TOPSHOT-PORTUGAL-RELIGION-FATIMA TOPSHOT-PORTUGAL-RELIGION-FATIMA  (AFP or licensors)

የእመቤታችን ድንግል ማርያም ካቶሊካዊ ዶግማዎች

ለፕሮቴስታንት ክርስቲያኖች በካቶሊካዊያን ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያላት ቦታ እና ክብር ከልክ ያለፈ ሆኖ ይታያቸዋል። በመሆኑም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ስለ እመቤታችን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም የደነገገቻቸውን አራቱን የአንቀጸ ሃይማኖት ድንጋጌዎች አይቀበሉም።

እነዚህን አራቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አንቀጸ ሃይማኖት ድንጋጌዎች የሚከተሉት ናቸው፡-

1. የእመቤታችን ድንግል ማርያም መለኮታዊ እናትነት (የአምላክ እናት መሆኗ)

2. እመቤታችን ድንግል ማርያም ከወሊድ በፊት፣በወሊድ ጊዜ እና ከወለደችም በኋላ ለዘላለሙ ድንግል መሆኗ (ዘላለማዊ ድንግልና)

3. እመቤታችን ድንግል ማርያም ወደ ሰማይ መፍለሷ (መውጣቷ)

4. እመቤታችን ድንግል ማርያም ከአዳም ኃጢአት ነፃ መሆኗ (በንጽህና መጸነሷ) ናቸው።

የእመቤታችን ድንግል ማርያም ጉዳይ ባጠቃላይ የፕሮቴስታንቶች ዋነኛ የውይይት ነጥብ ነው። ከዚህ ባሻገር በመካከላችን ባሉት እና መሠረታዊ ልዩነት ባላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ጥረት አድርግ (ለምሳሌ የሐዋርያት የሥልጣን ተዋረድ፣ ቅዱስ ቁርባን፣በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለን አመለካከት ወ.ዘ.ተ ዙርያ መወያየት)። ነገር ግን ስለ እመቤታችን ድንግል ማርያም የሚሰነዘሩትን ሐሳቦች በሚገባ ለማስተናገድ ዝግጅ መሆን አለብህ።

 በመሆኑም ስለ እመቤታችን ድንግል ማርያም የጠቅስናቸውን አራቱን የሃይማኖት ቀኖናዎች ጠቅሰህ ለመወያየት ከመጀመርህ በፊት በፕሮቴስታንት ወዳጆችህ ‹‹የአዳኛችንን እናት ማክበራችን ችግሩ ምንድን ነው?››የሚል ጥያቄ አቅርብላቸው።

እግዚአብሔር ራሱ እመቤታችን ድንግል ማርያምን የአንድ ልጁ እናት አድርጎ ሲመርጣት ከፍጥረታች ሁሉ የሚበልጥ ክብር እንደሰጣት ጠቁማቸው። በዚህ መሠረት ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ስታከብር የእግዚአብሔር መልካም አብነት በመከተል ነው። እመቤታችን ድንግል ማርያም ያላት ልዩ ቦታ እና የተሰጣት ትልቅ ክብር ሰጪ እና ባለቤት ራሱ እግዚአብሔር ነው እንጂ ሰው አይደለም።

ይህንን ዝግጅት በድምጽ ለማዳመጥ ተጫወት የሚለውን ምልክት ይጫኑ

 የሉቃስ ወንጌል 1፡26-56 ያለውን ክፍል አንብብ። ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን «ጸጋን የተሞላሽ.........» ብሎ ሰላምታ በማቅረብ እጅ ሲነሳ እንዴት ባለ ትልቅ ትህትና እና ክብር እንዳከበራት አስተውል። ኤልሳቤጥ ‹‹በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ›› ማርያምን ሁለት ጊዜ «ብፅዕት» እያለች እንደጠራቻት ተመልከት። በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ቅድስት ኤልሣቤጥ ድምጿን ከፍ አድርጋ ‹‹የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል›› በማለት በታላቅ አክብሮት እንደተቀበለቻት አስተውል።

 በቁጥር 48 ላይ እመቤታችን ድንግል ማርያም ትውልድ ሁሉ ብፅዕት እያለ እንሚጠራት ትንቢት ተናግራለች። ስለዚህ ካቶሊካዊያን እንደሚሉት ሁሉ ፕሮቴስታንቶች እመቤታችንን ስለምን ‹‹ብፅዕት›› ብለው እንደማይጠሯት ጠይቃቸው። ፕሮቴስታንቶች እመቤታችንን ‹‹ማርያም›› ወይም ደግሞ ምናልባት ‹‹ድንግል ማርያም›› ብለው ይጠሯታል እንጂ በፍፁም ‹‹ብፅዕት ድንግል ማርያም›› ብለው አይጠሯትም። እዚህ ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያላቸው ካቶሊካዊያን ናቸው እንጂ ፕሮቴስታንቶች አለመሆናቸውን እንዲያስተውሉ ጋብዛቸው።

እመቤታችንን ማክበር መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው መሆኑን በሚገባ ካስረዳህ በኋላ አራቱን ቀኖናዎች ለመዳሰስ አትሞክር፣ ምክኒያቱም ይህ ሰፋ ያለ ሰዓት ይወስድብሃል፤ የጎንዮሽ ተዛማጅ ርዕሶቹም በርከት ያሉ ስለሆኑ የውይይትህን ጥንካሬ ያለዝብብሃል።

በውይይትህ ስኬታማ ለመሆን ከዚህ በሚከተሉት ምክኒያቶች መሠረት ትኩረትህን የእመቤታችን መለኮታዊ እናትነት ላይ በማድረግ ጀምር።     

1. ይህ የመጀመርያው እና ከሁሉ የሚበልጥ ሥጦታዋ ነው፤ ሌሎቹ ሁሉ ከዚህ የሚከተሉ ናቸው። ፕሮቴስታንቶች ይህንን መረዳት እና መቀበል ከቻሉ ሎሎችን በቀላሉ ለመገንዘብ ይችላሉ።

2. ይህ ቀኖና በመጽሐፍ ቅዱስ እና በታሪክ ውስጥ በሚገባ የተገለጠ በመሆኑ ለመከላከል ይቀልሃል።

3. የፕሮቴስታንት መሥራቾች እና የእምነቱ ምሰሶዎች የሆኑት ሉተር፣ካልቪን እና ዝውንግሊ ይህንን (የእመቤታችንን የአምላክ እናትነት) በሙሉ ልባቸው ተቀብለውታል።

ለአብዛኞቹ ፕሮቴስታንቶች ይህ እንግዳ ነገር ነው፤ እነ ሉተር ምንም እንኳን በርካታ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቀኖናዎችን ቢቃወሙም የእመቤታችን ድንግል ማርያምን የአምላክ እናትነት ተቀብለው ክብር ይሰጧት እንደነበር እና በዘላለማዊ ድንግልናዋ ያምኑ እንደነበር ማሳየቱ ጠቃሚ ነው።

ክርስቲያኖች ሁሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ድንግል ማርያም መወለዱን ያምናሉ። እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ያምናሉ። እንግዲህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም በመወለዱ ምክንያት እመቤታችን ድንግል ማርያም የወልደ እግዚአብሔር እናት ሆናለች፤ ስለዚህ በአጭሩ እመቤታችን ድንግል ማርያም የአምላክ እናት ነች።

እመቤታችን ድንግል ማርያም የአምላክ እናት መሆኗን የሚክድ ሰው ሁሉ ‹‹ቃል ሥጋ ሆነ›› የሚለውን የመዳኛችንን አንኳር ነጥብ ይክዳል። ይህን በማድረጉ ሁለት ነገር ይናገራል፡- አንድም ኢየሱስ አምላክ አይደለም እያለ ሲሆን ሌላም ደግሞ ኢየሱስ ሁለት ነው፤ አንደኛው ሰው ሲሆን ሌላኛው አምላክ ነው እያለ ነው ማለት ነው።

ፕሮቴስታንቶች በዚህ ውይይት ውስጥ ይህንን ጥያቄ ያነሳሉ ‹‹እንደማንኛውም የሰው ልጅ ፍጡር የሆነችው ማርያም እንዴት ፈጣሪን ልትወልድ ትችላለች?›› ዘላለማዊው ወልደ እግዚአብሔር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሥጋ የለበሰው አምላክ የሰውን ባሕርይ ለብሷል፤ ይህንንም ለማድረግ እንደሰው ልጆች ሁሉ ከሴት ተወልዷል።

 

ምንጭ፡ “የእምነት ቀናኢነት፣ ካቶሊካዊት እምነትን ማወቅ፣ መጠበቅ እና መንከባከብ፥ ካቶሊካዊ እምነታችንን ለሌሎች ማካፈል” በሚል አርዕስት የአዲስ አበባ ካቶሊካዊ ሰበካ የሐዋርያዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በ2010 ዓ.ም ካሳተመው መጽሐፍ ላይ የተወሰደ።

13 June 2024, 18:17