ሊቀ ጳጳስ ጁንግ ሱን-ታክ ኮሪያውያ ጥላቻን ከመካከላቸው እንዲያስወግዱ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የሴኡል ከተማ ሊቀ ጳጳስ ጁንግ ሶን-ታክ በሰሜን እና በደቡብ ኮሪያ መካከል ያለውን የሻከረ ግንኙነት በመጥቀስ ባሰሙት ንግግር፥ “የምንገኝበት ወቅት ጨለማ የነገሠበት ቢመስልም አዳዲስ ግንኙነቶችን ለመገንባት ቁርጠኞች መሆን እንፈልጋለን” ብለዋል።
ሊቀ ጳጳስ ጁንግ ሶን-ታክ ይህንን የተናገሩት የኮሪያ ጦርነት መታሰቢያ ቀንን ምክንያት በማድረግ ሰኔ 18/2016 ዓ. ም. ለብሔራዊ እርቅ እና አንድነት ብለው በማዮንግዶንግ ካቴድራል ውስጥ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ነው።
ሊቀ ጳጳስ ጁንግ በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ ባለፉት ፈተናዎች እና በአሁን ጊዜ መካከል ያለውን ተመሳሳይነት ገልጸው፥ “ድህነትን እና አምባገነንነትን በተስፋ እንዳሸነፍን ሁሉ፣ መከፋፈልን ማሸነፍ እንችላለን የሚለውን ተስፋ መቀበል አለብን” ካሉ በኋላ፥ “ይህ ተስፋ በኮሪያ ምድር እውነተኛ ሰላምን ያመጣል” ብለዋል።
በማቴ. 5፤38 ላይ እንደተጠቀሰው ‘ዓይን ስለ ዓይን ጥርስ ስለ ጥርስ’ የሚለውን የአጸፋ ተግባር አስተሳሰብ በመንቀፍ፥ ሰላም የሚረጋገጠው በውይይት እንጂ በጥላቻ እንዳልሆነ አስገንዝበዋል።
ምእመናን በሌሎች ላይ ለውጥ እንዲመጣ ከመጸለይ ይልቅ ሰላምና ይቅርታን በራሳቸው ተግባር እንዲያሳዩ ሊቀ ጳጳስ ጁንግ አሳስበዋል። ሊቀ ጳጳሱ ዕለቱ ሁሉም የባሕረ ሰላጤው ነዋሪዎች ከግጭት ይልቅ የእርቅን መንገድ የሚመርጡበት የጸሎት ቀን እንደሆነም አስረድተዋል።
“በኮሪያ ባሕረ ሰላጤ የሚኖር ማንኛውም ሰው በኅብረት በመጸለይ ከአመጽ መንገድ ይልቅ ሁላችንም የይቅርታ እና የእርቅ መንገድን መምረጥ ይገባል ብለዋል።
በደቡብ ኮሪያ ውስጥ‘የብሔራዊ ዕርቅና አንድነት የጸሎት ቀን በአገሪቱ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ተነሳሽነት
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1965 ዓ. ም. የተጀመረ ሲሆን በ1992 ዓ. ም. እንደገና መሰየሙ ይታወሳል።
የሴኡል ሀገረ ስብከት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1995 ዓ. ም. የተከበረውን 50ኛ የነጻነት ቀንን በማስመልከት
ብሔራዊ የዕርቅ ኮሚቴን በማቋቋም መደበኛ የመስዋዕተ ቅዳሴና መንፈሳዊ ስብሰባዎችን በመጥራት በአገሪቱ ውስጥ የሚኖሩ የሰሜን ኮሪያ ከዳተኞች በማሰባሰብ ያበረታታቸዋል።