የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የብጹአን ጳጳሳቱን ልዑካን በኒው ዴሊሂ ሲቀበሉ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የብጹአን ጳጳሳቱን ልዑካን በኒው ዴሊሂ ሲቀበሉ 

የህንድ ብጹአን ጳጳሳት ከጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ጋር ተገናኝተው ክርስቲያኖች ላይ ስለሚደርሰው ጥቃት ተወያዩ

በብጹእ አቡነ አንድሪውስ ታዝሃት የሚመራ የቤተክርስቲያን ልዑካን ቡድን በህንድ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሄደውን ፀረ-ክርስቲያን ጥቃቶችን በተመለከተ የሃገሪቱን ብጹአን ጳጳሳቱን ስጋት ለመግለጽ አዲስ ከተመረጡት ብሄራዊ የሂንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የህንድ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች እያጋጠሟቸው ስላለው ጥላቻ እና ጥቃት ያላቸውን ስጋት ለጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ ገልጸዋል።

በህንድ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ፕረዚዳንት ብጹእ አቡነ አንድሪውስ ታዝሃት የተመራው የጉባኤው ልኡካን ቡድን ባለፈው ሳምንት ሃምሌ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. አዲስ የተመረጡትን ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲን በኒው ዴሊሂ ውስጥ አግኝተው በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እና ትንኮሳ ለማስቆም ጣልቃ እንዲገቡ መጠየቃቸውን ዩሲኤ (UCA) የተባለው የኢስያ ካቶሊክ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የፀረ-ልወጣ ህጎችን አላግባብ መጠቀም

ብጹአን ጳጳሳቱ “ልባዊ” ብለው በገለጹት የ45 ደቂቃ ስብሰባ ላይ፣ አራት አባላት ያሉት የልዑካን ቡድኑ ለሂንዱ ብሔርተኛ ብሃርትያ ጃናታ ፓርቲ መሪ እንደገለጹት፣ የፀረ-ልወጣ ሕጎችን አለ አግባብ ጥቅም ላይ መዋላቸውን እና በአስገድዶ ሃይማኖትን የማስቀየር የውሸት ሰበብ ምክንያት በክርስቲያኖች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው ጥቃት ማዘናቸዋን የሚገልጽ አጭር ጽሁፍ አቅርበውላቸዋል።

መድልዎ

ብጹአን ጳጳሳቱ ያወጡት የማስታወሻ ጽሁፉ የቤተክርስቲያን የረዥም ጊዜ ጥሪ የሆነውን በህንድ ውስጥ ለሚገኙ ‘ዳሊት’ የሚባሉ ዝቅተኛ የክርስቲያን ማህበረሰብ ክፍሎች የተቀመጡትን ልዩ ልዩ ጥቅማ ጥቅሞችን ማለትም እንደ በመንግስት ስራዎች፣ በትምህርት ተቋማት እና በገንዘብ ዕርዳታዎች ውስጥ ያላቸውን ኮታዎች ማስጠበቅ የመሳሰሉትን መንግስት እንዲያራዝም በድጋሚ ጥሪ አቅርቧል።

ክርስቲያን እና ሙስሊም የዳሊት ማህበረሰብ ከህንድ ነፃነት በኋላ የዘውድ ስርዓቱን የማይከተሉ በመሆናቸው ከነዚህ ልዩ ጥቅሞች መገለላቸው ቀጥሏል። አንዳንድ የሂንዱ ሃይማኖት ተከታይ ቡድኖች እንደሚጠይቁት ሁሉ፣ የቤተክርስቲያኒቷ መሪዎችም ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ የክርስቲያን ማህበረሰቡ ሲያገኙ የነበረውን የመንግስት ልዩ ጥቅሞች እንዲያስቀጥሉ በአጽንዖት ጠይቀዋል።

እንደ እነዚህ ቡድኖች አረዳድ ክርስቲያን የሆኑ ነገዶች የጎሳ ሃይማኖቶችን ስለማይከተሉ፣ አንዴ ከተቀየሩ በኋላ እንደ ጎሳ ሊቆጠሩ አይገባም በማለት ይሞግታሉ።

ማስታወሻ ጽሁፉ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ‘በብሔራዊ የአናሳ ብሄረሰብ ኮሚሽን’ እና በብሔራዊ የአናሳ ማህበረሰብ የትምህርት ተቋማት ኮሚሽን ውስጥ የክርስቲያን ውክልና አለመኖሩን ያሳወቀ ሲሆን፥ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ክርስቲያኖች እንዲሾሙም ጠይቋል።

ክርስቲያናዊ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ላይ የሚደርሱ ያልተገባ ተግዳሮቶች

በተጨማሪም የክርስቲያኑ ማኅበረሰብ በተለይም በትምህርት፣ በጤና አጠባበቅ እና በማኅበራዊ ደኅንነት ላይ የሚያበረክቱትን ጉልህ አስተዋጾ በማሳታወስ፥ ሆኖም ግን ክርስቲያናዊ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በውጭ ምንዛሪ ደንብ ህግ ስር (FCRA) ምዝገባቸውን ለማደስ ሲሄዱ ስለሚያጋጥሟቸው “ያልተገቡ ተግዳሮቶች” ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።

ሞዲ ህንድን እንዲጎበኙ ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ያቀረቡት ግብዣ

ከዚህም ባለፈ ማስታወሻው ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ሰኔ ወር ላይ በደቡብ ጣሊያን በተካሄደው የጂ-7 የመሪዎች ስብሰባ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ህንድን እንዲጎበኙ ያቀረቡትን ግብዣ በማወደስ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትን ወደ ሕንድ የማምጣት ሂደቱ እንዲፋጠን ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርቧል።

በስብሰባው ወቅት የልዑካን ቡድኑ ከሚያዚያ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በሰሜን ምስራቅ ህንድ ማኒፑር ግዛት ውስጥ በተቀሰቀሰው የጎሳ ጥቃት ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ጣልቃ እንዲገቡ ጠይቀዋል።
 

17 July 2024, 14:36