የሐምሌ 21/2016 ዓ.ም የ15ኛው እለተ ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የሐምሌ 21/2016 ዓ.ም የ15ኛው እለተ ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የሐምሌ 21/2016 ዓ.ም የ15ኛው እለተ ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

“ራሳችሁን በክርስቶስ ከሚገኘው ደስታ አታርቁ!”

የእለቱ ንባባት

1.    አሞጽ 7፡12-15

2.    መዝሙር 84

3.    ኤፌሶን 1፡3-14

4.    ማርቆስ 6፡7-13

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ላከ

ዐሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፣ ሁለት ሁለቱን ላካቸው፤ በርኩሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው።

ይህንም ትእዛዝ ሰጣቸው፤ “ለመንገዳችሁ ከበትር በስተቀር፣ እንጀራ ወይም ከረጢት ወይም ደግሞ ገንዘብ በመቀነታችሁ አትያዙ፤ ጫማ አድርጉ፤ ነገር ግን ሁለት እጀ ጠባብ አትልበሱ፤ ወደ አንድ ቤት በምትገቡበት ጊዜ ከዚያች ከተማ እስክትወጡ ድረስ እዚያው ቈዩ፤ የትኛውም ቦታ የማይቀበላችሁ ወይም የማይሰማችሁ ከሆነ፣ ከዚያ ስፍራ ስትወጡ ምስክር እንዲሆንባቸው ከእግራችሁ ሥር ያለውን ትቢያ በዚያ አራግፉ።”

እነርሱም ከዚያ ወጥተው፤ ሰዎች ንስሓ እንዲገቡ ሰበኩ፤ ብዙ አጋንንት አስወጡ፤ ብዙ ሕመምተኞችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱ።

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ ወንድሞቼና እህቶቼ እንደምን ከረማችሁ!

በዛሬው እለት ሥርዓተ አምልኮ ላይ የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል (ማር. 6፡7-13) ኢየሱስ አስራ ሁለቱን [ሐዋርያት] ቅዱስ ወንጌልን እንዲሰብኩ የላከበትን ቅጽበት ይተርካል። እያንዳንዳቸውን “ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ” (ማር 3፡14) ከጠራ በኋላ፣ አስተምህሮውን በማዳመጥ እና የፈውስ ምልክቱን ከተመለከቱ በኋላ፣ “ዐሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፣ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው፤ በርኩሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው” (6:7) ሊጎበኛቸው ወደሚሄድባቸው መንደሮች ይልካቸዋል። የጌታን ትንሳኤ ተከትሎ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንዲተገብሩ የሚላኩበት ተልእኮ “ልምምድ” ዓይነት ነው።

በእዚህ ቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ ቆም ብለን የሚስዮናውያንን ዘይቤ በሁለት ነጥቦች ልናጠቃልል እንችላለን፥ ተልዕኮው ማእከል አለው፤ ተልዕኮው ፊት ወይም ገጽታ አለው።

በመጀመሪያ ደረጃ፣ የሚስዮናዊው ደቀ መዝሙር የማመሳከሪያ ማዕከሉ እሱ ራሱ ኢየሱስ ነው። ትረካው ይህንን የሚያመለክተው እርሱን እንደ ርእሰ ጉዳይ ያሉትን ተከታታይ ግሦች በመጠቀም ነው - “ጠራቸው”፤ "መላክ ጀመረ"፣ "ሥልጣን ሰጣቸው"፣ “አዘዛቸው”፣ “አላቸው” (ማር. 6፡ 7፣8፣10) — ስለዚህም የአሥራ ሁለቱ መውጣትና መሥራት ከመሃል ላይ እየፈነጠቀ እንዲመስል፣ የኢየሱስን መገኘትና ሥራ በእነርሱ ውስጥ ያረጋግጣል። ሚስዮናዊ ድርጊቶች ናቸው። ይህ የሚያሳየው ሐዋርያት የኢየሱስ “መልእክተኞች” ሆነው እንደሚናገሩ እና እንደሚሠሩ እንጂ የሚሰብኩት የራሳቸው ምንም ነገር ወይም የመገለጥ ችሎታ እንደሌላቸው የምያሳይ ነው።

ይህ የወንጌል ክፍል እኛንም የሚመለከተው ለካህናቱ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የሕይወት ዘርፎች ስለ ክርስቶስ ወንጌል ለመመስከር ለተጠሩ የተጠመቁ ሰዎች ሁሉ ነው። ለእኛም ይህ ተልእኮ ትክክለኛ የሆነው ኢየሱስ እስከሆነ ድረስ በማይለወጥ ማእከል ውስጥ እርሱ ሊኖር እንደ ሚገባ ማወቅ የግድ ነው። የታማኝ ግለሰቦች ወይም የቡድኖች ተነሳሽነት ሳይሆን ትልቅ ስብሰባዎች እንኳን አይደሉም። የማይነጣጠል ከጌታዋ ጋር የተዋሃደች የቤተክርስቲያን ተልእኮ ነው። ማንም ክርስቲያን ወንጌልን “በራሱ/በራሷ” አያውጅም፣ ነገር ግን የተላከው ከኢየሱስ ትእዛዝ በተቀበለችው ቤተክርስቲያን ብቻ ነው። በእርግጥም ሚስዮናውያን የሚያደርገን ጥምቀት ነው። ወንጌልን መስበክ፣ ኢየሱስን ማወጅ የማይፈልግ ምስጢረ ጥምቀትን የተቀበለ ሰው እርሱ ጥሩ ክርስቲያን አይደለም።

ሁለተኛው የሚስዮናውያን ዘይቤ ባህሪ ሊሆን የሚገባው የኢየሱስን የፊት ገጽታ መመስከር ሲሆን እሱም በድህነት መኖርን ያካትታል። የእሱ ጌጥ ለትህትና መስፈርት ምላሽ ይሰጣል። በእርግጥም ለአሥራ ሁለቱ የተሰጣቸው ትእዛዝ ለጉዟቸው ከበትር በቀር ምንም አትያዙ የሚለው ነው። እንጀራም የለም፣ ከረጢትም የለም፣ በመታጠቅያቸው ገንዘብ የለም” (6፡8)። መምህሩ ነፃና ያልተደናቀፈ፣ ያለ ምንም ጥቅማ ጥቅሞች፣ በላካቸው ፍቅር ብቻ የተወሰነ፣ ሊሰብኩ በሚሄዱበት በቃሉ ብቻ እንዲጸኑ ይፈልጋል። በትሩና ጫማው የመንፈሳዊ ንግደት ጉዞ መጠቀሚያዎች ናቸው፣ ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንግሥት መልእክተኞች እንጂ ሁሉን ቻይ አስተዳዳሪዎች ሳይሆኑ፣ መተኪያ የሌላቸው ባለሥልጣኖች ሳይሆኑ፣ በጉብኝት ላይ ያሉ ታዋቂ ሰዎች አይደሉም፣ ነገር ግን የእግዚአብሔር ምስክሮች ናቸው።  እስቲ የአንዳንድ ቅዱሳንን ሕይወት እንመልከት ባለሥልጣኖች ወይም ነጋዴዎች አልነበሩም፣ ይልቁንም ትሑት የመንግሥቱ ሠራተኞች ነበሩ። የነበራቸው ፊት ይህ ነበር። እናም የዚህ “ፊት” መልእክቱ የተቀበለበት መንገድም ነው፣ አንድ ሰው አቀባበል እንዳልተደርገለት ሆኖ ሊሰማው ይችላል፣ “የትኛውም ቦታ የማይቀበላችሁ ወይም የማይሰማችሁ ከሆነ፣ ከዚያ ስፍራ ስትወጡ ምስክር እንዲሆንባቸው ከእግራችሁ ሥር ያለውን ትቢያ በዚያ አራግፉ”  (ማር. 6፡11)። ይህ ደግሞ ድህነት ነው፡ የውድቀት ልምድ። የተናቀው እና የተሰቀለው የኢየሱስ ልምድ የመልእክተኛውን እጣ ፈንታ እንደ ላኪው ሊሆን ይችላል። እናም ከሞተውና ከሙታን ከተነሣው ጋር ከተባበርን ብቻ ነው ወንጌልን ለመስበክ ድፍረት ማግኘት የምንችለው።

የእግዚአብሔር ቃል የመጀመሪያዋ ደቀ መዝሙርና ሰባኪ ድንግል ማርያም በትህትናና በደስታ የቅዱስ ወንጌልን መልእክት ለዓለም እናደርስ ዘንድ እርሷ በአማላጅነቷ ትርዳን።

አዘጋጅ እና አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ - ቫቲካን  

 

 

27 July 2024, 07:44