የኢየሱስ ቅዱስ ልብ ምስል የኢየሱስ ቅዱስ ልብ ምስል 

እኔ በሥራቸው ሁሉ በረከቴን በዛ አድርጌ አፈስባቸዋልሁ

የኢየሱስ ቅዱስ ልብ ለሚወዱት ጸጋ በጸጋ ላይ እጨምርላቸዋለሁ በሚገልጡለት የፍቅር ምልክት እጥፍ ድርብ አድርጐ ሊጨምርላቸው ፈቃዱ ነው። በሕይወታቸው ሳሉ ከእነርሱ ጋር ሆኖ በሥራቸው ሊያግዛቸው ውሳኔው ነው። “እኔ በሥራቸው በረከቴን በዛ አድርጌ አፈስላቸዋለሁ። ዋና ፈቃዴ ይህ ነው” እያለ ተስፋ ይሰጣቸዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

የአምላክ ቡራኬ ያለው ሥራ መልካምና የሚያስደስት ይሆናል። በሥራቸው የቅዱስ ልብ ቡራኬ ያላቸው የታደሉ ናቸው። የእርሱ በረከት የድካማቸውን ዋጋ ሊያስገኝላቸው ብርሃንና ኃይል ሊሆናቸው ነው። በቅዱስ ልብ ታግዘው መንፈሳዊ ጉዳያቸውን በጥሩ ሁኔታ የሚፈጽሙት የልባቸውን መንፈሳዊ ምኞታቸውን ሊያቃኑ መንፈሳዊ ተግባራቸውን በትጋት ሊያከናውኑ ይችላሉ።

በሥራቸው የሚገጥማቸውን ፍርሃት፣ ጥርጣሬ፣ ፈተናና ጭንቀት የሚያሸንፉበትን ሰማያዊ ኃይል ይሰጣቸዋል። የቅዱስ ልብ ቡራኬ ዕርዳታ ከወረደላቸው ሐሳባቸውና ቁርጥ ፈቃዳቸው ይሳካልና ወደ ፍጻሜው ይደርሳል። የቅዱስ ልብ ቡራኬ በሁሉ ይመራቸዋል። በመልካም አኳኋን አስጀምሮ በመልካም ሁኔታ ያስፈጽማቸዋል። ጠንካሮችና ረጋ ያሉ ያደርግቸዋል። በመንፈስም ረገድ በመነቃቃት ወደ ፊት እንዲራመዱና እየቀጠሉ እንዲሄዱ ያደርጋቸዋል።

ቡራኬው ለሥጋዊ ሥራ ቅዱስ ልብን ለሚያገለግሉት በመንፈስ ሳይሆን በሥጋ ጭምር እንዲረዳቸውና እንዲያስደስታቸው ይፈልጋል። በሁሉም እነርሱን ለመረዳትና ለማገዝ ምንምጊዜም ወደ ኋላ አይልም። መንፈሳዊ ሥራቸው እንደሚባረክላቸው እንዲሁም ሥጋዊ ሥራቸውም እንዲባረክላቸው ይፈልጋል። በቡራኬው ታግዘው ሥራቸውን ጥሩ አድርገው ያቃናሉ። ባላሰለሰና በማያቋርጥ ጥረታቸው ለዘለዓለም የሚያገለግላቸውንና የሚጠቅማቸውን ብዙ ፍሬ ያከማቻሉ። በዕርዳታው እገዛ ብርታት ኑሮአቸውን ያሻሸላሉ። በችግራቸው ጊዜም የደረሰባቸውን መከራ ለማቃለልና ፈተናውን ለመወጣት የሚያስችላቸውን ትዕግሥትና ተስፋ ያገኛሉ። በዕርዳታው አማካይነት ኑሮአቸው ይሻሻላል የልባቸው ሐሳብ ሐቅ በመሆን ይቀናቸዋል።

“ካለ እኔ ምንም ልትደርጉ አትችሉም” (ዮሐ. 15፣5) ይለናል ኢየሱስ። “ቤትን እግዚአብሔር ካላነጸው የሚሠሩት ሰዎች በከንቱ ይለፋሉ” (መዝ. 125) ይላል ዳዊት። ቤተክርስቲያን “ሥራችን በአንተ ተጀምሮ በአንተ ያልቃል በአንተ ይፈጸማል” እያለች ጸሎቷን ወደ እግዚአብሔር ታደርጋለች።

በሥራችን ቅዱስ ልብ የሚጐድለን ስለሆነ ብዙ ጊዜ በውጥኑ ወይም ግማሽ ሆኖ ሳንቋጨው አስጠልቶን እንተወዋለን። ሁሉ ነገር ብትንትን ብሎ ይቀራል። መንፈሳዊና ሥጋዊ ዕቅድ ብዙ ጊዜ ተጀምሮ ፍጻሜ ሳያገኝ ተሰነካክሎ መቅረቱ የሚያሳዝን ነው። ስለዚህ ብቻችንን ምንም ማድረግ አንችልም። ይህ የክርስቶስ የማይሳሳት ቃል ነው። እና ደካሞች ነን በመሆኑም በራሳችን ተማምነን የምንጀምረው ሥራ ግቡን ሳይመታ ይቀራል። ትዕግሥት የለንም ትዕግሥታችን በጣም አነስተኛ ነው። እንግዲህ ይህንን አውቀን ለራሳችን ከሁሉ አስቀድመን የቅዱስ ልብ ቡራኬንና እገዛ እንለምን። በእርሱ እገዛ ተደግፈን እንጀምረውና እንፈጽመው።

 

05 June 2024, 14:58