የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በመሬት መንሸራተት የተጎዱትን ለመርዳት መዘጋጀቷ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በደቡብ ኢትዮጵያ ጎፋ ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት ባስከተለው አደጋ ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን፥ በአደጋው የተጎዱትም ሰብዓዊ ዕርዳታው ቶሎ እንዲደርሳቸው በመማጸን ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።
በኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ተራራማ አካባቢ ሐምሌ 14 እና 15 በጣለው ከባድ ዝናብ የመጀመርያው የመሬት መንሸራተት አደጋ የተከሰተ ሲሆን ሁለተኛው አደጋ በአደጋው የተጎዱትን ሰዎች ለማትረፍ በተሰበሰቡት ሰዎች ላይ እንደነበር ይታወሳል።
የመጨረሻው የሟቾች ቁጥር ከ500 በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል
ሐሙስ ዕለት የሟቾች ቁጥር ወደ 257 የደረሰ ቢሆንም ነገር ግን የመጨረሻው የተጎጂዎች ቁጥር ከ500 በላይ እንደሚሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (OCHA) ገልጿል። በሰው ሕይወት ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ በአፍሪካ ቀንድ አገር በተመዘገበው እጅግ አስከፊው የመሬት መንሸራተት አደጋው የተፈናቀሉትን፣ የቆሰሉትን እና ቤታቸው የወደመባቸውን ጨምሮ ከ50,000 በላይ ሰዎችን በእጅጉ ጎድቶአቸዋል።
ከእነዚህም መካከል በሁለት መንደሮች (ቀበሌዎች) ውስጥ የሚገኙ 5,776 ቤተሰቦች አስቸኳይ መጠለያ እንደሚያስፈልጋቸው ታውቋል። በተጨማሪም በተለይ ለችግር የተጋለጡ እና አፋጣኝ ድጋፍ እና እንክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸው፣ 1,367 ህጻናትን ጨምሮ በአጠቃላይ 596 አባወራዎች በአደጋው ምክንያት ተፈናቅለዋል። የችግሩ መጠን በፍጥነት መጨመሩን የገለጸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፥ ቀጣይነት ያለው ዝናብ ተጨማሪ የመሬት መንሸራተትን ሊያስከትል እንደሚችል ገልጿል።
በሥፍራው የሰብዓዊ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው!
በአካባቢው የሚገኙት የቤተ ክርስቲያን ምንጮች ፊደስ ለተሰኘ የዜና ወኪል በክልሉ ያለው ሰብዓዊ ሁኔታ አሳሳቢ እንደ ሆነ አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ለጎፋ ዞን ሕዝብ በላኩት መልዕክት አደጋው አሳዛኝ እንደሆነ ተናግረው፥ የብጹዓን ጳጳሳቱን ልባዊ ሐዘን ገልጸዋል። ወዳጅ ዘመዶቻቸውን በሞት ላጡት በሙሉ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የማያወላውል ድጋፍ እንደምትሰጥ አረጋግጠዋል።
የቤተ ክርስቲያኒቱ የዕርዳታ ጥረቶች
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ከተለያዩ ኤጀንሲዎች፣ ባለስልጣናት እና ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የዕርዳታ እና የድጋፍ ሥራዎችን በማጠናከር ላይ ትገኛለች። የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በክልሉ ስታበረክት በቆየችው የረጅም ጊዜ አገልግሎት እና ቅንጅት ለተቸገሩት ዕርዳታን በፍጥነት እና በብቃት የማድረስ ቀልጣፋ ልምድ እንዳላት ይታወቃል።
ድንገተኛ የሕክምና አገልግሎት፣ የፍለጋ እና የማዳን ሥራዎች የመሳሰሉ ሕይወትን የማዳን ተግባራት ቅድሚያ ተሰጥቶባቸዋል። በሽታን መከላከል፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እና ንፅህና አጠባበቅን ጨምሮ ከቁሳቁስ እርዳታ በተጨማሪ የተጎጂዎችን ጭንቀት እና ሕመም ለመቆጣጠር ቤተ ክርስቲያኒቱ የምክር አገልግሎት በመስጠት ላይ ትገኛለች።
ለአብሮነት የቀረበ ጥሪ
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል በመልዕክታቸው፥ በአገሪቱ የሚገኙ ካቶሊክ ምዕመናን እና በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች በሙሉ ለተጀመረው የእርዳታ ሥራ በሚችሉት ሁሉ የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ደቡብ ኢትዮጵያ ባለፉት ወራት በተለይ በከባድ ዝናብ እና በጎርፍ መመታቷ ሲታወስ፥ ከባድ ዝናብ በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰት ቢሆንም የአየር ንብረት ለውጥ አደጋን የሚያስከትል ጎርፍ እንደሚጨምር እና ይህም የመሬት መንሸራተትን እንደሚያስከትል ይታወቃል።