የቅዱስ ጳውሎስ ሴት ልጆች ማህበር በመገናኛ ብዙኃን ወንጌልን ማሰራጨት የጀመሩበትን 109ኛ ዓመት አከበሩ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ብፁዕ ጄምስ አልበሪዮን በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ እያደገ የመጣውን የመገናኛ ብዙኃን ተጽዕኖ ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀበትም። የመገናኛ ተቋማት እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የህዝብን የግንዛቤ አድማስ በመቅረጽ ረገድ ያላቸውን ኃይል አይቷል፥ ከዚህም በመነሳት ይህ አዝማሚያ ለበጎ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል ብሎ በማሰብ ነበር ወደ ሥራ የገባው፥ ከጎኑም አጋዥ ትሆነው ዘንድ የጉባኤው የመጀመሪያ የበላይ አለቃ የሆነች እማሆይ ቴክላ ሜርሎ የተባለች አንዲት ወጣት በትጋት ቆማለች።
አልበሪዮን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ወንጌልን በሚሰብከው ሐዋርያው ጳውሎስን ተምሳሌት በማድረግ፥ ያሉትን ሁሉንም የማህበራዊ ግንኙነት መንገዶችን በመጠቀም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለዓለም መስበክን ተልዕኮ በማድረግ በጣሊያን የሚገኘውን የቅዱስ ጳውሎስ ሚስዮናውያን እና የቅዱስ ጳውሎስ ሴት ልጆች ማኅበርን እ.አ.አ. በ1915 ዓ.ም. አቋቋመ።
ብፁእ አልበሪዮን “እንደ ቅዱስ ጳውሎስ መኖር አለባችሁ” ብሎ በማወጁ ምክንያት የቅዱስ ጳውሎስ ሴት ልጆች ይህንን መንፈስ በመከተል ሥራቸውን በትጋት ይሰራሉ።
በቅዱስ ጳውሎስና በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መሪነት በክርስቶስ ላይ ያተኮረ ሕይወት
የቅዱስ ጳውሎስ ሴት ልጆች መንፈሳዊነት የተመሰረተው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን የተልዕኳቸው አብነት በማድረግ ለኢየሱስ ክርስቶስ ያላቸውን ታማኝነት በማሳየት ላይ የተመሰረተ ሲሆን፥ የሐዋርያት ንግሥት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም በጉባኤያቸው ልዩ ቦታ አላት።
ከዚህም ባለፈ በጉባኤያቸው ውስጥ በየቀኑ መስዋዕተ ቅዳሴ በማሳረግ ለቅዱስ ቁርባን ከፍተኛ ክብርን የሚሰጡ ሲሆን፥ በስግደት የሚያሳልፉት ሰዓታት ስለሰው ልጅ በጸሎት እንዲያማልዱ እንደሚያስችላቸው እንዲሁም ተልዕኮዋቸውንም ያጠናክሩበታል።
የቅዱስ ጳውሎስ ሴት ልጆች እንደ ብርሃን እና እውነት ማዕከላት ሆነው የሚያገለግሉ በዓለም ዙሪያ የመጻሕፍት እና የመገናኛ ብዙኃን ማዕከላትን ይሠራሉ። እነዚህ ማዕከላት ሰዎች የእምነት ምንጮችን የሚያገኙበት፣ ትርጉም ያለው ውይይት የሚያደርጉበት እና እርስ በርስ የሚተዋወቁበት ቦታዎች ሆነው ያገለግላሉ። በተለይም፣ እያንዳንዱ ማእከል የጸሎት ቤቶች ያሉት ሲሆን፥ ይህም ጸሎት የተልዕኳቸው እና የመድረሻቸው የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ እንዲቆይ ያገለግላቸዋል።
በዚህም መሰረት “ተልእኮ ከጸሎት ይመጣል፥ ከተልዕኮ ደግሞ የጸሎት ብርታትን እናገኛለን” ሲል የጉባኤው ድህረ ገጽ ይገልጻል።
ጸሎት፣ ሐዋርያዊ ሥራ፣ ትምህርት፣ እና የማኅበረሰብ ሕይወት የጥሪአቸው ምሰሶዎች ናቸው። ለትምህርት የሚያረጉት ትጋት ከሁሉም የሕይወት ዘርፎች የሚያገኟቸውን እና የሚያገለግሉበትን ውስብስብ ዓለም እንዲገነዘቡ ያደርጋቸዋል፣ እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃንን በጎ አስተዋጽዖ እና ለውጤታማ የወንጌል ስርጭት ያለውን አቅም እንዲከታተሉ ያስችላቸዋል።
አዲስ ጅምር እና ቀጣይ እድገትን በማክበር ላይ
ሰኔ 22 የቅዱሳን ጴጥሮስ ወጳውሎስ ክብረ በዓል ሲሆን፥ ሰኔ 23 ደግሞ የቅዱስ ጳውሎስን ክብረ በዓል እንደ ጉባኤያችው እንዲያከብሩ እድል ስለሚሰጣቸው የሰኔ ወር ለቅዱስ ጳውሎስ ሴት ልጆች ልዩ ጠቀሜታ አለው።
በርካታ የጉባኤው አባላት ሃይማኖታዊ ክብረ በዓሎችን ያከበሩበት የዘንድሮው ሰኔ ወር በተለየ ሁኔታ አስደሳች ነበር። አንዳንዶቹ 25ኛ፣ ሌሎቹ 50ኛ እንዲሁም 60ኛ ኢዮቤልዮ በዓላቸውን አክብረዋል።
ከእነዚህም ውስጥ ከአርጀንቲና የመጡት ሲስተር፣ አፍሪካ እና እስያን ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከመጡ ከሌሎች በርካታ ሰዎች ጋር በመሆን እግዚአብሔር ጥሪያቸውን በጸጋው እንዲደግፍላቸው ጠይቀዋል።
በተመሳሳይ ከአንጎላ፣ ኮንጎ፣ ዛምቢያ እና ኬንያ የመጡ ዘጠኝ ወጣት ሴቶች ልዩ ስልጠናቸውን ጨርሰው ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. የመጀመሪያ ሙያዊ መሃላቸውን አድርገዋል።
ምስክርነት እና መነሳሳት
የቅዱስ ጳውሎስ ሴት ልጆች ከሙያዊ ስልጠናው በፊት የተልዕኮ ተግባራትን፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥዕላዊ መግለጫ እና የሚዲያ አጠቃቀምን የመሳሰሉ ትምህርታዊ ሥልጠናዎች ላይ ይሳተፋሉ። ይህ “የቅድመ-አከባበር” መርሃ ግብር ምዕራፍ ለሁለት ዓላማዎች የሚያገለግል ሲሆን፥ እነዚህም ሴቶቹ ስለጉባኤዎች ያላቸውን ግንዛቤን ለማስፋት እና ወጣት ሴቶች ለሃይማኖታዊ አገልግሎት የተሰጠ ህይወት እንዲያስቡ ለማነሳሳት ያገለግላል።
የሚስማማ እና የሚያድግ ጉባኤ
የጉባኤው አዲስ ዓርማን ጨምሮ በቅርቡ የወጡት መጽሐፍት እና የሚዲያ ዓርማ በአዲስ መልክ መታየቱ ገዳማዊያን እህቶች በድፍረት “የዘመኑን ምልክቶች ለማንበብ” እና ለእነሱ ምላሽ ለመስጠት ያላቸውን ቁርጠኝነት አጉልቶ ያሳያል ተብሏል።
የበላይ ሃላፊዋ ሲስተር አና ካያዛ ለአባላቱ ጠንካራ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ “ለውጡን አንፈራም፤ እንደ ተጨማሪ እድል ሆኖ እንጠቀመዋለን” ካሉ በኋላ፥ “እናንተ በአገልግሎታችው አዲስ ነገር ፈጣሪዎች ናችሁ፣ በየጊዜው ከሚለዋወጠው የሚዲያ ገጽታ ጋር እየተለማመዳችሁ ነው” ሲሉ የቅዱስ ጳውሎስን ሴት ልጆች አስታውሰዋቸዋል።
109ኛ ዓመታቸውን በማስመልከት “ስክሮሊ ቴሊንግ” የተሰኘ አዲስ የመገናኛ መተግበሪያ ያቀረቡ ሲሆን፥ ይህም የትኩረት ውስንነቶችን ለመቅረፍ ማራኪ እና መሳጭ ተሞክሮ ለመፍጠር ጽሑፍን፣ ምስሎችን፣ ቪዲዮዎችን እና ድምፆችን ማጣመርን የሚያካትት አዲስ የዲጂታል የታሪክ አቀራረብ ዘዴ ነው ተብሏል።
የቅድስት መንበር የተግባቦት ጽ/ቤት ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ፓኦሎ ሩፊኒ ገዳማዊያኑ ያበለጸጉትን መተግበሪያ በማድነቅ “ይህ የቅዱስ ጳውሎስ ሴት ልጆች በዘመናዊው ዓለም በዘመናዊ ቋንቋ ለመገኘት ያላቸውን ብቃት ያሳያል” ብለዋል።
ሲስተር ካያዛ በመጨረሻም ባስተላለፉት መልዕክት የሃይማኖት ጉባኤያቸው ያለውን ዓለም አቀፋዊ ተደራሽነት በማስታወስ “በሁሉም አህጉራት እና ከ50 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ እንገኛለን” ካሉ በኋላ “ይህ እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት እና በጉባኤው እና በአጠቃላይ በቤተክርስቲያን ውስጥ ለተጨማሪ ጥሪዎች በመጸለይ የምንቀጥልበት ምክንያት ነው” ብለዋል።