መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያቱ ላይ ወረደ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያቱ ላይ ወረደ 

የሰኔ 16/2016 ዓ.ም ሰንበት ዘጴራቅሊጦስ ቃለ እግዚአብሔር አስተንትኖ

መንፈስ ቅዱስ ሆይ ና! የክርስቲያኖችን ልብ ሙላ፥ የፍቅር እሳት በውስጣቸው አንድድ ፤ እውነተኛ ምንጭ የሆንከው መንፈስ ቅዱስ ሆይ! ሕዝቦች ሁሉ ትሕትና በተሞላበት እምነት ደስ እንዲያሰኙህ ብርሃንህን ስጣቸው ፡፡

 የእለቱ ምንባባት

1.    የሐዋርያት ሥር 2፡1-11

2.    መዝሙር 103

3.    ገላቲያ 5፡16-25

4.    ዩሐንስ 15፡26-26፣ 16፡12-15

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

“እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ፣ ከአብ የሚወጣው አጽናኙ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፣ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል። እናንተም ደግሞ፣ ከመጀመሪያው ከእኔ ጋር ስለ ነበራችሁ፣ ትመሰክራላችሁ።  “ብዙ የምነግራችሁ ነበረኝ፤ አሁን ግን ልትሸከሙት አትችሉም። የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል። እርሱ ከራሱ አይናገርም፤ የሚሰማውን ብቻ ይናገራል፤ እንዲሁም ወደ ፊት ስለሚሆነው ይነግራችኋል፤ የእኔ ከሆነው ወስዶ እንድታውቁ በማድረግ ያከብረኛል። የአብ የሆነው ሁሉ የእኔ ነው፤ እንግዲህ፣ ‘የእኔ ከሆነው ወስዶ እንድታውቁ ያደርጋል’ ያልኋችሁ ለዚሁ ነው።

 

የዕለቱ አስተንትኖ

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እና እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

እነሆ የእውነትና የፍህት መንፈስ ፥ እነሆ የሰላምና የደስታ መንፈስ ፥  እነሆ የአንድነትና የፍቅር መንፈስ ፥ እነሆ የምሕረትና የይቅርታ መንፈስ ፥ እነሆ ያሸናፊነትና የተስፋ መንፈስ ፥ እነሆ የትሕትናና ያገልጋይነት መንፍስ ፥ እነሆ የልጅነትና የውንድማማችነት መንፈስ !

ይህንን ዝግጅት በድምጽ ለማዳመጥ ተጫወት የሚለውን ምልክት ይጫኑ

ለሃምሳ ቀናት የክርስቶስን ትንሳኤ ፥ የክርስቶስን አሸናፊነት ፥ የክርስቶስን ድል ፥ የክርስቶስን ክብር እና ኃይል ስናከብርና ስናስተነትን ቆይተናል ፡፡ እነሆ ዛሬ ደግሞ የቅድስት ሥላሴ ሶስተኛ አካል፥ የክርስቲያኖች ኃይል የሆነው ፥ የክርስቲያኖች ጥበብ የሆነው ፥ የክርስቲያኖች  አጽናኝ የሆነው ፤ መንፈስ ቅዱስን እንድናከብር ፥ እንድንወድስ ፥ እንድንጸልይ እንጋበዛለን።  

ውድ የእግዚኣብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ! በዚህ ሰንበት ይህንን ቅዱስ መንፍስ እንድትላበሱ ተጋብዛችኃዋል።

ይህ ቅዱስ መንፈስ የክርስቲያኖች ሁሉ ሕይወት ነው ፤ ይህ ቅዱስ መንፈስ ዛሬም ለእያንዳንዳችን በእሳት አምሳል  ይታደለናል ፥ ይህ ቅዱስ መንፈስ ዛሬም ቤተ ክርስቲያንን ይመራል፥  በዛሬ ቀን በሐዋርያት ሥራ እንደ ምናነበው ፤ መንፈስ ቅዱስ ከእግዚእብሔር ተልዕኮ ፤ በእመቤታችንና በሐዋርያት ላያ እንዴት እንደ ወረደና የዚህ ቅዱስ መንፈስ ኃይል እንዴት የብርታት መንፈስ እንደሆነ ቅዱስ ሉቃስ የሐዋርያት ሥራ ጸሐፊ ይተርክልናል።

በቅዱስ ወንጌል እንደ ምናነበው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት፤ ፈሪዎች፥ ድንጉጦች፥ ተጠራጣሪዎች፥ ብዙም ጥበብ የሌላቸው፥ ተራ የቀን ሠራተኞች፥ ሙሉ ሕይወታቸውን ሁሉ በባሕር ላይ ዓሳ በማጥመድ ያሳለፉ፥ በዚህ ዓለም እዚህ ግባ የሚባል ታሪክ የሌላቸው ሰዎች ነበሩ። ስለዚህ ሞትን ፈርተው ኢየሱስን አስተማሪያቸውን ቢከዱ ወይንም ቢፈሩ  ብዙም አይደንቅም።

ስለዚህ እነዚህ ምስኪንና ደካማ የገሊላ ተራ ሰዎች ፤ ከፍርሃት የተነሳ ቤታቸው ዘግተው ይኖሩ ነበር ፤ ከፍርሃት የተነሳ ልባቸው ተዘግቶ ነበር ። የሚፈራ ሰው ቤቱ ዘግቶ ይኖራል ። የሚፈራ ሰው ወኔ አይኖረውም ፥ የሚፈራ ሰው ብርሃን ይፈራል ፤ የሚፈራ ሰው ለሌሎች ቦታ የለውም ፤ ምክንያቱም ልቡ የተዘጋ ስለሆነ ፤ የሚፈራ ሰው እግዚአብሔርን ይሁን ሰውን አያምንም ፤ የማያምን ሰው ማፍቀር አይችልም ፤ የማያፈቅር ሰው መማር ወይም ይቅር ማለት አይችልም ፤ የማያምን ሰው ተስፋ አይኖረውም ፤ ነገ መልካም ይሆን ይሆናል ብሎ ማሰብ ይከብደዋል ፤ የሚፈራ ሰው የሚያወራው መልካም ዜና የለውም ፤ ለሚፈራ ሰው ሁሉም ነገር ከንቱ ነው ፤ ለማያምን ሰው ምንም ነገር መልካም የለም ፤ ለማያምን ሰው ሁሉ ነገር ክፉ ነው ። ስለዚህ ቤቱን ዘግቶ ቢኖር ምን ይደንቃል? እግዚአብሔር ግን መልካም ነው። መንፈሱን ይልካል ፤ በፍርሃትና በጥርጣሪ የተዘጋውን በር ይከፍታል፤ ባለ ማመን የተዘጋውን ልብ ያንኳኳል፤ እነዚህ ድንጉጥ ፥ ፈሪና ተጠራጣሪዎች ያን ቅዱሱ የእግዚአብሔር መንፈስ ሲቀበሉ ታሪካቸው ይቀየራል ። ታሪክ የሌላችው ተራ የገሊላ ዓሳ አጥማጆች የዓለም ብርሃን አብሳሪች ሆነው ተገኙ ፤ እነዛ የገሊላ ፈሪዎች ሞትን በሞት የሚያሸንፉ ጀግኖች ሆነው ተገኙ ፤ እነዛ የገሊላ ተጠራጣሪዎች የመምህራቸውን ታሪክ ለመድገም አሻፈረኝ አሉ ፤ ሕይወታቸውን ለመስቀልና ለስይፍ አሳልፈው ሰጡ ፤ እውነትም ከተራ ዓሳ አጥማጅነት ወደ ሰው አጥማጅነት መንፈስ ቅዱስ ለወጣቸው ።

ከእንግዲህ ለገሊላ ዓሳ አጥማጆች ፍርሃት ትርጉም የለውም ፥ ጥርጣሬ ዋጋ የለውም ። ከእንግዲህ ለእነርሱ መኖር ማለት ለመምህራችው መሞት ፥ ከእንግዲህ ለእነርሱ ሕይወት ማለት እውነትን መመስከር ፤ ለእነርሱ መኖር ማለት ዓለምን ለማዳን ሕይወትን መሰዋት ማለት ነው ፤ ስለዚህ ለእነርሱ ሕይወት ማለት የመምሕራቸውን ታሪክ መድገም ፥ ስለ ሌሎች መሞት ማለት ነው ።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

ይህንን ታሪክ የሚቀየረው መንፈስ ቅዱስ ፤ ዛሬም አዲስና ሕያው ነው ። ዛሬም የእያንዳንዳችንን ታሪክ ለመቀርየር ዝግጁ ነው ። ዛሬም ልክ እንደ ሐዋርያቶች እጅግ ብዙ ሰዎች ፤ በፍርሃትና በጥርጣሬ ተይዘው ልባቸውንና ቤታችቸውንም ዘግተው ይኖራሉ ። ዛሬም እጅግ ብዙ ክርስቲያኖች ተስፋ ቆርጠው ፥ ማመን ተስኖአቸው ፥ ማፍቀር አቅቶአቸው በጨለማ ይኖራሉ ። ነገ መልካም ይሆናል የሚለው ተስፋ ተረትና ቀልድ ሆኖ ይታያቸዋል ። ማፍቀር የሚለው ቃል እውነት ሆኖ አይታያቸውም ። እግዚአብሔርም ይሁን ባልንጀራን መውደደ ሊሆን የማይችል እውነታ ነው ብለው ያስባሉ ።

ዛሬም ብዙ ክርስቲያኖች ህብረትና አንድነት በዚህ ዘመን ሊኖር የማይችል እውነታ አድርገው ያምናሉ ። በአንድ በኩል እነዚህ ሰዎች ትክክል ናቸው ፤ ምክንያቱም በዓለማችን ያለው ሁኔታ እጅግ ግራ የሚያጋባ ነው ፤ እጅግ የተዘበራረቀ ነው ፤ እጅግ የተወሳሰበ ነው። የዓለም ሰዎች ክፋት ቢበዛ ብዙም አይገርምም። የክርስቲያኖች ክፋት ሲበዛ ግን እጅግ ያስደንቃል ።  ለዓለም ብርሃንና ጨው  እንዲሆኑ የተላኩ ክርስቲያኖች ፤  እንኳዋን ለዓለም ሊያበሩ ይቅርና ራሳችው በጨለማ ይኖራሉ ፤ እንኳዋን ዓለምን ሊያጣፍጡ ይቅርና ራሳቸው ጣዕም ያጣ  አልጫዎች ሆነዋል ።   የፍቅር ሳይሆን የጥላች ሰባኪዎች ሆነዋል ፥ የምሕረት ሳይሆን የበቀል ሰባኪዎች ሆነዋል ፥ ሰላምና አንድነትን ሳይሆን መለያየትና ጥልን ይሰብካሉ። ክርስቲያኖች በዓለም ላይ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ መሥራት ሲገባቸው ራሳችው የጦርነት መንስሄ ይሆናሉ ፥ ዓለምን እንዲያድኑ የተላኩ ክርስቲያኖች ፤ ለዓለም መጥፋት መንገድ ይሆናሉ ።

ስለ ሰላም ይሰብካሉ ግን ራሳቸው በሰላም መኖር አይችሉም ፥ ስለ ምሕረትና ይቅርታ ያውጃሉ ግን ራሳቸው ለምሕረትና ይቅርታ ዝግጁዎች አይደሉም ፥ ስለ ፍቅር ጥልቅ የሆነ ትምሕርት ይሰጣሉ፣ ነገር ግን ፍቅርን መኖር ይቸገራሉ ፥ ምሕረትና ፍቅር ለእነርሱ የሚያወሩት እንጂ የሚኖሩ አይመስላቸውም። የክርስቶስ ወንጌል ለራሳቸው ዓላማ  በሚመቻቸው መንገድ ይተረጉማሉ።  በዓለም በብዙህ ሺህ የሚቆጠሩ የተለያዩ የክርስትና እምነት እንዳለ ያስባል ፤ ክርስቲያኖችም ራሳቸው የተለያዩ  ክርስቶስና የክርስትና እምነቶች እንዳለ እናምናለን እናስተምራለን ፤ በዶክትሪን ወይንም በእምነት ሕግጋት  ሰበብ ፥ በስልጣን ሰበብ ፥ በፖለቲካ ሰበብ ፥ በዘርና በቀለም ሰበብ ፥  በገንዘብ ፍቅር ሰበብ ፤ ስንት የክርስትና ዓይነቶች ዛሬ በዓለማችን ተፈጥረዋል? ስንት ቤተ ክርስትያኖች ተመስርተዋል? የሚገርመዉ ግን አንዳቸው የአንዳቸው ጠላቶች መሆናቸው ፥ አንደኛው አንደኛውን ለማፍቀር አለመቻላቸው ነው። የዛሬ ክርስቲያኖች በጥንት ዘመን በእግዚአብሄር ላይ ያመጹ ባቢሎናውያን ሆነው ይታያሉ። የአንድ አገር ሕዝቦች ፥ የአንድ ባሕል ሰዎች ፥ አንድ ዓይነት  ቋንቋዋ የሚያወሩ  ፤ ነገር ግን  መግባባት የማይችሉ ።

ምክንያቱም ልባቸው በትዕቢትና በክፋት የተሞላ ስለሆን ። ልክ ዛሬም እኛም ፤ አንድ ዓይነት ቋንቋ እናወራለን  አንድ ዓይነት ክርስቶስ እንሰብካለን ፥ አንድ ዓይነት ጥምቀት እንጠመቃለን ፥ አንድ ዓይነት መጽሐፍ ቅዱስ እናነባለን ፥ አንድ ዓይነት ቅዳሴ እንቀድስለን ፤  ግን ደግሞ ልክ እንደ ባቢሎን ሰዎች አንግባባም ። የአንዳችን ቋንቋዋ ለአንዳችን አይገባም ። አንዳችን ለአንዳችን መናፍቃን እየሆንን እንገኛለን። አንዳችን ለአንዳችን ወንድም ሳንሆን ከሃዲዎች እየሆን እንገኛለን። አንዳችን ለአንዳችን የተወገዘና የተረገመ ነን ። ያ የሰው ሁሉ ወንድምና አዳኝ የሆነው ክርስቶስ ፤ የእኛ ቡድን ብቻ ወንድምና አዳኝ  እንደሆነ እናምናለን ፥ የሁሉ ወንድምና አዳኝ  የመሆን ክብሩን አሳጥተን ፤ የጥቂቶች ብቻ እንደሆነ አምነን ክብሩን ዝቅ ለማድረግ እንሞክራለን ። ስለ ክርስቶስ እያወራን ክርስቶስን እናሳድዳለን ።

በጣም የሚገርመው የጥንት ክርስቲያኖች መንግሥታትና የዓለም ሰዎች ሲጣሉ የማስታረቅና ሰላም የማውረድ የእነርሱ ግዴታ እንደ ሆነው አምነው የተቻላቸውን ሁሉ ያረጉ ነበር ፤ የዛሬዎቹ ክርስቲያኖች ግን እርስ በርሳቸው ይጣሉና የዓለም ነገሥታትና መንግሥታት ለማስታረቅ ሰላም ለማውረድ ይጥራሉ ፤ የዓለም ሰዎች ክርስቲያኖች ያምኑ ዘንድ  ለክርስቲያኖች ስለ ምሕረትና ፍቅር እየሰበኩ ይገኛሉ።

በተቃራኒው እነዚህ ፈሪና ተጠራጣሪ የገሊላ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ሲሞሉ፤ ከጥንት ባቢሎናውያን ተቃራኒዎች ሆነው ተገኙ።  የተለያዩ ቋንቋዋች ያወሩ ነበር፣ ነገር ግን ይግባባሉ ፤ ወይም ደግሞ አንድ ቋንቋዋ ያወራሉ፣ ለዓለም ሁሉ ይሰማል ፥ ቃላቸው ለዓለም ሁሉ ይገባል ፥ ከአፋቸው የሚወጣው ቃል ለዓለም ሁሉ ሕዝብ ይገባል ፥ ለዓለም ሁሉ ሕዝብ ይጥማል ፥ ለዓለም ሁሉ ሕዝብ ልብ ዕረፍትን ይሰጣል ። በእየሩሳሌም የተሰበሰቡ ከዓለም ዳርቻ ሁሉ የመጡ ሰዎች “እነዚህ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን?” (ሐዋ 2፡7) ብለው የናቁዋቸውን ሰዎች ቋንቋዋ ይሰማሉ ። ትሑትና በፍቅር የተሞላ  ልብ ነበራቸውና ፥ የሚያወሩት አንድ ቋንቋዋ ነበር፤ ይኸውም ፍቅርና ምሕረት ።  ፍቅርና ምሕረት ሁሉ ሰው ይገባዋል ፤ ፍቅርና ምሕረት የሁሉም ሀገር ቋንቋዋ ነው፤ ፍቅርና ምሕረት በሁሉም ሀገር ይፈለጋሉ፥ ሁሉም ሰው ይገባዋል ፥ ፍቅርና ምሕረት ለሁሉም እረፍትና ሰላም ይሰጣል።

የመንፈስ ቅዱስ የመጀመሪያ ስጦታው ፍቅርና ምሕረት ነው፥ የሚያወሩት ፍቅርና ምሕረት ስለሆነው ክርስቶስን ብቻ ነበር የሚሰብኩት ፤ ስለዚህ በእየሩሳሌም የተሰበሰቡ ሕዝቦች ይህን ቋንቋዋ ለመስማትና ለመገንዘብ ብዙ አልተቸገሩም ። ክርስቶስ በፍቅርና በምሕረት ሁሉን አሸነፈ ፤ በፍቅርና በምሕረት ብቻ ነው ክፋትንና ዓለምን ማሸነፍ የሚቻለው። የሚያፈቅር ሰው ብቻ ነው መማር የሚችለው፣ እንዲሁም መማር የሚችል ሰው ብቻ ነው ማፍቀር የሚችለው። እግዚእብሔር ማፍቀር አይሰለችውም ።

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች!

የትንሣኤ በዓል ወይንም የጴራቅሊጦስ በዓል ፤ ቀናትን ወይንም ወራትን ወይንም ደግሞ ዓመታትን ቆጥረን የምናከብራቸው እና የምናስታውሳችው በዓላት ሳይሆኑ፤ በየእለቱ በምናደርገው የሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ፤ በየእለቱ በምናድርገው የመኖር ትግል ውስጥ የምንኖረው ነው ፡፡ የእያንዳንዱ የሰው ልጅ ሕይወት ትርጉምና ዋጋ የሚያገኘው፤ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ እና በእግዚአብሔር ቅዱስ መንፍስ ስለሆነ ነው። የሰው ልጅ ሕይወትና እስትንፋስ የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ ነው። ለዚህ ነው የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ የሰው ልጅ እንዴት በእግዚአብሔር መልክና አምሳያ እንደ ተፈጠረ የሚነግረን በዚሁ ምክንያት ነው። ስለዚህ ክርስቶስ ወንድማችንና አዳኛችን በኃጥያታችን ምክንያት ያጣነውን ክብር በሞትና ትንሣኤው ዳግመኛ ይሰጠናል። መንፈስ ቅዱስን በመላክ ክርስቶስ ወንድማችን የሰጠን ክብር ጠብቀን እንድንኖር ያበረታናል፥ ያጽናናናል በተስፋ ይሞላናል ።

ስለዚህ ትንሣኤና መንፈስ ቅዱስ በየ ዕለቱ የምንኖረው ነው።  በዕለት ተዕለት በምናደርገው የሕይወት ውጣ ውረድና ትግል ውስጥ እያንዳንዱ መልካም እንቅስቃሴያችን ፥ እያንዳንዱ መልካም ሥራችን ፥ እያንዳንዱ መልካም ሐሳባችን ሁሉ በውስጣችን ያለው የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው። እያንዳንዱ ጸሎት ፥ በእያንዳዳችን ውስጥ ያለ እግዚአብሔርን የመፈለግና የማወቅ ፍላጎትና ጉጉት ፤ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን እንደ ሚሰራ የምናረጋግጥበት መንገድ ነው፥ በእያንዳዳችን ውስጥ ያለው ሰውንና እግዚአብሔርን ለመውደድና ለማፍቀር ያለንን ፍላጎት ፥ በእያንዳንዳችን ውስጥ እውነትን የመውደድና የመፈለግ ጥማት  ሁሉ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በውስጣችን ያሳደረው ጸጋ ነው ። ለዚህ ነው የመፈስ ቅዱስ በዓል ጊዜያትን ጠብቀን የምናከብረው ሳይሆን፤ በእየእለቱ ሕይወታችን ትግል እንድንኖርውና እንድናዳምጠው የምንጋብዘው በዚሁ ምክንያት ነው። በተለይም ደግሞ ለእኛ ለክርስቲያኖች በሚታይና በሚጨበጥ በሚዳስስ መልኩ በቅዱሳት ምስጢራት ይህን ቅዱሱ የእግዚአብሔር መንፍስ ይታደለናል። እያንዳንዱ ምስጢራት የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው ። በጥምቀት አማካይነት የእግዚአብሄር መንፈስ በውስጣችን ከእናት ከአባታችን የወርስነውን ማነንት አጥፍቶ ሌላ ማነንት የሚሰጠን ፥ የሰው ልጆች ብቻ መሆናችን ቀርቶ የእግዚእብሔር መለኮታዊ ማንነት የሚያላብሰን ።

ስለዚህ ትልቁ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ የሰው ልጆችን ወደ የእግዚአብሄር ልጅነት መቀየር ነው። ለሰው ልጆች የአምላክን ባሕሪ ማላበስ ነው። በጥምቀት የምናገኘው ጸጋ ሁል ጊዜ ከማንነት ጋር የተያያዘ ነው ። ከደምና ከሥጋ የተዋኸደ ነው ። ዳግም የተወለደ ነው ፥ ለዚህ ነው የጥምቀት ጸጋ የማይሻር ነው የምንለው ። የተጠመቀ ሰው ዝርያው ጎሳው እና ባህሉ የእግዚአብሔር ነው ። ለዚህ ነው “ቤተክርስቲያን” የሚለው የግዕዝ ቃል የሚያመለክተው “የክርስቲያን ዘር የክርስቲያን ጎሳ ወይም የክርስቲያን ብሔር ወይም የክርስቲያን ግንድ ነው” የሚለው።

ክርስቲያን ሆይ ! አንተ የእግዚእበሄር ዘር ነህ! አንተ የእግዚአብሄር ጎሳ ነህ! ክርስቲያን ሆይ ! የእግዚአብሄር ብሔር ነህ ። ማንነትህ ከእግዚእብሄር ጋር የተዋኸደ ነው፥ ዘርህ ፥ ደምህ ፥ ሥጋህ ከክርስቶስ ዘርና ደም ጋር የተዋኸደ ነው ። ታዲያ ለምን እራስህን ትክዳለህ? ዘርህና ጎሳህን ለምን ትክዳለህ ? ክርስቲያን መሆን የክርስቶስ ዘር መሆን ነው ፥ ክርስቲያን መሆን የክርስቶ ጎሳ መሆን ነው ።

ስለዚህ ክርስቲያን ሆይ! የተጠመቀ ሁሉ ያንተ ጎሳና ብሔር ነው። የተጠመቀ ሁሉ ያንተ ወንድም ነው ፤ ዛሬ የእግዚእብሔር ቅዱስ መንፈስ ይህን ወንድምህን እንድትወደው እንድታፈቅረው ይቅር እንድትለው ይጋብዝሃል ፤ አንዲሁም ክርስቶስ ወንድማችን የሰዎች ሁሉ ወንድም ነው ፤ የሰው ሁሉ አዳኝ ነው፣ ያንተ ቡድን ወይም ያንተ ማኅበር ብቻ አይደለም ።  ሰው ሆኖ በተፈጠረው ሁሉ ላይ  የክርስቶስ መንፈስ አለ ።

ክርስቲያን ከሆንክ ! በሁሉም ሰው ላይ ፤ በክፉና በደጉ ፥ በሚያምን ሆነ በማያምን ላይ ወንድምህን ፥ አዳኝህን እና አፍቃሪህን የሆነውን ክርስቶስ ተመልከት ። የተጠራኸውም ለዚህ አንድነት ነው ። የአንድነትና የፍቅር ሰባኪ እንድትሆን ነው ። አንተም እንደ ጴጥሮስ  ምሕረት ፍቅር  እድታውጅ ነው የተጠራኸው። እንድትፈርድ እና እንድትለያያ አይደለም። አንተም እንደ መቅደላዊት ማርያም ‘ክርስቶስ ሞትን አሸነፉዋል’ ብለህ ድልን እንድታውጅ ነው ፤ አንተም እንደ ቅድስት ድንግል ማርያም ያዘነውን እና የደከመውን በተስፋ እንድታበረታና ለመንፈስ ቅዱስ መውረድ እንድታዘጋጅ ነው ።  ስለዚህ ሁል ጊዜ በልብህ ፥ መንፈስ ቅዱስ ሆይ ና! የፍቅር እሳት በውስጤ አንድድ ብለህ ጸልይ ፤ በሁሉም ሰው ውስጥ ክርስቶስን ማየት እችል ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ሆይ እርዳኝ ብለን እንጠይቀው። አሜን!   

ምንጭ፡ ሬዲዮ ቫቲካን

አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ

22 June 2024, 08:07