የፓኪስታን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ተሻሽሎ የጸደቀውን አዲሱን የጋብቻ ሕግ አወደሱ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በፓኪስታን የሚገኙ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች የክርስቲያን ወንድ እና ሴት ልጆች ጋብቻ ዝቅተኛው ዕድሜ ወደ 18 ዓመት ከፍ የሚያደርገው የአዲሱን ሕግ መጽደቅ አድንቀዋል።
እንደ ጎሮጎሮሳውያኑ በ 1872 ዓ. ም. የወጣውን የክርስቲያን ጋብቻ ሕግ የሚያሻሽል አዲሱ ሕግ ከጥቂት ወራት በፊት በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ከፀደቀ በኋላ ባለፈው ሳምንት በብሔራዊ ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ ጸድቋል።
በቀድሞው ሕግ መሠረት፥ በሕንድ የብሪታንያ አገዛዝ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ልጃገረዶች በ13 ዓመታቸው ወንዶች ደግሞ በ16 ዓመታቸው ማግባት ይችላሉ።
ክርስቲያን ልጃገረዶችን ከግዳጅ ጋብቻ መጠበቅ
በፓኪስታን ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች በተለይ ልጃገረዶችን ከፆታዊ ጥቃት እና ግዳጅ ጋብቻ መጠበቅ የሚለውን ሕግ ሲደግፉት እና ለተግባራዊነቱም ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
የፓኪስታን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብጹዕ አቡነ ሳምሶን ሹካርዲን ከብሔራዊ የፍትህ እና ሰላም ኮሚሽን (NCJP) ጋር በመሆን እንዲሁም ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር በአዲሱ ሕግ መጽደቅ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።
የፓኪስታን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብጹዕ አቡነ ሳምሶን ሹካርዲን በመግለጫቸው፥ “ይህን ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምጽ በማጽደቁ ለመላው ፓርላማ ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን” ብለው፥“ይህ ሕግ ለጋብቻ ያልደረሱ ሴት ልጆቻችን ከግዳጅ ጋብቻ ለመጠበቅ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት፥ መንግሥትም የግዳጅ ጋብቻ ወንጀልን ለመከላከል ተጨማሪ እርምጃዎችን እንደሚወስድ ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።
አዲሱ የክርስቲያን ጋብቻ ሕግ
በፓክስታን የጸደቀው አዲሱ የክርስቲያን ጋብቻ ሕግ የሁለቱም ተጋቢዎች ዕድሜ 18 ዓመት ሲሞላ ብቻ እንዲፈጸም እና እንዲመዘገብ ይጠይቃል።
በተጨማሪም የማንኛውም ተጋቢዎች ዕድሜን በሚመለከት አለመግባባት ሲፈጠር ፍርድ ቤቱ ዕድሜያቸውን የሚወስነው በኮምፒዩተር በተመዘገበው የብሔራዊ መታወቂያ ካርድ፣ የልደት የምስክር ወረቀት፣ የትምህርት ማስረጃ ወይም ሌሎች ተያያዥ ሠነዶች መሠረት እንደሆነ፥ ነገር ግን እነዚህ ሠነዶች ከሌሉ ዕድሜው በሕክምና ምርመራ ዘገባ ላይ ተመሥርቶ ሊወሰን እንደሚችል ሕጉ ያሳስባል።