የ 'ኮርፐስ ክሪስቲ' ኮንሰርት በፖላንዷ ሪዜዞው ከተማ ሲከበር የ 'ኮርፐስ ክሪስቲ' ኮንሰርት በፖላንዷ ሪዜዞው ከተማ ሲከበር   (Tadeusz Pozniak)

በፖላንድ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ‘ኮርፐስ ክሪስቲ’ በሚባለው ሥርዓተ አምልኮ ዝግጅት ላይ ተሳተፉ

‘ኮርፐስ ክርስቲ’ ተብሎ በጎርጎሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ግንቦት 25 ቀን 2016 ዓ.ም. የተከበረው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ሥጋው እና ክቡር ደሙ የሚታወስበት ክብረ በዓል ላይ ከመላው ፖላንድ የተውጣጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሰባሰቡ ሲሆን፥ በዚህ ክርስቲያናዊ የዝማሬ ዝግጅት ላይ ከ25,000 በላይ የሚሆኑ ምእመናን እንደተሳተፉ እና ዝግጅቱም በተለያዩ ሚዲያዎች ለመላው ዓለም እንደተላለፈ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“አንድ ልብ አንድ መንፈስ” በሚል መሪ ቃል በፖላንድ ደቡባዊ ምስራቅ በምትገኘው የሪዜዞው ከተማ የተካሄደው የዘንድሮ የክርስቶስ ክቡር ሥጋ እና ክቡር ደም የሚከበርበት ክብረ በዓል ከ25,000 የሚበልጡ ከፖላንድ እና ከሌሎች የአውሮፓ ሀገራት የተውጣጡ ሰዎችን በጋራ አሰባስቧል።

በላቲን ቋንቋ ኮርፐስ ክሪስቲ ማለት “የክርስቶስ ክቡር ሥጋው ክቡር ደሙ” ማለት ሲሆን፥ ክብረ በዓሉም መከበር የጀመረው እ.አ.አ. በ 1246 ዓ.ም እንደሆነ እና ይህ በበርካታ የሮማ ካቶሊኮች የሚከበረው ክብረ በዓል ከሥላሴ እሑድ በኋላ ባለው የመጀመሪያው ሐሙስ ሲሆን፥ ይህም ከበዓለ ሃምሳ ወይም ከጴንጤቆስጤ በኋላ ባለው የመጀመሪያው እሑድ ነው።

በዚህም በዓል ካቶሊኮች በዓለም ሁሉ ፊት የእምነታቸውን ሥርዓተ አምልኮ የሚያከብሩበት ክብረ በዓል እንደሆነም ይታወቃል።

የዚህ ክብረ በዓል አዘጋጆች እንዳሳወቁት “ኮንሰርቱ ጸሎታዊ ይዘት ያለው እንደሆነ እና ከሁሉም በላይ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚከበርበት ብሎም መርሃ ግብሩ በርካታ ሰዎችን በአውታረ መረብ እና በቴሌቪዥን እንዲሁም በራዲዮ እና በኢንተርኔት ስርጭቶች በአንድነት እንዲያመልኩ እንደሚያመቻች” ገልጸዋል።

ዝግጅቱ በተለያዩ ስርጭቶች እና የሚዲያ ተቋማት በፖላንድ እና በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች እንደተዳረሰም ተዘግቧል።

የዚህ “አንድ ልብ ፡ አንድ መንፈስ” በሚል መሪ ቃል የተከበረው የመዝሙር ዝግጅት ላይ የተገኙት የሙዚቃ ቡድን ኦኬስትራ እና መዘምራን የዝማሬ አቅራቢዎችን ያጀቡ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ወደ 200 የሚጠጉ ዘማሪዎች እንዲሁም የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች እና በጎ ፈቃደኞች በዓሉን አድምቀውታል።

የመንፋሳዊ ሙዚቃ ዝግጅቱ ተሳታፊዎች በዚህ ለሶስት ሰዓታት በቆየው ክብረ በዓል 26 በሚሆኑ ዝማሬዎች እና ሃይማኖታዊ ዝግጅቶች መንፈሶቻቸውን አድሰውበታል ተብሏል።

ከኮንሰርቱ አዘጋጆች አንዱ የሆኑት አባ አንድርዜይ ካፕሪስ፣ የሙዚቃ ዳይሬክተር የሆኑት ማርሲን ፖስፒዝልስኪ እና ጃን ቡዲዚያስክ በጋራ በመሆን “አንድ ልብ፣ አንድ መንፈስ” ተብሎ ለ22ኛ ጊዜ በተከበረው ክብረ በዓል ላይ የተሰበሰቡትን ሁሉ በደስታ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በመጨረሻም የሪዜዞው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ጃን ዋትሮባ በዓሉን በቡራኬ ዘግተዋል።

የኮርፐስ ክሪስቲ ቀን ላይ የሚደረጉ የአምልኮ ኮንሰርቶች አሁን ላይ በፖላንድ በሚገኙ ትላልቅ ከተሞች እንዲሁም በትናንሽ ከተሞች ውስጥ በጣም ተወዳጅ እየሆኑ መጥተዋል።

በርካታ ሰዎች የመንፈሳዊ ሙዚቃ ዝግጅቱን ይዘት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በመለጠፍ በመገናኛ ብዙሃን ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ ያሳረፉ ሲሆን፥ አብዛኛው የክብረ በዓሉ ተሳታፊዎችም ወጣቶች እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል።
 

03 June 2024, 13:15