የሐምሌ 21/2016 ዓ.ም ዘክረምት 4ኛ ሰንበት ምንባባት እና ቃለ እግዚኣብሔር የሐምሌ 21/2016 ዓ.ም ዘክረምት 4ኛ ሰንበት ምንባባት እና ቃለ እግዚኣብሔር  (©khanchit - stock.adobe.com)

የሐምሌ 21/2016 ዓ.ም ዘክረምት 4ኛ ሰንበት ምንባባት እና ቃለ እግዚኣብሔር

የእለቱ ምንባባት

1.     2ቆሮ 9፡1-15

2.     1ጴጥ 3፡15-22

3.     ሐዋ 27፡21-32

4.     ማቴ 24፡36-51

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የሚመጣበት ቀንና ሰዓት አለመታወቁ

 “ያን ቀንና ሰዓት ግን ከአብ በስተቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፣ ወልድም ቢሆን ማንም አያውቅም። ልክ በኖኅ ዘመን እንደሆነው የሰው ልጅ መምጣትም እንደዚሁ ይሆናል፤ ከጥፋት ውሃ በፊት ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፣ ሲያገቡና ሲጋቡ እንደ ነበሩ፣ እስከዚያ ጊዜ ድረስም ምን እንደሚመጣ ሳያውቁ ድንገት የጥፋት ውሃ እንዳጥለቀለቃቸው፣ የሰው ልጅ ሲመጣም እንደዚሁ ይሆናል በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በዕርሻ ላይ ይውላሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል።ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች፣ ሌላዋ ትቀራለች።

 “እንግዲህ ጌታችሁ የሚመጣበትን ቀን ስለማታውቁ ነቅታችሁ ጠብቁ። ይህን ልብ በሉ፤ ባለቤት ሌሊት ሌባ በየትኛው ሰዓት እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፣ በነቃ፣ ቤቱም እንዳይደፈር በተጠባበቀ ነበር። የሰው ልጅም ባላሰባችሁት ሰዓት ይመጣልና እናንተም እንደዚሁ ዝግጁ ሁኑ።

 “በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን እንዲሰጣቸው ባለቤቱ በቤተ ሰዎቹ ላይ የሾመው ታማኝና ብልኅ አገልጋይ እንግዲህ ማነው? ባለቤቱ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ የተጣለበትን ዐደራ እየፈጸመ የሚያገኘው ያ አገልጋይ የተባረከ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ በንብረቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል። ነገር ግን ያ አገልጋይ ክፉ ቢሆንና ለራሱ፣ ‘ጌታዬ ይዘገያል’ በማለት፣ ተነሥቶ ሌሎች አገልጋይ ባልንጀሮቹን መምታት ቢጀምር፣ ከሰካራሞችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፣ እርሱ ባልጠበቀው ቀንና ባላሰበው ሰዓት ጌታው መጥቶ፣ይቈራርጠዋል፤ ዕድል ፈንታውንም ከግብዞች ጋር ያደርግበታል፤ በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።

 

የእለቱ አስተንትኖ

የተወደዳሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

የዓለም መድኃኒት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ጊዜ በኢየሩሳሌም ከተማ እየተዘዋወረ ሲያስተምር ሳለ የከተማው ሕዝብ ለስጋዊ ሕይወታቸው ሲወጡ ሲወርዱ ለመንፈሳዊ ሕይወታቸው ግን ምንም ዓይነት ደንታና ጥንቃቄ ባለማድረግ ወዲያ ወዲህ ሲሉ ተመለከተ፡፡ በዚያን ጊዜ ሰዎቹን ለማስጠንቀቅ ከላይ በመሪ ጥቅሱ ላይ እንደተመለከተው “የሰው ልጅ ክርስቶስ በማታስቡበት ሰዓት ስለሚመጣ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ” በማለት ስለሚመጣው ዓለምና ስለ መንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲያስቡ መከራቸው፡፡ በኖህ ዘመን በነበሩት ሰዎች ላይ ድንገት አደጋና ጥፋት እንደደረሰባቸው በእነርሱም ላይ ከባድ አደጋና ጥፋት ሊደርስባቸው እንደሚችል አስጠነቀቃቸው፡፡

በብሉይ ኪዳን ዘመን ከነበሩት የጥንት አበው ማለትም ከአባታችን አዳም አስረኛ ትውልድ የነበረው ኖኅ በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ምንም በደል ያልሰራና የእግእዚአብሔር መንገድ ይከተል የነበረ ደግ ሰው ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “ኖኅ ጻድቅና ፍጹም ሰው ነበር” (ዘፍ 6፡9) ይለናል፡፡ ምንም እንካ ኖኅ በዚያ በክፉና በኃጢአተኛ ኅብረተሰብ መካከል ቢኖርም እንደ እነርሱ በክፋትና በኃጢአት አልረከሰም፡፡

በኦሪት ዘፍጥረት እንደምናነበው በኖኅ ዘመን የነበሩ ሰዎች እጅግ አመጸኞችና ሥራቸው ብቻ ሳይሆን ሐሳባቸውም ሁሉ ዘወትር ክፋት ብቻ ነበር፡፡ በሴቶችና በወንዶችም ላይ እጅግ የሚያስነውር ኢሞራላዊ ድርጊት ይፈጽሙ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ የነበሩ ሰዎች ይሰሩ የነበሩትን የከፋ ኃጢአት በተመለከተ ጊዜ እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ በልቡም እጅግ አዘነ፡፡ እግዚአብሔርም አለ የፈጠርሁትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ አለ፡፡ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር ለሰው አገልግሎት እንዲውሉ የተፈጠሩትንም እንስሳትና ሌሎች ፍጥረቶች ሁሉ ከምድር ላይ ለማጥፋት እንደ ወሰነ ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል (ዘፍ. 7፡6-8)፡፡

ሆኖም እግዚአብሔር ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ቅጣትን ወይም ጥፋትን በሰዎች ላይ አያመጣም፡፡ ጌታም ከዕለታት በአንድ ቀን ወደ ኖኅ መጥቶ የምድር ሰዎች ክፋትና ኃጢአት በመብዛቱ ሰዎችን በጥፋት ውኃ ለማጥፋት እንደወሰነ ለኖኅ ነገረው፡፡ ይህ ዜና ኖኅን እጅግ አሳዝኖት ነበር፡፡ ስለዚህ ኖኅ የጥፋት ውኃ በምድር ላይ እንደሚመጣ በማስጠንቀቅ ለሕዝቡ ሁሉ ከክፉ ስራቸውና ከኃጢአታቸው እንዲመለሱ ነግሮአቸው ነበር፡፡ ግን ኖኅን ማንም ሊሰማው አልፈለገም፡፡ ጌታችን እግዚአበሔር አብም ኖኅና ቤተሰቦቹ እንዲሁም የፈለገ ሁሉ እንዲድንበት አንድ ታላቅ መርከብ እንዲሰራ ኖኅን አዘዘው፡፡ ይህንንም መርከብ ለመሥራት ብዙ ዓመታት ፈጅቶበታል፡፡ ሰዎች መጀመሪያ ትልቅ ቤት የሚሰራ መስሎአቸው ነበር። ከጥፋት ውሃ የሚድንበት መርከብ መሆኑን ሲነግራቸው ግን ሁሉም ይስቁበት ጀመር። አንዳንዶቹም ይህ ሽማግሌ አበደ ጃጀ እያሉ መሳቂያ መሳለቂያ አደረጉት። ኖህ ለማስረዳት ቢሞክርም ማንም አልሰማውም ስለዚህ የመርከቡን ስራ እየሰራ ሰዎቹን ከሃጢአታቸው እንዲመለሱ ይመክራቸው ነበር። እርሱም ጌታ በአመለከተው መሰረት መርከቡን ሰርቶ ጨረሰ።

ጌታችን እግዚአብሔር አብ ኖህን ከእርሱና ከቤተሰቡ ጋር በሕይወት እንዲጠበቁ ከሀያዋን ፍጥረቶች ሁሉ ከእንስሳቱም ከአራዊቱም ሁለት ሁለት ወንድና ሴት ወደ መርከቡ ውስጥ እንዲገቡ በመርከቡ ውስጥ የተለየ ክፍል እንዲያዘጋጅ አዞት ነበር። እንግዲህ የመርከቡ ስራ ከአለቀና ጊዜው ከደረሰ በሁዋላ ኖህ የመርከቡን በር ከፍቶ እንስሳቱንና አራዊቱን ሁሉ እንዲያስገባና በመጨረሻም እሱና ቤተሰቦቹ እንዲገቡ አዘዘው። በሩ በተከፈተ ጊዜ እንስሶችና የዱር አራዊቱ በማይታይ እጅ እየተነዱ ወደ መርከቡ ገቡ በመጨረሻም ኖህና ቤተሰቡ ወደ መርከቡ ከገቡ በሁዋላ የመርከቡ በር ከውጭ ከርችሞ ዘጋው። በጌታ ትእዛዝ የጥፋት ውሃ የሚወርደው ከሰባት ቀናት በኋላ ነበር።

ኖህ ወደ መርከቡ ከገባ እስከ ሰባት ቀን ድረስ ምንም ዝናብ ባለመዝነቡ ከውጭ የነበሩት የጥፋት ውሃ የቀረ መስሎአቸው በኖህ ላይ ይስቁ ይሳለቁ ጀመር። ሆኖም ከሰባት ቀናት በሁዋላ ከባድ ዝናም መዝነብ ጀመረ። ከምድር በታች ያለው የታላቁ ቀላይ ምንጮች ተነደሉ የሰማይም መስኮቶች ተከፈቱ ዝናቡም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ይወርድ ጀመር (ዘፍ 7፡11-12)። ምድር ሁሉ በውሃ ተሸፈነች ተጥለቀለቀች። ቦታው ሁሉ ሃይቅና ባህር ሆነ ሰዎች ሁሉ መድረሻ አጡ። ሁሉም ወደ ከፍተኛና ተራራማ ቦታ መራራጥ ሆነ ብዙዎች ደግሞ ወደ መርከቡዋ በመሄድ ክፈትለን! ከፈትልን! እያሉ ወደ ኖህ ይጮሁና ይማጠኑ ጀመር። ጌታ የዘጋውን ማን ሊከፍተው ይችላል? የውሃው ሃይል ከላይም ከታችም እየበዛ በመሄዱ ሁሉም በጥፋት ውሃ ሰጥመው አለቁ፡ ሴቱ ወንዱ ሕይወት ያለው ሁሉ በውሃ ሰጥሞ ቀረ።

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ለጅ ክርስቶስ በማታስቡበት ሰዓት ስለሚመጣ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ በማለት ሲያስተምር በኖህ ዘመን የደረሰውን ይህን የጥፋት ውሃ መውረድ እንደ ምሳሌ አድርጎ የጠቀሰው እኛም ንስሃ ገብተንና ተጸጽተን ከሃጢአታችን ሳንመለስ ዕለተ ሞታችን ቶሎ እንዳይደርስብን ለማስጠንቀቅ ነው። ደካሞች ሰዎች ስለሆንን በየጊዜው በየቀኑ እንድያውም በየሰዓቱ ሃጢአት ክፋት ተንኮል በመስራት በመመቀኘት በመቅናት በትእቢት በማን አለብኝነት መንፈስ እግዚአብሔርን ስለምናስቀይመው በየጊዜው ንስሓ መግባት አለብን። የእግዚአብሔር ቃል የሚለንን መምህራኖቻችን የሚነግሩንን ሳንሰማ እየቀረን በሃጢአት ላይ ሃጢአት እየጨመርን ከሄድን በኖህ ዘመን እንደነበሩት ሰዎች የጥፋት ውሃ ሊመጣብን ይችላል። ዛሬ በዘመናችን እየተከሰቱ የምናያቸው ሁሉ ሳንረዳቸው ቀርተን ነው እንጂ የዚያ ምልክቶች ናቸው በሩቅ ምስራቅ የሚደርሱ እጅግ አስፈሪ የጎርፍ መጥለቅለቅና የምድር መናወጥ አይነተኛ ምልክቶች ናቸው። እንደዚሁም የጥፋት ውሃ ብቻ ሳይሆን ካልታዘዝን ካልተገዛንለት ካላከበርንው ጌታ በእያንዳንዳችን ላይ የተለያየ መቅሰፍት ሊያመጣብን ይችላል። ስለዚህ ሁላችንም ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ተዘጋጅተን መኖር አለብን። ቅድስት ቤተክርስቲያናችንም ለዚህ ጉዞ ይረዱን ዘንድ የተለያዪ መንገዶችን አዘጋጅታልናለች ለምሳሌ የመቁጠሪያ ጸሎት በጋራም ይሁን በግል የቅዱስ ቁርባን ስግደት የቅዳሴ ስርዓት በተለይም በመስዋዕተ ቅዳሴ ጊዜ የምንካፈለው የጌታ ስጋና ደም ለዚህ ሕይወት ዋነኛው መሳሪያችን ነውና በንስሃ ታጥበን ልንፈጽመው ይገባል። ጌታ የሚመጣበትን ሰዓት ማንም የሚያውቅ የለም። ዛሬ ነገ ተነገ-ወዲያ ሊሆን ይችላል ስለዚህ ጌታ ሁልጊዜ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ ይለናል። ልዑል እግዚአብሔር ከክፉ ነገር ከድንገተኛ ሞት ይሰውረን!ለንስሃ ሞት ያብቃን አሜን!!!

ምንጭ፡ የቫቲካን ሬዲዮ የአማርኛው አገልግሎት ክፍል

አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

27 July 2024, 07:39