የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ  

አቡነ ኮዘንስ፥ በዘንድሮው የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ተአምራትን ለማየት እንደሚጠብቁ ተናገሩ

ዘንድሮ ለ10ኛ ጊዜ የተዘጋጀውን ብሔራዊ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤን ለመሳተፍ ከመላው ዩናይትድ ስቴትስ በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን በኢንዲያናፖሊስ ከተማ ተሰብሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኢንዲያናፖሊስ ውስጥ ከረቡዕ ሐምሌ 10-14/2016 ዓ. ም. በሚካሄደው ብሔራዊ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ላይ ለመገኘት በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናን ወደ ከተማይቱ ገብተዋል።

ከግንቦት 9/2016 ዓ. ም. ጀምሮ በአራት ልዩ ልዩ ሥፍራዎች ሲደረግ በቆየው መንፈሳዊ ጉዞ ላይ ከ100,000 የሚበልጡ ምእመናን የተሳተፉ ሲሆን ከ10,000 በላይ ኪሎ ሜትሮችን እንደተጓዙ ተነግሯል።

የኢንዲያናፖሊስ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቻርልስ ቶምፕሰን የመሩትን መስዋዕተ ቅዳሴ በርካታ መንፈሳዊ ተጓዥ ምዕመናን የተካፈሉት ሲሆን፥ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጉባኤው ተወካይ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግል እና የጉባኤው አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሚኒሶታው ጳጳስ አቡነ አንድሪው ኮዘንስ ተካፍለዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ የሚካሄደውን አሥረኛ ብሔራዊ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ በገንዘብ የደገፈው የአሜሪካ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሲሆን፥ ከፍተኛ ዕድገት የታየበት እና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እንደሆነም ተገልጿል።

“ሚስዮናዊ ደቀ መዛሙርት ለመሆን ተጠርተዋል!”
በመላ ሀገሪቱ ውስጥ ባሉ ቁምስናዎች ዘንድ ከፍተኛ መበረታታት የታየበት የቅዱስ ቁርባን ጉባኤው በሦስተኛ የፍጻሜ ዓመት ላይ እንደሚገኝ ሲታወቅ፥ የጉባኤው አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቡነ አንድሪው ኮዘንስ ከቫቲካን ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ ዓመቱ የሚሲዮናዊነት ዓመት በመሆኑ “እያንዳንዱ ካቶሊክ ምዕመን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ጥሪ ተቀብሎ ሚስዮናዊ ደቀ መዛሙር እንዲሆን እንጋብዛለን” ብለዋል።

የአሜሪካ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የወንጌል ደስታ” በሚለው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያቸው በኩል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2013 ዓ. ም. በላኩት ጥሪ በመነሳሳት በዛሬው ዓለም ወንጌልን በማወጅ ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፥ “እርስ በርስ ‘መገናኘት’ እና ‘ተልዕኮ’ የሚሉት ከቅዱስ ቁርባን ጉባኤ የሚገኙ ሁለት ዋና ዋና ማነቃቂያዎች ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል።

አቡነ ኮዘንስ፥ “ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲቀበሉት እና ወደ ተልዕኮ እንዲገቡ እንፈልጋለን” ብለው፥ “እርስ በርስ መገናኘት እና ተልዕኮ “የወንጌል ደስታ” በሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ውስጥ የተጠቀሱ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

“በጉባኤው መሃል ተአምራትን እንጠብቃለን!”
አቡነ ኮዘንስ ከቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ስለሚጠብቋቸው ነገሮች ተጠይቀው ሲመልሱ፥ ተአምራትን ለማየት እንደሚጠብቁ፥ “ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በሚሰበሰቡበት ጊዜ እርሱ በኃይል እንደሚገለጥ፣ በዚህም የተነሳ ጥልቅ ለውጦችን፣ ፈውሶችን እና ከሁሉም በላይ የሚስዮናዊነት መንፈስ እውነተኛ ዕድገትን እንጠብቃለን” ብለዋል።

“በልባችን እሳት እንዲቀጣጠል እንፈልጋለን!”
“የቅዱስ ቁርባን ማነቃቂያ” የሚለውን የሦስተኛ እና የመጨረሻ ዓመት መሪ ሃሳብ ያስታወሱት አቡነ ኮዘንስ፥ “ዓላማችን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጠየቁት የሚስዮናዊነት ለውጥ በዩናይትድ ስቴትስ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲመጣ መርዳት እና የተጠራነውም ሚስዮናውያን ለመሆን ነው” በማለት በቃለ ምልልሳቸው ገልጸዋል።

አቡነ ኮዘንስ አክለውም፥ “በዓለማችን ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ እና ሕይወቱ እንዲገለጥ በሚፈለግበት በዚህ ጊዜ በመሰብሰባችን ክብር ይሰማናል” ብለው “በቅዱስ ቁርባን በኩል ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቱን ለዓለም እንደሰጠ ስለምናውቅ፥ ለሚያስፈልጋቸው በሙሉ እርሱን ማድረስ እንድንችል ልባችን በመንፈስ ቅዱስ እሳት እንዲቀጣጠል እንፈልጋለን” ብለዋል።

 

18 July 2024, 13:07