የቅዱስ ቁርባን ቡራኬ የቅዱስ ቁርባን ቡራኬ  (AFP or licensor)

ካርዲናል ፒየር፥ በቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ላይ እውነተኛ መንፈሳዊ መነሳሳት እንዲታይ አሳሰቡ

በአሜሪካ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ብጹዕ ካርዲናል ፒየር ክሪስቶፍ፥ በኢንዲያናፖሊስ በተዘጋጀው ብሔራዊ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ንግግር፥ በጉባኤው መካከል እውነተኛ መነሳሳት እንዲገለጥ ጠይቀው፥ ምእመናኑ ለታላቅ የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዲጸልዩ እና በተልዕኮአቸውም የበለጠ ፍሬያማ እንዲሆኑ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዘንድሮ ለ10ኛ ጊዜ በአሜሪካ ኢንዲያናፖሊስ ግዛት የተዘጋጀው ብሔራዊ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ከረቡዕ ሐምሌ 10-14/2016 ዓ. ም. የሚካሄድ ሲሆን፥ ብጹዕ ካርዲናል ፒየር ክሪስቶፍ በመክፈቻው ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ንግግር፥ የእርሳቸው በጉባኤው ላይ መገኘት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መንፈሳዊ ቅርበት እና ከአገሪቱ ሕዝቦች ጋር ያላቸውን አንድነት የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረው፥ “በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኩል እንደ ቤተ ክርስቲያን አንድ መሆን እንዴት ያለ ስጦታ ነው!” ሲሉ አወድሰዋል።

የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ብጹዕ ካርዲናል ፒየር ክሪስቶፍ እንደዚሁም፥ “ቅዱስ ቁርባን ለአንድነት ትልቅ ስጦታ ነው” ብለው፥ የጉባኤው ዋና ጸሎት መሆን ያለበት እንደ ቤተ ክርስቲያን በአንድነታችን ማደግን እና በተልዕኳችንም የበለጠ ፍሬያማ መሆንን ብለዋል።

ከቅዱስ ቁርባን የሚገኝ መንፈሳዊ መነሳሳት ምንድነው?
የቤተ ክርስቲያንን አንድነት እውን ለማድረግ “በቅዱስ ቁርባን መበረታታት ማለት ምንድን ነው?” የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ጠቃሚ እንደሆነ የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ፒየር፥ ምናልባት በይበልጥ “በቅዱስ ቁርባን አማካይነት መነሳሳትን እንደምናገኝ እንዴት እናውቃለን?” ሲሉ ጠይቀዋል።

እውነተኛ በቅዱስ ቁርባን መበረታታት ሁልጊዜ ለምስጢራት ባለን አክብሮት እነርሱም፥ በስግደት፣ በቡራኬ፣ በትምህርተ ክርስቶስ እና በመንፈሳዊ ዑደት የታገዘ መሆን አለበት ብለዋል። እውነተኛ መንፈሳዊ ጥንካሬ ማለት ኢየሱስ ክርስቶስን በሌሎችም ሰዎች ውስጥ ማየት፣ በቤተሰቦቻችን፣ በጓደኞቻችን እና በማኅበረሰቦቻችን ብቻ ሳይሆን ነገር ግን በዘር ወይም በመደብ በተከፋፈሉ፣ የእኛን ሃስብ በሚቃወሙ ወይም ከእኛ በተለየ መንገድ በሚያስቡ ሰዎች ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስን ማየት እንደሆነ አስረድተዋል።

“ከእንዲህ ዓይነት ሰዎች ጋር ስናገኛቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ድልድይ በመሆን ሕዝቦችን አንድ በማድረግ የአንድ አባት ልጆች የሆኑትን እና ወደ ዘላለማዊ ዕጣ ፈንታ የተጠሩትን ያገናኛቸዋል” ሲሉ ብጹዕ ካርዲናል ፒየር አስረድተዋል።

“ለአንድነት ተጠርተናል!”
“የአንድነት ድልድዮችን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት እውነተኛው የቅዱስ ቁርባን መታደስ ምልክት ነው” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፒየር ክሪስቶፍ፥ “ቅዱስ ቁርባንን ስናከብር የሰው ልጅ ከእርሱ ተለይቶ በነበረበት ጊዜ እንኳ ሰው ሆኖ የመጀመሪያውን ድልድይ የገነባው ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን እናውቃለን” ብለዋል።

በዚህ ምክንያት እውነተኛው መገናኘት ኢየሱስ ክርስቶስ በምስጢራት ማለትም በእንጀራ እና በወይን ጠጅ ውስጥ እንደሚገኝ ማመን ብቻ ሳይሆን በአማኞች ጉባኤ ውስጥም ጭምር፥ እንዲያውም በፍርሃታቸው ወይም በኃጢአታቸው ምክንያት የቆሰሉት እና ከእርሱም ጋር ለመገናኘት ጥረት በማድረግ ላይ በሚገኙ ሰዎች ውስጥ መኖሩን አስረድተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፒየር፥ “የቅዱስ ቁርባን ስግደት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ላለን ግንኙነት አስፈላጊ ነው” ብለው፥ በተጨማሪም የቅዱስ ቁርባን ስግደትን በትክክል መረዳቱ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል። “ቅዱስ ቁርባን እንደ ቀላል አለመመልከት ነገር ግን በውስጡ ከሚገኝ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድነትን በመፍጠር የእግዚአብሔርን መኖር በሚገልጽ መንገድ ከሌሎች ጋር እርስ በርስ መገናኘትን መማር ይገባል” ብለዋል።

ይህም የቅዱስ ቁርባንን ሕይወት በተጨባጭ መኖር ማለት እንደሆነ አስረድተው፥ አምልኮቱ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ ብርታትን እንደሚያፈስ፣ ሕይወታችንን ከሌሎች ሰዎች ጋር በማገናኘት እነርሱን የምናይበት መንገድ እንደሆነም ተናግረዋል።

ለሐዋርያዊ ለውጥ የቀረበ ጥሪ
የወንጌል ተልዕኮ ችግሮቻችን፥ የዘመናዊነት ችግሮችን ጨምሮ የተለየ አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎች መውደድን መማር፣ ልዩነትን ማሸነፍ እና ለመከራ ምላሽ መስጠት በእኛ ጥረት ብቻ የሚፈታ ሳይሆን የእግዚአብሔር ኃይል ሲታከልበት እንደሆነ አስረድተዋል።

በአሜሪካ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ብጹዕ ካርዲናል ፒየር ክሪስቶፍ፥ ዓይኖቻችን ተከፍተው በተለየ መንገድ ማሰብን እንድንማር ሁሉም ሰው ለእውነተኛ የቅዱስ ቁርባን ተሃድሶ እንዲጸልይ በመጋበዝ፥ “ከቅዱስ ቁርባን የሚገኝ ብርታት ወደ ሐዋርያዊ ለወጥ እንዲመራን እና ምእመናን ጠንካሮች እንዲሆኑ የሚያግዛቸው መንገዶች እንዲገልጡላቸው እግዚአብሔርን ከለመንን እና በእርሱ ለመመራት ፈቃደኞች ከሆንን የመንግሥቱ እውነተኛ ሐዋርያት እንሆናለን” በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

 

18 July 2024, 16:00