥብ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የቀረበውን ጥሪ እና አመለካከት እንድንይዝ ሁላችንንም የምትወክለውን የቅዱስ ፍራንቺስኮ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ዕድል ያጎላ ነበር። እንዲያውም ብጹእ አቡነ ፓኦሎ ማርቲኔሊ ምእመናን ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር ያላቸው ልዩነት እንቅፋት እንዳልሆነ እንዲገነዘቡ ረድተዋቸዋል፥ ነገር ግን በተቃራኒው እያንዳንዳችን በደንብ እንድንተዋወቅና የራሳችንን የእምነት መሰረት ይበልጥ እንድናጠናክር ይረዱናል። “ወደዚህ ቤተክርስቲያን ለቅዱስ ቁርባን ወይም ለአፍታ ፀሎት ስትመጡ ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን በተጨማሪ ሌሎች ሁለት የጸሎት ስፍራዎች ማለትም መስጊድ እና ምኩራብ ወደሚገኝበት ስፍራ መምጣታችሁን ትረዳላችሁ" ። በዚህ መንገድ፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስትሄድ በተፈጥሮ የሌሎች ሃይማኖቶች መኖራቸውን እንድትገነዘብ እና ሰላማዊ እና ገንቢ የሆነ የአብሮ መኖር እሳቤ እንዲኖርህ ትበረታታለህ። ምእመናኖቻችን ሌሎች የአምልኮ ቦታዎች መኖራቸውን ሳያውቁ ቤተ ክርስቲያናቸውን ማሰብ አይችሉም። ከሌሎች ሀይማኖቶች ጋር ባለን ግንኙነት ልዩነቶችን ማክበር እና ስለእምነታችን ግንዛቤን ማሳደግ ነው። ምዕመኑ ከእሱ ሃይማኖት የተለየውን ሲያውቅ፣ የራሱን እምነት በደንብ ያውቃል።

ጥያቄ፦ የቅዱስ ፍራንቺስኮ ቤተክርስቲያን የወደፊት እይታዎች የትኞቹ ናቸው?

መልስ፦ ይህ ነው ለማለት አስቸጋሪ ነው። በእርግጠኝነት ለመናገር ግን የቤተክርስቲያናችን ራእይ በሰብአዊ ወንድማማችነት ሰነድ ውስጥ የተካተቱትን እሴቶች ከእረኝነት አገልግሎት አንፃር፣ እንዲሁም ከሥነ መለኮት እይታ አንጻር በማስተዋወቅ መቀጠል ነው። በአብርሃም ቤተሰብ ቤት የሚገኘው የቅዱስ ፍራንቺስኮ ቤተክርስቲያን በዚያ ሀገር ውስጥ ለሚኖሩ ምእመናን ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ላሉ ቤተክርስቲያናት ሁሉ አስደሳች ቋሚ ቤተ ሙከራ የመሆን አቅም አለው። በተለያዩ እምነቶች መካከል ጥልቅ እና እውነተኛ ግንኙነቶችን ማበልጸግ የዕለት ተዕለት ጸጋ የሆነበት አዲስ “የጴንጤ ቆስጤ ሥነ-መለኮት” የሚኖርበት ቦታ ሊሆን ይችላል። ልዩነቶች እንደ አስፈላጊ እና ተጨማሪ አካላት እንደሚታዩበት እንደ አንድ በጥሩ ሁኔታ የተዋሃደ የኦኬስትራ ሙዚቃ የሚታዩበት ቦታ ነው። ነገር ግን አሁንም እንደገና እላለሁ ይህ ለመናገር አስቸጋሪ ነው፥ መንፈስ ቅዱስ ወዴት እንደሚመራን ወደፊት በጋራ እናያለን።
 

24 June 2024, 21:45