የተረቀቀው የድርጊት መርሃ ግብር ለሲኖዶሱ ጉባኤ ግልጽ መመሪያ ይሰጣል መባሉ ተገለጸ!
የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
አቡነ ፓውሎ ማርቲኔሊ የድርጊት መርሃ ግብሩ ከታተመ በኋላ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሰነዱ “በመጪው ጥቅምት ወር በሚካሄደው ሁለተኛ የሲኖዶስ ጉባሄ ዝግጅት በተሻለ ሁኔታ መረዳት ይቻላል” ብለዋል።
በቃለ ምልልሱ፣ የደቡብ አረቢያ ሐዋርያዊ እንደራሴ የድርጊት መርሃ ግብሩ በጥቅምት ወር ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለሚደረጉ ውይይቶች “ግልጽ መመሪያ” የሚሰጥ “ግልጽ እና ቀላል” ሰነድ ነው በማለት አወድሰዋል።
ከአቡነ ፓኦሎ ማርቲኔሊ ጋር የተደርገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል ...
ጥይቄ፡ የድርጊት መርሃ ግብሩን እንዴት ይመለከቱታል፣ የእርሶ ሐሳብስ ምንድነው?
የእኔ የመጀመሪያ ምላሽ ሰነዱ በጣም ግልጽ እና ቀላል ነው። በጥቅምት ወር ለውይይቱ በጣም ግልጽ የሆነ መንገድ ይከፍታል። ባለፈው ዓመት ሰነዱ በጣም ብዙ ገጽታዎች ነበሩት። የድርጊት መርሃ ግብሩን ሐሳብ በሚገባ ለማስረጽ ይቻል ዘንድ አሁን ብዙዎቹ ጭብጦች ለተለያዩ ኮሚሽኖች ተሰጥተዋል። አዲሱ የድርጊት መርሃ ግብር በደንብ ተሠርቷል፣ እናም የበለጠ ትኩረት ያደረገው በሲኖዶሳዊነት ጭብጥ ላይ ነው።
ጥያቄ፡ በዚህ ሰነድ ውስጥ የተጠቆሙት አስገራሚ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
በመጨረሻም፣ ከብዙ ውይይቶች በኋላ፣ ለሲኖዶሳዊነት የበለጠ ግልጽ ትርጉም አለን። ሲኖዶስ ለቤተክርስቲያን አዲስ ቃል ባይሆንም ማለት ነው። በሰነዱ መሰረት በዚህ በጥቅምት ወር የሚብራሩ የተለያዩ ገጽታዎች አሉ። የሚብራሩት አንዳንድ መሪ ሃሳቦች አንድነት ለእኛ የልዩነት ስምምነት፣ ወንድ እና ሴት - እህቶች እና ወንድሞች መካከል ያለው መረዳዳት ፣ በጸጋ እና በአገልግሎት መካከል ያለውን ልዩነት እና የቅርብ ግንኙነት ለመረዳት ነው። በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ስለ ክርስቲያናዊ አጀማመር፣ ማንነት እና የክህነት ሚና፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅ፣ በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ውሳኔ አሰጣጥ እና ሌሎችም በሚለው ጭብጥ ላይ እንነጋገራለን። በጥቅምት ወር ለምናደርጋቸው ውይይቶች ግልጽ አቅጣጫ የሚሰጠውን ይህን ሰነድ በማግኘታችን በጣም ደስተኛ ነኝ።
ጥያቄ፡ ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ከዚህ ሰነድ አንጻር፡ የጥቅምት ወር ሲኖዶሱን ጉባኤ እንዴት ያዩታል?
የሲኖዶሱ ጉባኤ ራሱ በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ በጣም አስፈላጊ ነው። ከቅዱሳን አበው ጳጳሳት እና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከተውጣጡ ጳጳሳት ጋር መሆን ታላቅ የስብከተ ወንጌል ዝግጅት ነው። በዚህ ሲኖዶስ ጉባኤ ውስጥ ጳጳሳት ብቻ ሳይሆኑ በውይይት ጉዳዮች ላይ ድምጽ የመስጠት መብት ያላቸው ካህናት፣ ደናግላን፣ እና ምእመናን አሉ። በጣም ጥሩ ነው ምክንያቱም ከአለም ዙሪያ የተገኙትን አስደናቂ ተሞክሮዎች ስለምንጋራ ፣የቤተክርስቲያንን ህይወት ከተለያዩ ባህሎች ፣ሀገሮች ስለምንረዳ እና ብዙ እንማራለን ። ይህ ራሱ የሲኖዶሱ ትልቅ ሀብት ነው።
በድጋሚ፣ ውይይታችንን ለመምራት በየድርጊት መርሃ ግብር ውስጥ የተሰጡ ጭብጦች አሉን። መላው የእግዚአብሔር ሕዝብ በሀገረ ስብከቱ እና በአህጉራዊው ሂደት እንዲሳተፍ መጠየቁን ልብ ልንል ይገባል። በአገረ ስብከታችን ስላለው ሲኖዶስ በምእመናን ዘንድ ታላቅ ጉጉት አለ።
ጥያቄ፡ በዚህ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ የቤተክርስቲያኒቱን የወደፊት እጣ ፈንታ እንዴት ያዩታል?
ሲኖዶሳዊነትን ለወደፊት እንደ ዝግጅት አድርጎ መረዳት ይቻላል። ሲኖዶሳዊ ቤተ ክርስቲያን አዲስ ቤተክርስቲያን ሳይሆን የማንነት እውነትን የሚያጎለብት ያው ቤተክርስቲያን ነው። ሲኖዶሳዊነት ሁል ጊዜ ‘ሕብረት’ ከሚለው ቃል ጋር የተያያዘ ነው። ሲኖዶሳዊ መንገድ በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ በቤተ ክህነት መካከል ያለውን የኅብረት ክብር መኖር ነው። ይህ ጭብጥ በባህረ ሰላጤው ያለችውን ቤተክርስቲያን በደንብ ያገናኛል። እኛ የስደተኞች ቤተ ክርስቲያን ነን፣ ብዙ ብሔረሰቦች፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎች እና ሥርዓቶች አሉን። ግን እዚህ በሙስሊሞች መካከል ቤተክርስቲያን ምን መሆን አለበት? ለእኔ በመጀመሪያ እና ከሁሉም በላይ፣ እዚያ ቤተክርስቲያን መሆን ማለት የክርስቶስ ምስክር መሆን ማለት ነው። የእግዚአብሔር ሕዝቦች በልዩነት ውስጥ ያለው አንድነት ከሁሉ የተሻለው መመስከር ነው። ለኛ አንድነት የልዩነቶች መስማማት ነው። ስለዚህ፣ ሲኖዶሳዊነት ወደ ትንቢታዊ ተስፋ እየመራው ያለው ወደዚህ እውነታ ነው።
ጥያቄ፡ በዚህ ሰነድ እና በሲኖዶሱ ጉባኤ ላይ በአገረ ስብከቶ ላሉት ምእመናን መልእክትዎ ምንድነው?
በቅድሚያ ሁሉም ምእመናን ከሲኖዶሱ እና ከሙሉ ዝግጅቱ ጋር በጸሎት እንዲተባበሩ እጋብዛለሁ። የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤውን በጸሎታቸው አጅበው ለሚሄዱት ምእመናን ሁሉ ይህ በጣም አስፈላጊው ክፍል ነው። ለመንፈስ ቅዱስ ተግባር ክፍት እንድንሆን ምእመናን እንዲጸልዩ እጋብዛለሁ። እንደውም ነፍስ በሥጋ እንዳለች እርሱ በቤተክርስቲያን አለ። በሁለተኛ ደረጃ፣ ከዚህ ረጅም ሂደት እና በዚህ ሲኖዶሳዊ ጉዞ ውስጥ የቤተክርስቲያንን መንገድ ከየት እንደደረሰ ለመረዳት ሁሉም የድርጊት መርሃ ግብሩን እንዲያነቡ እጠይቃለሁ።
እንዲሁም የሲኖዶሱን ጉባኤ ከቫቲካን በሚወጡ የመገናኛ ብዙኃን ጽሑፎች ይከታተሉ። እኔም ልክ እንደ ባለፈው አመት በጉባኤው ወቅት ከህዝቦቼ ጋር ለመገናኘት አንዳንድ አስተያየቶችን እጽፋለሁ።
ከሁሉም በላይ ደግሞ የሲኖዶሱን ሂደት ማለትም አብሮ የመሄድ መንፈስን የበለጠ እና የበለጠ ይኑሩ። በባህረ ሰላጤው ከምትገኘው ቤተክርስቲያናችን እንደዚህ ባለ ብዙሃነት ‘አብረን መመላለስን’ የተሻለ ልምድ የምናገኝበት ሌላ ቦታ የለም። የተጠመቅን አንድ ማንነት ይዘን አብረን እንጓዝ። ራሳቸውን ከቤተ ክርስቲያኗ ያገለሉትን፣ እንደ ተገለሉ የሚሰማቸውን፣ አናሳ የሚባሉትን፣ የማይፈለጉትን ወይም ያልተሰሙትን ለማግኘት እንሞክራለን። የእኛ ሀላፊነት፣ ከሁሉም በፊት፣ ሁሉም ሰው በቤተክርስቲያን ውስጥ ማንም ወደ ኋላ እንደማይቀር፣ ሁሉም እንደሚያስፈልግ፣ ሁሉም አስፈላጊ እንደሆነ እንዲሰማቸው ማድረግ ነው። ቤተክርስቲያን የሁሉም ሰው ቤት ናት፣ እና በዚህ ቤት ውስጥ፣ ሁሉም እንኳን ደህና መጣችሁ ሊባሉ ይገባል፣ ሁሉም አብረው ሊጓዙ ይገባል።
በመጨረሻም፣ ለጳጳሳችሁ እና የሮም የሲዶስ አባል ለሆንኩኝ ለእኔ መጸለይ እንዳትረሱ!