አባ ሰባስቲያኖ ዳምብራ አባ ሰባስቲያኖ ዳምብራ  

አባ ሰባስቲያኖ በእያንዳንዱ ሰው ልብ ውስጥ ዘወትር የሰላም ፍላጎት እንዳለ ገለጹ

አባ ሰባስቲያኖ ዳምብራ በፊሊፒን ሚንዳናኦ ደሴት ውስጥ በክርስቲያኖች እና በሙስሊሞች መካከል ሰላም እና የጋራ ውይይት እንዲያድግ ላደረጉት ከፍተኛ ጥረት “የአቡነ ጆርጅ ባርሊን ወርቃማ መስቀል” በመባል የሚታወቅ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በፊሊፒንስ የምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ይህንን ሽልማት ለአባ ሰባስቲያኖ ዳምብራ እንድትሰጥ ያነሳሳት፥ ካኅኑ በፊሊፒን ሚንዳኖ ደሴት ውስጥ በሚኖሩ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች መካከል ሰላምን እና የጋራ ውይይትን ለማሳደግ ያደረጉት ጥረት እንደ ሆነ ተገልጿል። አባ ሰባስቲያኖ ዳምብራ ጳጳሳዊ የውጭ ተልዕኮዎች ተቋም አባል እና በሃይማኖቶች መካከል የጋራ ውይይት መድረክ መሥራች ናቸው።

በፊሊፒን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን “የብጹዕ አቡነ ጆርጅ ባርሊን ወርቃማ መስቀል” ሽልማት መዘጋጀት የጀመረው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1906 ዓ. ም. ለመጀመሪያ ጊዜ የጵጵስና ማዕረግ የተሰጣቸው የአገሪቱን ካኅን መታሰቢያ እንደሆነ ተገልጿል። የሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ የተዘጋጀው የፊሊፒን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ምልዓተ ጉባኤያቸውን ባካሄዱበት ሰኔ 30/2016 ዓ. ም. እንደ ነበር ታውቋል።

በጣሊያን የሲሲሊ ደሴት ተወላጅ የሆኑት የ82 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ አባ ሰባስቲያኖ ዳምብራ በቅርቡ ከሮም ሀገረ ስብከት የ “አባ ሳንቶሮ” ሽልማት ማግኘታቸው ይታወሳል። ለአባ ሰባስቲያኖ ዳምብራ ሽልማቱ የተሰጣቸው በፊሊፒን ሚንዳኖ ደሴት ውስጥ ከ40 ዓመታት በላይ በሚስዮናዊነት ባበረከቷቸው የስብከተ ወንጌል አገልግሎቶች እና መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ባስመዘገቧቸው ውጤቶች እንደሆነ ታውቋል።

በሽልማቱ ደስተኛ እንደሆኑ የገለጹት አባ ሰባስቲያኖ፥ በቃለ ምልልሳቸው፥ “በተለይ የፊሊፒን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እኔ ባስመዘገብኳቸው ውጤቶች ብቻ ሳይሆን ባለፉት ዓመታት ከሥራዬ የዳበሩትን ልዩ ልዩ ገጽታዎችም ስለተገነዘበች ነው” ስሉ አስረድተዋል። በተልዕኮአቸው የመጀመሪያ ዓመታት በአማፂ ቡድኖች እና በአገሪቱ ጦር ኃይሎች መካከል አስታራቂ ሆነው ለሰላም አስተዋፅዖ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።

በወቅቱ ከእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር ለመወያየት የሚያግዙ ዕውቀቶችን መቅሰማቸውን የገለጹት አባ ሰባስቲያኖ፥ እንደ ጎሮጎሮሳውያኑ በ1983 ዓ. ም. ወደ ፊሊፒንስ ተመልሰው “ስልሲላህ” የተሰኘ እንቅስቃሴን እንደጀመሩ ተናግረው፥ የሁለቱ እምነቶች ተከታዮች በእንቅስቃሴው በመታገዝ እንደ ጎሮጎሮሳውያኑ    ከ1984 ዓ. ም. ጀምሮ አብረው መሥራት መጀመራቸውን አስረድተዋል።

ከፊሊፒንስ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ እውቅናን ያገኘ፣  ሕይወታቸውን ለኢየሱስ ክርስቶስ እና ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ያቀረቡ ምእመናንን፣ ባለትዳሮችን፣ ካኅናትን፣ ደናግልን፣ የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎችን፣ ወጣቶችን እና በቅርቡም አንድ ጳጳስ አባል የሆኑበትን “የኤማሁስ የውይይት እንቅስቃሴን” እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1987 ዓ. ም. መመሥረታቸውን አባ ሰባስቲያኖ ገልጸዋል።

“የፊሊፒንስ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ እንቅስቃሴው የሚያበረክታቸው አገልግሎቶችን በትኩረት እንደሚከታተል እና ሽልማቱን ሊሰጥ የወደደው በዚህ ምክንያት ነው” ሲሉ ተናግረው፥ በክርስቲያኖች እና በሙስሊሞች መካከል ሰላምን መፍጠር እና የጋራ ውይይት ማሳደግ ከፍተኛ ጥረት እንደሚጠይቅ ገልጸው፥ ገና ከጅምሩ ብዙ ፈተናዎችን ማለፍ እንደ ነበረባቸው እና በወቅቱ አዲሶቹ የተልዕኮ መንገዶች እና የጋራ ውይይቶች አካል ተደርጎ ይቆጠር የነበረውን ሁለተኛ የቫቲካን ጉባኤ መመሪያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ መሞከራቸውን አስረድተው፥ በፊሊፒን ሚንዳናኦ ደሴት ውስጥ አገልግሎታቸውን ሲጀምሩ የአገሪቱ ማርሻል ሕግ ተግባራዊ ይሆን እንደ ነበር፥ በክርስቲያኖች እና በሙስሊሞች መካከል ጥቃት እና ጥላቻ እንደ ነበር አባ ሰባስቲያኖ አስታውሰዋል።

ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ ሥቃይ እና አለመግባባቶች እንደ ነበሩ፣ መጀመሪያ ላይም ጭፍን ጥላቻ እና ጥርጣሬ እንደ ነበር፣ በአንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ተቃውሞ እና ጥርጣሬዎች ቢኖሩም አሁን ግን በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያኑ ተልዕኮ ላይ ሁሉም ሰው ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው፣ አብዛኛው ሙስሊም በሆነባቸው አንዳንድ የደሴቲቱ አካባቢዎች መንግሥት ጣልቃ በመግባት የሰላም ስምምነቶችን ለማድረግ እና የራስ ገዝ አስተዳደር መዋቅሮችን ለመዘርጋት እየሞከረ እንደሚገኝ አባ ሰባስቲያኖ ገልጸዋል።

በፊሊፒንስ የምትገኝ እና መላዋ ቤተ ክርስቲያን በሲኖዶሳዊነት መንገድ እየተጓዙ ስለሆነ የጋራ ውይይቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በዓለም ሰላም አድማስ ላይ አዳዲስ ችግሮች እያንዣበቡ መሆናቸውን፣ የሰላሙ ሂደት በሁከት እና በብጥብጥ ውስጥ የሚያልፍ መሆኑንም ተናግረዋል።

“ከሙስሊም ማኅበረሰብ ጋር ያለን ግንኙነት ጥሩ ነው” ያሉት አባ ሰባስቲያኖ፥ “ሲልሲላ” የተሰኘ እንቅስቃሴ በካቶሊክ ሚስዮናዊ ቢጀመርም የሁሉም ሰው እንቅስቃሴ እንደሆነ ቢያውቁትም፣ እንደ ሌሎች የዓለም ክፍሎች በፊሊፒንም አሸባሪ ቡድኖች መኖራቸውን ችላ ልንል አንችልም ብለው፥ በዓለም አቀፍ ወንድማማችነት መንፈስ ውስጥ ለመልካም እና ለሰላም የበኩላችንን አስተዋፅኦ እንድናበረክት ተጋብዘናል ብለዋል።

እስከ ዛሬ ያደረግነው የጋራ ውይይት እና የሰላም ጉዞ እግዚአብሔር በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ያስቀመጠውን ፍቅር ለመካፈል ካላቸው ፍላጎት የተነሳ እንደሆነ እና በእያንዳንዱ ሰው ልብ ውስጥ የሰላም ፍላጎት በመኖሩ በአመፀኞች መካከል ተልዕኮአቸውን እንደሚቀጥሉ በፊሊፒን ሚንዳኖ ደሴት ውስጥ ከ40 ዓመታት በላይ በሚስዮናዊነት ያገለገሉት አባ ሰባስቲያኖ ዳምብራ ተናግረዋል።

 

 

 

 

15 July 2024, 16:33