ወንድም ጃክ ኩራን በቫቲካን ውስጥ  ወንድም ጃክ ኩራን በቫቲካን ውስጥ  

በቤተልሔም ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ ተማሪዎች “አስከፊ” ችግሮች እያጋጠሟቸው ነው ተባለ

የቤተልሔም ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ብሩክ ጃክ ኩራን ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ጸሎት እና ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጥሪ አቅርበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እ.አ.አ. በ 1964 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ደረጃ የተደረገ የመጀመሪያ ታሪካዊ መንፈሳዊ ጉዞዋቸውን ወደ ቅድስት ሀገር ባደረጉበት ጊዜ የፍልስጤምን ህዝብ ለመርዳት አንድ ነገር ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው ነበር።

ብጹእነታቸው ያሰቡት ይህ ፕሮጀክት እውን ሆኖ ተግባራዊ እስከሚሆን ድረስ አሥር ዓመት ገደማ ፈጅቷል። ከዚህ ሁሉ ዓመታት ውጣ ውረድ በኋላ እ.አ.አ. በ1973 በቅድስት ሀገር የመጀመሪያው የሆነውን የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ በቤተልሔም ተከፈተ።

ዛሬ በቤተልሔም የሚገኘው ይህ ዩኒቨርሲቲ “ነጻ፣ ሰላማዊ እና ንቁ ፍልስጤምን ለመገንባት” በሚል መርህ ወደ 3,000 የሚጠጉ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያሰለጠነ ይገኛል።

የምስራቃዊ ካቶሊኮች አብያተ ክርስቲያናትን ለሚያገለግሉ የረድኤት ኤጀንሲዎች ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ የዩንቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ወንድም ጃክ ኩራን በአሁኑ ጊዜ ሮም ይገኛሉ።

የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ላይ እያደረሰ ስላለው ጉዳት እና ሰራተኞቹ ይህን ችግር ለመቅረፍ ስለሚጥሩባቸው መንገዶች ወንድም ጃክ የቫቲካን ዜና ባልደረባ ከሆኑት አባ አድሪያን ዳንካ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

“ያልተለመዱ” ችግሮች

ወንድም ጃክ ኩራን በቃለ ምልልሱ ወቅት እንዳሉት በቤተልሄም ዩንቨርሲቲ የተማሪዎች ሁኔታ “ለበርካታ ዓመታት በጣም አስቸጋሪ” እንደ ነበር ገልጸው፥ ነገር ግን ባለፈው ዓመት በጥቅምት ወር ላይ የእስራኤል-ሃማስ ጦርነት ከተነሳ ጀምሮ ችግሮቹ “ከበፊቱ በተለየ ሁኔታ በእጅጉ ተባብሰዋል” ብለዋል።

በተለይም ወደ ዌስት ባንክ ለመግባት እና ለመውጣት ወይም ከከተማ ወደ ከተማ ለመዘዋወር እጅግ አዳጋች መሆኑንም ጭምር አፅንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።

ወንድም ጃክ እንደተናገሩት አርባ በመቶው የቤተልሄም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከሚኖሩባት እየሩሳሌም ወደ ቤተልሔም ለመድረስ ርቀቱ ስምንት ኪሎ ሜትር ብቻ ያለው ቢሆንም፥ ይህን ማድረግ “ለአምስት ወራት የማይቻል” ነበር ብለዋል።

አዳዲስ ዘዴዎች

ይህ ሁኔታ በቤተልሔም ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ መምህራንን እና ሰራተኞችን “ተማሪዎቹ የሚያሳትፉበት አዳዲስ መንገዶችን እንዲፈልጉ” እንዳስገደዳቸው ወንድም ኩራን ተናግረዋል።

ይህ ማለት በተልዕኳቸው ወቅት አስፈላጊ ነገሮች ላይ ብቻ በማተኮር “ለተማሪዎቹ የሰው እና ክርስቲያናዊ ትምህርት ለመስጠት” ባህሪያቸውን በማጎልበት እና የተሻሉ ዜጎች እንዲሆኑ መርዳት ነው ብለዋል።

ዓላማቸውም በተማሪዎቻቸው ውስጥ “መጪው ጊዜ ተስፋ የሚደረግበት ጊዜ ነው” የሚለውን አስተሳሰብ ማዳበር እንደሆነ ተናግረዋል።

አንዳንድ ጊዜ ይህን ማድረግ በጣም ከባድ እንደሆነ በመግለጽ “በተማሪዎቻችን እና በመምህራን ላይ የሚደርሰው የስነ ልቦና ጫና በጣም አሳሳቢ ነው” ብለዋል።

በዚህ ምክንያት፣ “በተቻለ መጠን መደበኛ ኑሮን ለማስቀጠል እና የተማሪዎቻችንን ስነ ልቦናዊ እና አካዳሚያዊ ጉዳዮችን ለመከታተል የምንችለውን ለማድረግ እየሞከርን ነው” በማለት ገልጸዋል።

ጸሎት እና ህብረት

የቤተልሔም ዩኒቨርሲቲን ሥራ ግለሰቦች እንዴት መደገፍ እንደሚችሉ የተጠየቁት ወንድም ኩራን፥ ጸሎት እና ተጨባጭ ህብረት ማሳየት በእጅጉ የሚያስፈልግበት ወቅት ነው ብለዋል።

የሚደረጉት የገንዘብ ስጦታዎች ለተማሪዎቻችን የምንሰጠውን “የምክር እና የስነ-ልቦና እንክብካቤን ለማሻሻል” እንዲሁም የአካዳሚክ ድጋፍን ለመጨመር ስለሚረዱ ለዚህም ድጋፍ በጣም አድናቆት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ወንድም ኩራን በመጨረሻም “ይህ በቅድስት ምድር ብቸኛ በሆነው የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የምንተገብረው መንፈሳዊ ተልእኮ በሚገርም ሁኔታ አስፈላጊ ነው፥ ቤተክርስቲያናችንም ሥራዋን የምታከናውንበት ምቹ ቦታ ነው” ብለዋል።
 

26 June 2024, 21:59