ገዳማዊያቱ የጎረጎሳዊያኑ የ2024  የካቶሊክ ገዳማዊያት እህቶች ተነሳሽነት ጉባኤ ላይ- ዛምቢያ፣ ሉሳካ ገዳማዊያቱ የጎረጎሳዊያኑ የ2024 የካቶሊክ ገዳማዊያት እህቶች ተነሳሽነት ጉባኤ ላይ- ዛምቢያ፣ ሉሳካ 

የካቶሊክ ገዳማዊያት ጉባኤ ላይ ገዳማዊያቱ ለጋራ ጥቅም አገልግሎት መተባበር እንዳለባቸው ተገለጸ

‘ኮንራድ ኤን ሒልተን ፋውንዴሽን’ ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ከ15 ሃገራት በላይ የተውጣጡ የካቶሊክ ገዳማዊያት በዛምቢያ የተሰባሰቡ ሲሆን፥ የጋራ ራዕያቸው በሆነው ተፅእኖ መፍጠር፣ መማር እና በጋራ ጥቅም አገልግሎት መተባበር በሚለው ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከ15 ሃገራት በላይ የተውጣጡ ከ100 የሚበልጡ ገዳማዊያት እህቶች የዛምቢያ መዲና በሆነችው ሉሳካ ከተማ ከግንቦት 21 እስከ 23/ 2016 ዓ.ም. ድረስ የካቶሊክ ገዳማዊያት ንቅናቄ የሆነው ‘ኮንራድ ኤን ሒልተን ፋውንዴሽን’ ባዘጋጀው ክልላዊ ጉባኤ ላይ ተሰብስበው ነበር።

የዝግጅቱ ዓላማ የሲኖዶሳዊነትን ግንዛቤ እና ልምምድ ለማጎልበት እና ሀሳቦችን ለመለዋወጥ፣ በተጨማሪም የጋራ መግባባትን ለስልታዊ ተፅእኖ እና እድገት እንዲሁም ለጋራ ጥቅም ቀጣይነት ያለው ትብብር ለመፍጠር ያለመ እንደሆነም ተነግሯል።

“እንደዚህ ዓይነት ጉባኤዎች የጋራ ጥረቶቻችንን ጥራት እና ዘላቂነት ለማጠናከር እንዲሁም ለአዳዲስ ግንኙነቶች በር ለመክፈት ብሎም ከዚህ በፊት ይደረጉ የነበሩ ግንኙነቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እድል ይሰጣሉ” ሲሉ የፕሮግራም ትግበራ ተባባሪ ምክትል ፕሬዝዳንት እና በኮንራድ ኤን ሂልተን ፋውንዴሽን የካቶሊክ እህቶች ንቅናቄ መሪ የሆኑት ሲስተር ጄን ዋካሂዩ ተናግረዋል።

በስብሰባው ወቅት ገዳማዊያቱ ከተወያዩባቸው ጉዳዮች ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን ድምጽ ማሰማት ስለሚቻልባቸው መንገዶች፣ ጠንካራ ሃይማኖታዊ ማህበረሰቦችን ለማፍራት በማስረጃ የተደገፈ አቀራረብን መከተል እና ለጋራ ተጠቃሚነት ስር የሰደዱ ጎጂ ባህላዊ ልምዶችን መቀየር በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተወያዩ ሲሆን፥ የገዳማዊያቱን ሃሳቦች አንድ ያደረገው ነገር ወርቃማ ገመድ የሆነው ሲኖዶሳዊነት እንደሆነም ተነግሯል።

ገዳማዊያን በቤተክርስቲያን ውስጥ የግንኙነት ዋና ተዋናዮች ናቸው

ሲኖዶሳዊነትን አስመልክቶ በተደረገው የውይይት ክፍል ላይ፥ የቫቲካን ተወካዮች የቅድስት መንበር ሃዋሪያዊ ጽ/ቤት ተልእኮ እና ሃዋሪያዊ ሥራ ኃላፊነት ላይ እንዲሁም ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ውይይት አድርገዋል። የውይይት መድረኩ የተመራው ‘ፍሬንድስ ኢን ሶሊዳሪቲ’ የተባለ ማህበር ፕሬዝዳንት በሆኑት በሲስተር ሙምቢ ኪጉታ ሲሆን፥ በውይይቱ ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የማዳመጥ፣ የትብብር እና የኅብረት አስፈላጊነት ላይ የተናገሩትን በማስታወስ ንግግር አድርገዋል።

በጉባኤው ላይ የቅድስት መንበር የተግባቦት ጽ/ቤት ሃላፊ ዶ/ር ፓኦሎ ሩፊኒ እንደተናገሩት በዓለም ላይ ያሉ የካቶሊክ ገዳማዊያት እህቶች ሥራ በገሃድ እንዲታይ በጋራ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው በመናገር፥ “አገናኝ ገዳማዊያቱ ክርስቲያናዊ አመለካከትን በማቅረብ በቤተክርስቲያን ውስጥ የግንኙነት ዋና ተዋናይ መሆን አለባቸው” ብለዋል። ሃላፊው አክለውም እንደተናገሩት የተለያዩ ታሪኮች ሲነገሩ ከተጎጂው በኩል ሆነው ለመነገር ክፍት መሆን እንዳለባቸው አሳስበው፥ “በህብረተሰቡ ጥቅም ላይ ያተኮረ አዲስ የግንኙነት መንገድ መፍጠር አለባችሁ” በማለት አሳስበዋል።

የቅድስት መንበር የግንኙነት ጽ/ቤቱ ከእያንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ጋር በህብረት ስለሚሰራ፥ ከአጥቢያ ቤተክርስቲያን ተነስቶ እስከ ቫቲካን ድረስ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስተዳዳሪው አጽንዖት ሰጥተው ተናግረው፥ “በሲኖዶሳዊ መንፈስ ውስጥ ለጋራ ጥቅም ትብብር እና ትስስር ዋናው ጉዳይ ነው” ብለዋል።

ዶ/ር ሩፊኒ በሂልተን ፋውንዴሽን የሚደገፈውን የጽ/ቤቱን የጴንጤቆስጤ ፕሮጄክትን በማንሳት ከካቶሊክ ገዳማዊያት የግንኙነት ባለሙያዎች ጋር ትስስር እና ትብብርን በመፍጠር የሲኖዶሳዊነት ምሳሌ መሆኑን አሳይቷል ብለዋል። የጰንጠቆስጤ ፕሮጀክት በቫቲካን ሚዲያ ውስጥ ዓለምአቀፍ የገዳማዊያት ትስስር ድምጽ ለመፍጠር እንደሚፈልግም ገልጸዋል።

ዶ/ር ሩፊኒ ፕሮጀክቱ ገዳማዊያቱ በተግባቦት ላይ ያላቸውን ዕውቀት ለማሳደግ ከኦንላይን ፎርሜሽን ኮርሶች እና ዌብናሮች ጀምሮ የቫቲካን ሬድዮ ጣቢያ በአካል ተገኝተው እንዲለማመዱ እድል እንደሚሰጥ የገለጹ ሲሆን፥ ይህም አዲስ የትብብር እድል ይፈጥራል ብለዋል።

በቫቲካን ዜና ውስጥ በሚገኘው በቫቲካን ራዲዮ ከ12 ሀገራት የተውጣጡ 13 ገዳማዊያን እህቶች በስልጠና ላይ እንደሚገኙ፥ በአሁኑ ወቅትም የ2024 የካቶሊክ ገዳማዊያት እህቶች ቡድን ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ባሉት 12 ሳምንታዊ የዙም ስብሰባዎች ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የመስማት እና የመተባበር አስፈላጊነት

የቅድስት መንበር የቅድስና ሕይወት እና የሐዋርያዊ ሕይወት ማኅበረሰብ የትምህርት ማዕከሎች ጽ/ቤት ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት ሲስተር ካርመን ሮዝ ኖርቴስ ስለ ሲኖዶሳዊነት በማንሳት ጳጳሳዊ ጽ/ቤቱ ለቅድስና ሕይወት ያለውን ቁርጠኝነት አጉልተዋል። ምክትል አስተዳዳሪዋ ስለ ጳጳሳዊ ጽ/ቤቱ አስፈላጊነት ሲገልጹ “ጽ/ቤቱ በተለያዩ ልግስና እና አገልግሎት መካከል እንዳሉ ግንኙነቶች ወይም የቤተክርስቲያኑ ውበት እንደሚታይበት ቤተ-ሙከራ ሊታይ ይችላል” ሲሉ ተናግረዋል።

የሲኖዶሱ ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሃፊ የሆኑት ሲስተር ናታሊ ቤክኳርት በበኩላቸው መደማመጥ እና በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተው በመግለጽ፥ “ገዳማዊያት እህቶች በሲኖዶሱ ሂደት ውስጥ ትልቅ ሚና አላቸው፥ ምክንያቱም ደግሞ በሂደቱ ገና ከጅምሩ ስለሚሳተፉ ነው፥ በመሆኑም የእግዚአብሔርን ህዝብ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘይቤ የሆነውን ሲኖዶሳዊ ዘይቤ እንዲቀበሉ መርዳት አለባቸው” ብልዋል።

አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በስደት ጉዳዮች ላይ መስራት አለባቸው

ስለ ስደት ጉዳይ በማንሳት ለምክክር መድረኩ ያቀረቡት የቅድስት መንበር የተቀናጀ የሰው ልጅ ልማት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ጸሃፊ የሆኑት ሲስተር አሌሳንድራ ስሜሪሊ ሲሆኑ፥ የጽ/ቤቱ አንዱ ተግባር የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ለስደት ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ እንቅፋቶችን እንዲያስወግዱ መርዳት እንደሆነ አስረድተዋል።

“የግዳጅ ስደት ከብጹአን ጳጳሳት እና ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ጋር እየሠራንበት ያለነው ትልቁ ተግዳሮት ነው፤ ይህንን ችግር ለመፍታት ጳጳሳቱ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለስልጣናት ጋር እንዲሠሩ ጥሪያችንን እናቀርባለን” ብለዋል ሲስተር አሌሳንድራ።

ሲስተሯ በተጨማሪም ጉዟቸው ምንም ይሁን ምን፣ ስደተኞች አሁንም የአንዲት ቤተክርስቲያን አባል እንደሆኑ እና የትም ቢሆኑ እርዳታ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ካሳሰቡ በኋላ፥ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ለስደተኞቹ ተገቢውን የሃዋሪያዊ ሥራ እንክብካቤ አድርገው ሊሸኟቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሲስተር አሌሳንድራ ስሜሪሊ በመጨረሻም “እግዚአብሔር ከህዝቡ ጋር ይራመዳል” የሚለውን የዘንድሮውን የዓለም የስደተኞች እና የፍልሰተኞች ቀን መሪ ቃል አስታውሰው፥ እያንዳንዱ ሰው ተገደው ወደ ስደት የገቡ ሰዎች ውስጥ የእግዚአብሔርን ፊት ማስተዋል እንዲችል እንደተጠራ አጉልተው አንስተዋል።
 

04 June 2024, 17:10