የሱዳን ግጭት እየተባባሰ በመምጣቱ የሃገሪቱ ብጹአን ጳጳሳት የሰላም ጥሪ አቀረቡ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የሱዳን እና የደቡብ ሱዳን የካቶሊክ ጳጳሳት ሱዳንን ለሁለት ከፍሎ ቀውስ ውስጥ እየከተታት ያለው አስከፊ ጦርነት በአስቸኳይ እንዲያቆም ተማጽነዋል።
ሱዳንን ለ30 ዓመታት ያክል ያስተዳደሩት ኡመር ሀሰን አልበሽር በህዝባዊ አመጽ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ሀገሪቱ ፓለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ገብታለች። የአል በሽርን ከስልጣን መወገድ ተከትሎ ወታራዊ እና ሲቪል አስተዳደርን ያካተተ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሞ የነበረ ቢሆንም ወታደሮቹ የሲቪል አስተዳደሩን የሚመሩንትን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክን በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን አስወግደዋል።
መፈንቅለ መንግስቱን በመሩት ሁለቱ ጀነራሎች መካከል ጸብ ተፈጥሮ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ የተቀሰቀሰው ጦርነት እስካሁን መቋጫ አላገኘም። በጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ ሚሊዮኖች ደግሞ ከቀያቸው ተሰድደዋል።
ብጹአን ጳጳሳቱ ሰሞኑን ባወጡት መግለጫ “የሱዳን ህዝብ መዋቅር ተበጣጥሷል፣ ህዝቡ ከፍተኛ ደረጃ ያለውን ጥቃት እና የጥላቻ መንፈስ በማየቱ ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ገብቷል” በማለት ነበር የገለጹት።
የግጭቱ ዋና ተሳታፊዎች የሱዳን ጦርን የሚመሩት ጀነራል አብዱልፈታ አልቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎችን የሚመሩት ጀነራል መሀመድ ሀምዳን ደጋሎ ወይም በቅጽል ስማቸው ሄሜቲ የሚባሉት ሲሆኑ፥ በሁለቱም ሃይሎች መካከል እየተባባሰ የመጣው ግጭት መጨረሻ ያለው አይመስልም።
መጨረሻ የለውም
የሱዳን ጦር ሃይል መሪ ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን የእርስ በርስ ጦርነቱን ለማስቆም እንዲቻል እየተሞከሩ ያሉ የውይይት በሮችን በማያወላውል ሁኔታ የዘጉ ሲሆን፥ “በዚህ ጦርነት ድል እስከምናገኝ ድረስ እንቀጥላለን፣ አሁንም እደግመዋለሁ፣ ከሚያጠቃንና መሬታችንን ከሚይዝ ጠላት ጋር አንደራደርም” ሲሉ ጄኔራሉ በሳቸው ቁጥጥር ሥር በምትገኘው በዋና ከተማይቱ ካርቱም ዙሪያ በሚገኙ አካባቢዎች ላይ ያሉ ወታደሮቻቸውን በጎበኙበት ወቅት ተናግረዋል።
የሱዳን ዋና ከተማ የሆነችው ካርቱም በሁለቱ ሃይሎች መካከል ከአንድ ዓመት በላይ በቆየ የከረረ ጦርነት ዋና ማዕከል ሆና ቆይታለች።
አል-ቡርሃን ለዓለም አቀፍ ጫና እንደማይንበረከኩ እና በሳውዲ አረቢያ ጂዳህ ከተማ በተደረገው የድርድር ጠረጴዛ ላይ ለመቀመጥ ፈቃደኛ አለመሆናቸውንን በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
ፊደስ የዜና አገልግሎት እንደዘገበው ጀኔራሉ “እነሱ ማለትም (አስታራቂዎቹ) ጆሯችንን ይዘው ሊጎትቱን ወደሚፈልጉበት የድርድር ጠረጴዛ አንሄድም፣ ጠላት መሬታችንን ተቆጣጥሮ እያለ፣ ብሎም ሀብታችንን እየዘረፈን ወደ ድርድር አንሄድም፥ ጠላት ከመውጣቱ በፊት ወደ ድርድር አንሄድም፣ አስታራቂዎቹ እንድንደራደር ከፈለጉ ይሄንን ማስገደድ አለባቸው” ብለዋል።
ሰብአዊ ቀውስ
በግጭቱ ወቅት እየደረሰ ያለው ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ በአዳዲስ ግዛቶች ላይ እያደረገ ባለው ከበባ ምክንያት ቢያንስ 55,000 ሰዎች የሴናር ዋና ከተማ የሆነችውን ሲንጃን ለቀው እንዲሰደዱ አድርጓል።
እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘገባ ከሆነ ጦርነቱ ሚያዚያ 2015 ዓ.ም. ላይ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ቢያንስ 10 ሚሊዮን ሱዳናውያን የተፈናቀሉ ሲሆን፥ በመጨረሻም ተፈናቃዮቹ ብዙውን ጊዜ እራሳቸውን የሚያገኙት ሁለቱ ቡድኖች በሚፋለሙባቸው አካባቢዎች ውስጥ ነው።
ከነዚህም መሃል የካርቱም አውራጃ በሆነችው በአል ሻጃራ ውስጥ በሚገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተቋም በሆነው የዳር ማርያም ትምህርት ቤት ውስጥ የተጠለሉ 80 ያህል ሰዎች ይጠቀሳሉ።
በታጣቂ ሃይሎቹ ካምፕ አቅራቢያ የሚገኘው ይህ አካባቢ የከባዱ ጦርነት ዋና ማዕከል ሲሆን፥ እዚህ አከባቢ የተጠለሉት ስደተኞች በቂ ንፁህ ውሃና ምግብ ባለማግኘታቸው ለከፋ ችግር እየተዳረጉ እንደሆነ እና እነሱን ከስፍራው ለማስወጣት የተደረገው ሙከራም እንዳልተሳካ ተገልጿል።
ራስ ወዳድነት ባህሪ ያለው ጦርነት
የሱዳን ብጹአን ጳጳሳት ሰኔ ወር ላይ ባደረጉት ስብሰባ ማጠቃለያ ላይ ግጭቱን እንዲከሰት ያደረጉትን የራስ ወዳድነት ፍላጎቶችን በጽኑ በማውገዝ፥ “ይህ በሁለት ጄኔራሎች መካከል የሚደረግ ጦርነት ብቻ አይደለም፣ ምክንያቱም ወታደሩ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ መዋቅር ውስጥ እራሱን ዘፍቋል ፤ ሁለቱም ሃይሎች የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ሲቆጣጠሩ ተጠቃሚ የሚሆኑ፣ በተለያዩ ነገሮች የሚደግፏቸው ባለሃብት ሱዳናውያን፣ ዓለም አቀፍ ታዋቂ ሰዎች እና ነጋዴዎች ጋር ትስስር አሏቸው። ከዚህም በተጨማሪ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ጨምሮ በጣም የተራቀቁ መሳሪያዎችን ከሚሰጧቸው የውጭ ዳጋፊ ሃይላት ጋር የተገናኙ ናቸው” ብለዋል ብጹአን ጳጳሳቱ።