ከለዳውያን ጳጳሳት በቅድስት አገር “ሁለት መንግሥታት” የሚለው የመፍትሄ ሃሳብ ተግባራዊ እንዲሆን ጠየቁ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በጋዛ የሚካሄደው ጦርነት ወደ መላው የመካከለኛው ምስራቅ አገራት እየተቀጣጠለ ባለበት እና በየመን የሚገኙት የሁቲ አማፂያን ከእስራኤል ጦር ሠራዊት ጋር የሚሳኤል ተኩስ ልውውጥ እያደረጉ በሚገኙበት ወቅት በኢራቅ ጉባኤያቸውን ያካሄዱት የከለዳውያን ብጹዓን ጳጳሳት እስራኤል እና ፍልስጤም ሁለቱም በሰላም የሚኖሩበት “ሁለት መንግሥታት” የሚለው የመፍትሄ ሃሳብ ተግባራዊ እንዲሆን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በባግዳድ የተካሄደውን ዓመታዊው የኢራቅ ጳጳሳት ጉባኤን የመሩት ብጹዕ ካርዲናል ራፋኤል ሳኮ በቅርቡ ባደረጉት ንግግር፥ በመካከለኛው ምሥራቅ እየተከሰቱ ያሉት በርካታ ግጭቶች “በተለይም በቅድስት ሀገር” የሚካሄደው ጦርነት እጅግ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል። ብጹዕ ፓትርያርኩ በንግግራቸው ሁሉንም ዓይነት ብጥብጥ በማውገዝ፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘወትር ሰላምን እንዲያስከብር እና አውዳሚውን ጦርነት በአፋጣኝ ለማስቆም በንቃት እንዲሳተፍ አሳስበዋል።
ሁለቱ ተጎራባች ክልሎች በሰላም፣ በፀጥታ እና በመተማመን ይኖሩ ዘንድ
የከለዳውያን ብጹዓን ጳጳሳት በመግለጫቸው፥ ለአሥርተ ዓመታት ለዘለቀው የእስራኤል እና የፍልስጤም ግጭት ብቸኛው አዋጭ መፍትሔ፥ በሰላም፣ በደህንነት፣ በመረጋጋት እና በመተማመን” የሚኖሩበትን ሁለት ተጎራባች መንግሥታትን መፍጠር እንደሆነ ገልጸዋል።
ይህ አቋም ቅድስት መንበርን ጨምሮ ብዙዎች የሚደግፉት የመፍትሄ ሃሳብ ቢሆንም ነገር ግን የሃማስ አሸባሪዎች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥቅምት ወር 2023 በእስራኤል ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ ሃሳቡን አሁን ያለው የእስራኤል መንግሥት እንደሚቃወመው ይነገራል።
የኢራቅ ክርስቲያኖች ስቃይ
በክልሉ በሚኖሩ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች ላይ ትኩረቱን ያደረገው መግለጫው፥ “በተለይ ኢራቅን በተመለከተ በዚያች ምድር ላይ ሥር የሰደዱ፣ ክርስቲያኖችን በመቃወም መብታቸውን በመግፈፍ፣ በማግለል እና ንብረቶቻችውን በሕገወጥ መንገድ በመያዝ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ብዙ መከራ ደርሶባቸዋል” ሲል ገልጾ፥ ይህ እየደረሰ ያለው ከፍተኛ በደል በርካቶችን እንዲሰደዱ እንዳደረጋቸው አስታውሷል። በመሆኑም ብጹዓን ጳጳሳቱ በመግለጫቸው የኢራቅ መንግሥት እምነትን እና ብሔራዊ ትብብርን በማሳደግ እንዲሁም አገሪቱን በማልማት፣ ችሎታቸውን በመጠቅም ክርስቲያኖችን በመመልከት ፍትሃዊ እንዲሆን ጠይቀዋል።
ኢራቅ ውስጥ ለሁሉም ዜጎች እኩል መብት ይሰጥ!
ሲኖዶሱ የኢራቅ ባለ ሥልጣናት ክርስቲያኖችን ጨምሮ ለሁሉም የኢራቅ ዜጎች ተመሳሳይ የፖለቲካ እና የዜግነት መብቶች እንዲከበርላቸው በማለት ጥሪውን አቅርቧል። እንደ ዜጋ እኩል ውክልና እና የሥራ ዕድል እንዲሰጣቸው፣ መብታቸውም ሙሉ በሙሉ እንዲያስከብርላቸው ጠይቀው፥ አንዳንድ ቡድኖች መብታችን ነው በማለት የክርስቲያኖችን ንብረት መቀማታቸውን እንደማይቀበሉት በመግለጫው አክለዋል።
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ሺአ አል-ሱዳኒ ብጹዕ ፓትርያርክ ካርዲናል ሳኮ የከለዳውያን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን መሪ እንደሆኑ በቅርቡ ላወጡት ቆራጥ ድንጋጌ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ብጹዕ ፓትርያርክ ሳኮ የኢራቅ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪ እንደሆኑ እውቅና የሚሰጠውን ድንጋጌ ቁጥር 147 ፕሬዚዳንት አብዱል ላፍ ራሺድ ከሻሩ ወዲህ ፓትርያርኩ ለአንድ ዓመት ያህል ወደ ባግዳድ አለመመለሳቸው ይታወሳል።
ቅድሚያን ለኢራቅ ሕዝብ እንጂ ለአክራሪ መንግሥት መስጠት የለበትም
መንግሥት ከባለሥልጣናት እና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመሆን፥ ሕግና ፍትሕን በማስፈን፣ ሰላምን እና መረጋጋትን ለመፍጠር ተጨባጭ ዕርምጃዎችን እንደሚወስድ፤ ብሔራዊ አንድነትን ወደነበረበት በመመለስ የዜግነት ጽንሰ-ሐሳብን በማጠናከር እና የዜጎችን ሕይወት በማረጋገጥ፣ ለሕዝብ በቂ አገልግሎቶችን በመስጠት፣ እንዲሁም ከማንኛውም የአክራሪነት ጥቅም ይልቅ ለኢራቅ ሕዝብ ጥቅም ቅድሚያን መስጠት እንደሚገባ ሲኖዶሱ አሳስቧል።
ብጹዓን ጳጳሳቱ በመግለጫቸው በክልሉ የሚኖሩትን ክርስቲያኖች የወደፊት ዕጣ ፈንታ በማስመልከት ብጹዕ ፓትርያርክ ሳኮ ያቀረቡትን የአንድነት እና የመተሳሰብ ጥሪን በመድገም፥ “አንድ ሊያደርገን የሚገባው ዋናው እምነታችን እና መሬታችን ነው” ብለዋል።
በመካከለኛው ምሥራቅ ክርስቲያናዊ አንድነት እና መደጋገፍ
ከጎረቤት አገራት ብጹዓን ጳጳሳት ጋር ያላቸውን ወንድማማችነት የገለጹት የኢራቅ ጳጳሳቱ፥ ቤተ ክርስቲያን የነገ አዲስ ራዕይ እንደሚያስፈልጋት፥ እንዲሁም የክርስቲያኖችን ሚና፣ በኅብረተሰባቸው እና በአገራቸው ውስጥ ለማረጋጋት፣ ማንነታቸውን ለማስከበር እና ለማጎልበት ደፋር እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል ብለዋል።
“አንድነት ኃይላችን እና መዳናችን ነው” በማለት አስተያየታቸውን የሰጡት ብጹዓን ጳጳሳቱ፥ “ቁስሎች ቢኖሩንም አገሮቻችንን እና ዜጎቻችንን መውደድን እንቀጥላለን፤ ከእነርሱ ጋር አብሮ የመኖር ባህልን በማስፋፋት፣ የሌሎችን ልዩነቶች በማክበር እና በፍትሃዊ እና ሲቪል ማኅበረሰብ መካከል ተስፋን ለማጠናከር መተባበር እንፈልጋለን” በማለት መግለጫቸውን ደምድመዋል።