ከተለያዩ ጉባኤያት የተውጣጡ ገዳማዊያት ‘የግንኙነት አውታረ መረብ ለካቶሊክ እህቶች'  ምረቃ ላይ ከተለያዩ ጉባኤያት የተውጣጡ ገዳማዊያት ‘የግንኙነት አውታረ መረብ ለካቶሊክ እህቶች' ምረቃ ላይ  

በኬንያ የመገናኛ አውታረ መረቦች ገዳማዊያትን ለማብቃት እና ወንጌልን ለማሰራጨት ይጠቅማል ተባለ

በኬንያ የሚገኙ የካቶሊክ ገዳማዊያን ‘የግንኙነት አውታረ መረብ ለካቶሊክ እህቶች’ (CNCS) የተሰኘ አውታረ መረብ መጀመራቸው ተገልጿል። ዳይሬክተሯ ሲስተር ሚሼል ንጄሪ እንደገለጹት፣ “ራእያችን በማህበራዊ ለውጥ ታሪኮች አማካይነት ወንጌልን በማሰራጨት ጠንካራ የካቶሊክ እህቶች ትስስር መሆን ነው” ብለዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በኬንያ የሚገኙ የካቶሊክ ገዳማዊያት እህቶች ‘የኬንያ እህትማማችነት ማኅበር’ (AOSK) ጥላ ሥር ‘ለካቶሊክ እህቶች የግንኙነት አውታረ መረብ’ የሚል ትስስር በይፋ ከፍተዋል። ይህ አዲስ አውታረ መረብ ገዳማዊያቱ ሚዲያን ለማህበራዊ ለውጥ ለመጠቀም ያላቸውን ቁርጠኝነት በመግለጽ፣  በዘመናዊ ማህበራዊ ግንኙነት የወንጌል ስርጭትን ለማሳደግ ያለመ ነው ተብሏል።

የመክፈቻው ዝግጅቱም አርብ ሰኔ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. የተካሄደ ሲሆን፥ ዓላማው ገዳማዊያቱን በዚህ በዲጂታል ዘመን ጋር እንዲራመዱ የሚያስፈልጉ ክህሎቶችን ማስታጠቅ በሆነበት እና 13 ባለሙያ ገዳማዊያትና የተግባቦት ባለሙያዎች በኮሚዩኒኬሽን የሰለጠኑበት፣ ብሎም ስለ ትስስሩ ዓላማዎች ስልጠና የወሰዱበት፣ በናይሮቢ በተዘጋጀው የሁለት ቀናት የቅድመ አውደ ጥናትን ተከትሎ ነው።

የማህበራዊ ሚዲያ ደህንነት እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ስልጠና

የመሰናዶ አውደ ጥናቱ የተመራው በሙያው በቂ ዕውቀት ባለው በታዋቂው ኤክስፐርት አቶ ኬኔዲ ካችዋንያ ሲሆን፥ በማህበራዊ ሚዲያ ደህንነት፣ ጥበቃ እና የሳይበር ጥቃት ላይ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደዋል። ባለሙያው በማህበራዊ መድረኮች ላይ የሳይበር ጥቃት ማጋጠሙ የማይቀር መሆኑን ገልፀው፥ ገዳማዊያቱ በጸጋ እና በስብከተ ወንጌል መንፈስ ምላሽ እንዲሰጡ መክረው፥ “በማህበራዊ ምህዳር የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ወንጌልን በመስበክ እና ህዝቡን ለመለወጥ ልንጠቀምበት ይገባል” ሲሉም ገዳማዊያቱ እህቶች በአውታረ መረቡ በሚያደርጉት ግንኙነቶቻቸው መግባባትን እና ርህራሄን የማሳደግ ተልእኮአቸውን ጠቁመዋል።

በአውደ ጥናቱ ወቅት በወንድም ኤሊያስ ሞኩካ መሪነት በሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ - AI) ላይ ጉልህ ትኩረት ተደርጎ ስልጠና የተሰጠበት ሲሆን፥ በመገናኛ ዘርፍ ውስጥ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን የመለወጥ አቅምን በማጉላት፥ “ሰው ሰራሽ አስተውሎት ለፈጠራ ብዙ ዕድል ይሰጠናል፥ የአስተሳሰብ አድማሳችንን እንደገና እንድናጤን እና ወደፊት ለመራመድ ልንጠቀምበት ይገባል” ብለዋል።

ይህ መርሃ ግብር ገዳማዊያቱ እህቶች ሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ ያላቸውን ዕውቀት ለማስፋት እና ውጤታማ የወንጌል ስርጭት እና ትምህርተ ክርስቶስን እንዲያስፋፉበት ተብሎ የተዘጋጀ ነበር ተብሏል።

መነገር ያለባቸው ታሪኮች

በማስጀመሪያ ሥነ ስርዓቱ ላይ ከተገኙት ተወካዮች መሃል ከኮንራድ ኤን ሂልተን ፋውንዴሽን የፕሮግራም ትግበራ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የካቶሊክ እህቶች ህብረት ኃላፊ የሆኑት ሲስተር ጄን ዋካሂዩ፣ አንጀሊክ ሙቶምቦ የአፍሪካ ኢኒሼቲቭ የካቶሊክ ገዳማዊያት እህቶች ከፍተኛ የፕሮግራም ኦፊሰር እና የአፍሪካ ካቶሊክ እህቶች ተነሳሽነት ፕሮግራም ኦፊሰር ሲስተር አግነስ ንጄሪን ጨምሮ የኬንያ እህትማማቾች ማኅበር ሊቀመንበር (AOSK) ሲስተር ጆሴፊን ካንጎጎ እና ‘የግንኙነት መረብ ለካቶሊክ እህቶች’ የቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ክርስቲን ንጉኩ እንዲሁም ከኬንያ ሚዲያ ካውንስል እና ከተለያዩ የካቶሊክ ሚዲያ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።

ሲስተር ጄን ዋካሂዩ ከአውታረ መረቡ ውጥን እስከ ጅማሮው ድረስ የነበረውን ጉዞ በማብራራት የተሰማቸውን ደስታ እና ምስጋና ለተሳታፊዎቹ ሲገልጹ፥ “ይህ አውታረ መረብ በአንድ ወቅት ህልም ነበር፣ ነገር ግን በህብረት ባደረግነው ጥረት እና በትልልቅ አስተሳሰቦች እውን ሊሆን ችሏል፥ ገዳማዊያት እህቶች በርህራሄ እና በጥንቃቄ ሊነገሩ የሚገቡ የተስፋ፣ የፍቅር እና የጥንካሬ ታሪኮች አሏቸው፥ አውታረ መረቡ ለዚህ ያገለግላል” ካሉ በኋላ ገዳማዊያቱ እህቶች በኢየሱስ አይን እና በፈውስ ተልእኮአቸው ተመርኩዘው ታሪኮቻቸውን ለማካፈል አውታረ መረቡን እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።

ሲስተር ካንጎጎ በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን የመግባቢያ ወሳኝ ሚና በማንሳት “ግንኙነት የእያንዳንዱ ተራማጅ ማህበረሰብ እና የእለት ተእለት ህይወት ደም ነው። ትክክለኛ እና ተአማኒነት ያለው መረጃ መስጠት ከሁሉም በላይ ነው” በማለት አጽንኦት ሰጥተዋል።

ይህ የትስስር አውታረ መረብ ገዳማዊያት እህቶች ታሪካቸውን በትክክል እና በግልጽ እንዲያካፍሉ እንደሚያስችላቸው፣ በዚህም የወንጌል አገልግሎት ጥረታቸውን እና ድምጽ ለሌላቸው ሰዎች መሟገትን እንደሚያጠናክር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

‘የግንኙነት አውታረ መረብ ለካቶሊክ እህቶች’ የገንዘብ ድጋፍ የተደረገው በኮንራድ ኤን ሂልተን ፋውንዴሽን ሲሆን፥ ተቋሙ የካቶሊክ ገዳማዊያት እህቶችን ለመደገፍ የረጅም ጊዜ ቁርጠኝነት እንዳለው ተገልጿል። ሲስተር ዋካሂዩ የፋውንዴሽኑን እምነት በማጉላት “ልግስና የበጎነት ውሃ ልክ ነው” በማለት፥ ፋውንዴሽኑ በገዳማዊያቱ ያላሰለሰ ጥረት እና የርህራሄ ልብ አማካይነት የሰውን ልጅ ስቃይ ለመቅረፍ የሚሰሩትን ሥራ ለማበረታታት የሚያደርገውን ድጋፍ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመገናኛ ብዙሃን አማካይነት ህብረተሰቡ ላይ ተጽእኖ ማሳደር

የአውታረ መረቡ ዳይሬክተር የሆኑት ሲስተር ሚሼል ንጄሪ ከተለያዩ ጉባኤያት ለተውጣጡ ገዳማዊያት እህቶች አንድ ወጥ የሆነ የግንኙነት መስመር ለማቅረብ ተብሎ የተዘጋጀ መሆኑን በመግለጽ፣ “ይህ አውታረ መረብ በመገናኛ ብዙኃን የምንሰጠውን የወንጌል አገልግሎት አቅማችንን ለማሳደግ፣ በመካከላችን የበለጠ ትስስር እና ትብብር ለመፍጠር ያለመ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

አውታረ መረቡ ለካቶሊክ እህቶች የተለያዩ ሐዋሪያዊ ሥራዎችን ለስብከተ ወንጌል እና ለማህበራዊ ለውጥ በመዘገብ ድምፃቸውን የሚያሰሙበት መድረክ እንደሚያዘጋጅ ሲስተር ንጄሪ አጽንኦት ሰጥተዋል። “አውታረ መረቡ የሚመራው ዋና እሴቶቹ በሆኑት በጸሎት፣ ታማኝነት፣ ተጠያቂነት፣ መከባበር፣ ልዩነት፣ ትስስር እና አጋርነት ነው” ሲሉም አክለዋል።

ሲስተር ንጄሪ “ራዕያችን በማህበራዊ ለውጥ ታሪኮች ወንጌልን በመስበክ ኃይል ያላቸው የካቶሊክ እህቶች ጠንካራ አውታር መሆን ነው” ሲሉ በአውታረ መረቡ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ተናግረዋል። በማከልም ታሪኮቻችንን በማካፈል ለውጥን ለማነሳሳት እና በህብረተሰቡ ውስጥ ጥልቅ ግንዛቤን እና ርህራሄን ለማዳበር አላማ እናደርጋለን ብለዋል።

በኬንያ ለሚገኙ የካቶሊክ እህቶች አዲስ ዘመን ነው

ይህ የግንኙነት አውታረ መረብ ለካቶሊክ እህቶች ትስስር መጀመሩ በኬንያ ላሉ የካቶሊክ እህቶች አዲስ ዘመን ነው። ገዳማዊያቱ ዘመናዊ የመገናኛ መሳሪያዎችን እና መድረኮችን በመቀበል የስብከተ ወንጌል ጥረታቸውን እያሳደጉ በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደሩ ነው። በተስፋ፣ በፍቅር እና በጥንካሬ ታሪኮቻቸው አማካኝነት የበለጠ ሩህሩህ እና አስተዋይ ዓለምን እያሳደጉ ነው። እህቶች በዚህ አዲስ መድረክ እየገሰገሱ ሲሄዱ ጥልቅ ታሪኮቻቸውን እና መልእክቶቻቸውን ለብዙ ተመልካቾች በማካፈል በህብረተሰቡ ውስጥ የበለጠ ግንዛቤን እና ርህራሄን በማጎልበት፣ ይህ በዲጂታል ዘመን የብርሃን ፍንጣቂ እና የለውጥ ጊዜ ሆኖ እንደሚቀጥል ምንም ጥርጥር የለውም ተብሏል።
 

20 June 2024, 17:01